“የተዘራው አልበቀለም፣ በማሳው ልምላሜ አልታየም”

46

ባሕርዳር፡ መስከረም 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ማሳው ደርቋል፣ ምድሩ ዘር ቆርጥሟል፣ የደረቀችው ምድር አለመለመችም፣ የምህረት ዝናብ በዚያች ሰማይ አልወረደችም፣ ጎርፍ አልታየም፣ በክረምት የሚደነፉት ወንዞች አልጠነከሩም፣ ልጆች በክረምት ጭቃ አላቦኩም፣ ዝናቡ ቸሬ እያሉ ሕፃናት ዝናብ አልተመቱም፡፡ እረኞች ከብቶቻቸውን አላጠገቡም፣ ላምና በሬዎች፣ ፍየልና በጎች ለምለም እሳር አልጋጡም፤ ምድሪቱ እንደደረቀች ከርማለች፣ እንደደረቀችም አለችና፡፡

ለወትሮው “ሞትና ክረምት አይቀርም” ይባል እንዳልነበር ዘንድሮ ግን በዚያች ምድር ክረምት ቀርቷል፣ ሰማዩ ጨክኗል፣ ምድር እርጥበትን ተጠምታለች፣ ቡቃያን ናፍቃ ከርማለች፣ የዝናብ ጠልን እየፈለገች ተነፍጋለች፡፡ የወንዞችን መሙላት፣ የተራራዎችን አረንጓዴ ውበት ስትመኝ ሳታገኝ ቀርታለች፡፡

በጎተራው ያለችን ዘር በምድር ላይ የበተኑ ገበሬዎች ቡቃያ አልተመለከቱም፣ የበሬዎቻቸውን ድካም አላገኙም፣ ተስፋ ያደረጉትን አላዩም፡፡ በዝናብ አብቅለው፣ በፀሐይ አብስለው ለልጆቻቸው እሸት አላቀመሱም፣ ላሞቻቸውን ልምላሜ አብልተው ወተት አላገኙም፡፡

“አርሶ መራብና ተኩሶ መሳት ያንገበግብ የለ እንደ እግር እሳት” እያለ የሚቀኘው የሀገሬው ሰው አርሶ አዝመራ አላየም፣ ቡቃያ አላበቀለም፣ በሬና ገበሬ ደክመው ቀርተዋል፣ ረሃብ አንዣቦበታል፡፡ በዚያች ምድር የአዝመራ መውቂያው አውድማ አይለቀለቅም፣ ጎተራው አይስተካከልም፡፡ ለምን ቢሉ ማሳው ሰብል የለውምና፡፡ ምድር ቡቃያ ካልሰጠች ገበሬ ሰማይ ይደፋበታል፣ አብዝቶም ያዝናል፣ ይደነግጣል፡፡ ጌታ ኾይ ጉርሳችን አትንሳን፣ ያለ እራት አታሳድረን፣ በረሃብም አትቅጣን እያለ ይማጸናል፡፡

ከመከራ ሁሉ የከፋው መከራ ምድር እርጥበትን በተጠማች፣ ዘርም ባላበቀለች፣ ጎተራም ባዶዋን ባደረች ቀን ነው፡፡ ምድር ልምላሜን ባጣች፣ ሰብልንም በነፈገች ዘመን ረሃብ በምድሯ ላይ ይነግሳል፡፡ እናት እና ልጅ ይላቀሳሉ፣ ፆም አድረው ጾም ይውላሉ፣ እንስሳት የምትበጠስ ቅጠል አጥተው በጠኔ ይወድቃሉ፡፡

በአማራ ክልል በዋግኸምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰሃላ ሰየምት ወረዳ ምድር እርጥበትን እንደተጠማች ከርማለች፡፡ ዝናብ የሚበዛባቸው፣ የማዕበል ድምጽ የሚሰማባቸው፣ አፍላጋት የሚጎለብቱባቸው የሐምሌና የነሐሴ ወራት ዝናብን ሳይሰጡ አልፈዋል፡፡ በክረምት አርሰው በበጋ ለማፈስ ተስፋ ያደረጉ ገበሬዎችም ባዶ እጃቸውን ቀርተዋል፡፡

መኮንን በላይ ይባላሉ፡፡ ነዋሪነታቸው በዋግኸምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰሃላ ሰየምት ወረዳ 09 ቀበሌ ነው፡፡ የሰባት ቤተሰብ አባወራ ናቸው፡፡ እያረሱ ደካማ እናታቸውን ይጦራሉ፣ ልጆቻቸውንም ያሳድጋሉ፡፡ እንደወትሮው ሁሉ ምድር የምህረት ዝናብን ታገኛለች በሚል ተስፋ ሞፈርና ቀንበራቸውን አሰናድተው፣ በሬዎቻቸውን ይዘው ዘር ለመዝራት ተሰናድተው ነበር፡፡ ምድር ግን ልምላሜን እንደተጠማች፣ እርጥበትንም እንደናፈቀች ቀረችና ጨነቃቸው፡፡

