“ቅርሶችን በዓለም ቅርስነት ማስመዝገብ ለሀገር መልካም ገጽታ ያላብሳል” የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን

56

ባሕርዳር፡ መስከረም 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ የበርካታ ታሪካዊ፣ ባሕልናዊ እና ሃይማኖታዊ መስህቦች መገኛ ሀገር ናት፡፡ ተፈጥሮ አሳምሮ የሰጣት ውብ ሥፍራዎቿ፣ ልጆቿ በየዘመናቸው የሠሯቿው ታሪካዊ ቦታዎቿ፣ ውብ ባሕሎቿ፣ የጸኑ እሴቶቿ ኢትዮጵያን ተወዳጅ ያደርጓታል፡፡ ባሏት ውብ መስህቦች በርካቶች ለማየት የሚጓጉላት ሀገር እንድትኾን አድርጓታል፡፡

ኢትዮጵያ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶቿን ለዘመናት ጠብቃ በዓለም ቅርስነት እያስመዘገበች ነው፡፡

በኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን የብሔራዊ ሙዚዬም ሥራ አስፈጻሚ አንዷለም ግርማይ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኒስኮ) የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን በማስመዝገብ በአፍሪካ ቀዳሚ መኾኗን ተናግረዋል፡፡ ዪኒስኮ ሦስት አይነት ቅርሶችን እንደሚመዘግብ ያነሱት ሥራ አስፈጻሚው ቋሚ ቅርሶችን፣ የማይዳሰሱ ቅርሶችን እና መዛግብትን እንደሚመዘግብ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ አሥራ አንድ ቋሚ እና አራት የማይዳሰሱ ቅርሶችን በድምሩ አሥራ አምስት ቅርሶችን በማስመዝገብ በአፍሪካ ቀዳሚ መኾኗን ነው ያነሱት፡፡ ቅርሶችን በዓለም አቀፍ ቅርስነት ማስመዝገብ ጥበቃቸው የጠበቀ እንዲኾን እንደሚያስችልም ተናግረዋል፡፡ ቅርሶቹ ዓለም አቀፍ ሲኾኑ ከሚያስገኙት ገቢ በተጨማሪ በጦርነት ጊዜ ቅርሶቹ እንዳይውድሙ ጥበቃ እንደሚደረግላቸውንም ገልጸዋል፡፡ የሠራውና የጠበቀው ማኅበረሰብም ዓለም አቀፍ እውቅና እንደሚያገኝ ነው የተናገሩት፡፡

ኢትዮጵያ በቅርሶቿ ምክንያት በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ዘንድ ታውቃለችም ነው ያሉት፡፡ ቅርሶቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲመዘገቡ ለሀገር መልካም ገጽታን በማላበስና በማስተዋወቅ ጎብኚዎች ወደ ሀገር እንዲመጡ እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡

ጎብኚዎች ወደ ሀገር ሲመጡ ለወጣቶች የሥራ እድል እንደሚፈጥሩም ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ ቅርሶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስመዝገቧ በጥንታዊነቷ፣ በታሪካዊነቷና በታሪክ ጠባቂነቷ እንድትታወቅ እንደሚያደርጋትም አስታውቀዋል፡፡ ኢትዮጵያን በአልተገባ መንገድ ሲረዷት የነበሩ ሁሉ መልካም ገጽታዋን እንዲያዩ እንደሚያደርጋቸውም አመላክተዋል፡፡

ቱሪዝም የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ እና የፖለቲካ ጥቅሞችን ይዞ እንደሚመጣም ገልጸዋል፡፡ ዪኒስኮ የሚመዘግባቸው የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች የራሳቸውን ታሪክ፣ ባሕልና እሴት በማይነካ መልኩ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ማኅበረሰቡ ባሕሉን እና እሴቱን በመጠበቅ የራሱ መገለጫ የኾኑ ቅርሶችን ለዓለም ማስተዋወቅ እንደሚገባውም አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ተጨማሪ ቅርሶችን በዪኒስኮ ለማስመዝገብ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ጥንታዊ ቅርሶች ተጠብቀው እንዲኖሩ እየሠሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየዓለም ቱሪዝም ሳምንትን በማስመልከት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በኮንታ ዞን የመስህብ ሥፍራዎች ጉብኝት ተካሄደ።
Next article“የተዘራው አልበቀለም፣ በማሳው ልምላሜ አልታየም”