ስለገጠማቸው ችግር ሲነግሩን “የተዘራው ዘር አልበቀለም፣ ደክመን ቀረን፣ ከብቶቻችን በረሃብ ተወግተዋል፣ እንዳይሸጡ ደክመዋል፣ እንዳንተዋቸው የሚበሉት የላቸውም፣ የረሃብ አደጋ ተከስቷል፤ ያለው ነገር አሳሳቢ ነው፤ ተነግሮ የሚዘለቅ ነገር የለውም” ነው ያሉን፡፡

ድካማቸው ከንቱ ቀርቷል፤ ተስፋ ያደረጉትም አልተገኘም “ ቀደም ብለው የበቀሉት ቡቃያዎችም ደርቀው ቀርተዋል፣ ምንም አይነት አረንጓዴ መሬት ሳናይ ነው የቀረነው፣ የዘንድሮው ከባድ ነው” ይላሉ የችግሩን አስከፊነት ሲገልጹት፡፡ የደረሰው ችግርና የሚያስከትለው ጦስ አስከፊ መኾኑንም ነግረውናል፡፡ ለልጆቻቸውና ለከብቶቻቸው የሚያጎርሱትም አጥተዋል፡፡

“ እንስሳት እየሞቱ ቁርበት ነው የሚመጣው፣ ስጋውም አይረባም፣ እየተገፈፈ ጫካ ይጣላል፤ ሰው ከብትና ፍየሎችን ይዞ ተሰዷል፤ በጣም አሳሳቢ ነው፣ የኑሮ ውድነቱም አስቸጋሪ ኾኗል፣ ነጋዴዎች እናመጣለን ቢሉም ሰላም አልኾነም እየተባለ አልመጣም፣ ሰው ሁሉ ለረሃብ አደጋ እየተጋለጠ ነው፤ እንጃ ዘንድሮን የሚያልፍ ሰው ያለ አይመስልም” ነው ያሉት የገጠመውን ችግርና ያንዣበበውን ፈተና ሲገልጹት፡፡ ከማሳቸው አንድም ፍሬ ሳያገኙ ማለፉ ከባድ ነውና፡፡ ገበሬ ሲኾን አምርቶ ለሰው ይተርፋል፣ ባይኾን ራሱን ይችላል፣ በእነርሱ ቀዬ ግን ይሄ አልኾነም፤ ወደ ጎተራቸው የሚያገቡት ምንም ምርት የላቸውምና፡፡

“ ምን ብዬ ልንገርህ ? በረሃውን ብታየው፣ ወንዙ ሁሉ እየደረቀ ነው፣ ምንጭ የነበሩት ሁሉ ደርቀው ሰው ሁሉ እየተሰደደ ነው፣ ሠርቶ የሚበለው ነገር ሁሉ ያጠረ ነው፡፡ ምን ብዬ እነግርሃለሁ” ነው ያሉን ከባዱን ችግር ሲነግሩን፡፡ የከበደውና ያንዣበበው ችግራቸውን ለመግለጽ ይቸግራቸዋል፡፡ ድርቅ ሲከሰት ማካካሻ ዘር እናገኝ ነበር ዘንድሮ ግን ምንም አላገኘንም፣ በተደጋጋሚ ጥያቄ እያቀረብን ነው ምላሽ ግን አላገኘንም ብለውናል፡፡

አሁን ላይ ድጋፍ እየተደረገላቸው አለመኾኑን የነገሩን መኮንን መንግሥት አስቸኳይ ድጋፍ እንዲደረግላቸውም ጠይቀዋል፡፡

የሰሃላ ሰየምት ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ እሸቱ ዘገየ በወረዳው ከፍተኛ የኾነ የዝናብ እጥረት ማጋጠሙን ገልጸዋል፡፡ የዝናብ እጥረቱ ከፍተኛ አደጋ መደቀኑንም ተናግረዋል፡፡ በወረዳው በዘር የተሸፈነው ማሳ ከጥቅም ውጭ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡ በወረዳው በሁሉም ቀበሌዎች ችግር መኖሩንም ተናግረዋል፤ ከ51 ሺህ በላይ የሚኾኑ የወረዳው ነዋሪዎች አስቸኳይ ድጋፍ እንደሚሹም ገልጸዋል፡፡

አስቸኳይ ድጋፍ ማድረግ ካልተቻለ በነዋሪዎች ላይ አስከፊ ጉዳት ሊደርስ እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡ ከሰዎች ባለፈ እንስሳትም ለከፋ ጉዳት መዳረጋቸውን ነው የገለጹት፡፡ የሰበዓዊ እርዳታ እንዲደረግ ጥያቄ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን የተናገሩት ምክትል ኀላፊው የደረሰ አስቸኳይ ድጋፍ አለመኖሩንም አስታውቀዋል፡፡

የዋግኸምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባባሪያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ምህረት መላኩ ዝናብ ዘግይቶ በመግባቱ፣ ጀምሮ በማቋረጡና ፈጥኖ በመውጣቱ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ችግር መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሰሃላ ሰየምት፣ ዝቋላ፣ ድሃና እና አበርገሌ ወረዳዎች የዝናብ እጥረት መከሰቱንም አስታውቀዋል፡፡ በሰሃላ ሰየምት ግን የከፋ ችግር ማጋጠሙን ነው የተናገሩት፡፡

በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በሁሉም ወረዳዎች የዝናብ ስርጭቱ አነስተኛ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡ ሰሃላ ሰየምት አስቸኳይ የሰበዓዊ ድጋፍና የእንስሳት መኖ እንደሚያስፈልገውም ተናግረዋል፡፡ የአደጋ ጊዜ እቅድ አቅርበው ምላሽ ለመስጠት እየሠሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ለመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና ለረጅ ድርጅቶች የዝናብ እጥረት የተከሰተባቸውን አካባቢዎች ማሳየታቸውንም ተናግረዋል፡፡ የክልሉ መንግሥትም ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቱን ገልጸዋል፡፡ በክልሉ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት የተፈቀደው ድጋፍ አለመድረሱንም ተናግረዋል፡፡

የሕጻናት አድን ድርጅት ድጋፍ ለማድረግ የተረጂ ልየታ እያደረገ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ በሰሃላ ሰየምት ወረዳ ሁሉም የወረዳው ነዋሪዎች ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ነው የተናገሩት፡፡ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከ123 ሺህ በላይ ወገኖች አስቸኳይ የሰበዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውም አስታውቀዋል፡፡

መንግሥት፣ ረጅ ድርጅቶች እና በጎ ፈቃደኛ ግለሰቦች ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በዝናብ እጥረት የተጎዱ ወገኖች በቀጣይ ዓመት አምርተው ራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ የሰው እጅ እንደሚጠብቁም ገልጸዋል፡፡

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዳይሬክተር ብርሃኑ ዘውዱ በአማራ ክልል ዋግኸምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር፣ ሰሜን፣ ደቡብ እና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች ላይ ቆላማ አካባዎች የዝናብ እጥረት መከሰቱን ገልጸዋል፡፡ በሰሜን ወሎ ዞንም ቆላማ አካባቢ እጥረት መኖሩንም ገልጸዋል፡፡ በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች ሊኖር እንደሚችልም አመላክተዋል፡፡

በዝናብ እጥረት ምክንያት እንስሳት ላይ ጉዳት መድረሱንም ተናግረዋል፡፡ የዝናብ እጥረት በገጠማቸው አካባቢዎች በአስቸኳይ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ወገኖች መኖራቸውንም አመላክተዋል፡፡ አስቸኳይ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች በቂ ባይኾንም ድጋፍ መላኩን ነው የተናገሩት፡፡ በክልሉ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት አንዳንድ ቦታዎች ላይ ድጋፉ አለመድረሱንም አስታውቀዋል፡፡

ረጅ ድርጅቶችን እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት ድጋፍ እንዲያደርጉ ምክክር ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡ የሰበዓዊ ድጋፍ የሚያደርጉ ዓለማቀፍ ተቋማት ተንቀሳቅሰው እንዲሠሩ መምከራቸውንም አመላክተዋል፡፡ በዋግኸምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በዝናብ እጥረት ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ ለማድረግ ቃል የገቡ መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡ በአማራ ክልል የተፈጠረውን ችግር ለፌደራል መንግሥት ማሳወቃቸውን እና የተወሰነ ድጋፍ መፈቀዱንም ገልጸዋል፡፡ ድጋፉን ተደራሽ ለማድረግ ግን የሰላምና የደኅንነት ጉዳይ አሳሳቢ መኾኑን ነው ያነሱት፡፡

በሁሉም አካባቢዎች ያለውን መረጃ ለመሰብሰብ ባለመቻሉ ድርቁ ሊሰፋም ሊጠብም የሚችልበት እድል እንዳለውም አመላክተዋል፡፡ በአማራ ክልል ተደራራቢ ችግሮች መኖራቸውን ያነሱት ዳይሬክተሩ በሰሜኑ ጦርነትና ከሌሎች ክልሎች ተፈናቅለው የሚመጡ ወገኖች ድጋፍ ሲደረግላቸው መቆየቱን ነው ያነሱት፡፡ የክልሉ ሕዝብ፣ ባለሀብቶች፣ ረጂ ድርጅቶች እና መንግሥት ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየተቻውንም ተናግረዋል፡፡ አሁንም በማኅበረሰቡ ውስጥ እየተደገፉ የሚኖሩ ወገኖች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡

መላው ኢትዮጵያውያን፣ ረጅ ድርጅቶች፣ መንግሥታዊ ያልኾኑ ወገኖች እና መንግሥት በድርቅ ምክንያት የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ቅርሶችን በዓለም ቅርስነት ማስመዝገብ ለሀገር መልካም ገጽታ ያላብሳል” የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን
Next articleከ1 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ለሆኑ ሰዎች የኮሌራ መከላከያ ክትባት ተሰጠ