የዓለም ቱሪዝም ሳምንትን በማስመልከት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በኮንታ ዞን የመስህብ ሥፍራዎች ጉብኝት ተካሄደ።

68

ባሕርዳር፡ መስከረም 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ የተመራው የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ቡድን በኮንታ ዞን የሚገኙ የቱሪስት መስህብ ሥፍራዎችን ጎብኝተዋል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ፤ ኮንታ በመንግሥት በቱሪዝም ልማት ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው ሥፍራዎች አንዱ መሆኑን ገልፀዋል።

ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ 4 ሺህ 100 ሄክታር የቆዳ ስፋት ያለው ሲሆን፤ በውስጡም ትልልቅ ወንዞች፣ ሐይቆችና ፏፏቴዎችን ያቀፈ መሆኑን ጠቁመዋል።

መንግሥት ይህን ኃብት ለማስተዋወቅ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየሰራ መሆኑን ገልፀው፤ በገበታ ለሀገር የአካባቢው ማኅበረሰብ ባሕላዊ ኃብቶች የሚተዋወቁበት ይሆናል ነው ያሉት።

በመንግሥትና በግል ባለሃብቶች እየተገነቡ ያሉ የመዝናኛ ሥፍራዎች ለቱሪዝም ዘርፍ እድገት ትልቅ ሚና እንደሚኖራቸው አንስተዋል።

በአጠቃላይ የአካባቢው ሁለንተናዊ ልማት የፍራፍሬና የቅመማቅመም ዕምቅ አቅምን ተጠቃሚ ለማድረግ ያስችላል ነው ያሉት።

የገበታ ለሀገር ኮይሻ ፕሮጀክት በተፈጥሮ ውበት የቸረውን መልክዓ-ምድር በጥቂት ኢንቨስትመንት ወደ ጥቅም መለወጥ እንደሚቻል የሚያሳይና ሌሎችም በዘርፉ ኢንቨስትመንት እንዲነሳሱ የሚያደርግ መሆኑን ገልፀዋል።

ጨበራ ጩርጩራ በተፈጥሮ ሕብር የሚታይበትና የቱሪስት ቆይታ የሚያራዝም መሆኑን ጠቁመዋል።

የኮንታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ነጋ አበራ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ዞኑ በርካታ ሐይቆች፣ ፏፏቴዎችና ጥብቅ ደኖች ባለቤት ነው።

ያም ብቻ ሳይሆን በዕፅዋት ብዝኃ-ሕይወት እንዲሁም የተለያዩ የዱር እንስሳት የያዘውን የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ለአብነት ጠቅሰዋል።

አካባቢው የውሃ ሃብቶች ያሉበት ለአብነት የኮይሻ ኃይል ማመንጫ እንደሚገኝበትም ነው የተናገሩት።

ከለውጡ ወዲህ የቀድሞው የኮንታ ልዩ ወረዳ ወደ ዞንነት ከማደጉ ባሻገር፣ በተለይም በቱሪዝም ዘርፍ ተጠቃሚነትን የሚጨምሩ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነው የኮይሻ ፕሮጀክትም መምጣት ለዞኑ ዕምቅ የቱሪስት ፍሰት መጨመር ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ከገበታ ለሀገር ኮይሻ ፕሮጀክት በተጨማሪ የቱሪስት መዳረሻና ማረፊያ ቦታዎቹ እየተገነቡ ነው ብለዋል።

ይህም የኅብረተሰብን ባሕላዊ እሴት ለማስተዋወቅና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያጎለበተ መሆኑን ነው ያነሱት።

የመንገድና መሰል መሠረተ-ልማቶች የአካባቢው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያመጣ ስለመሆኑም እንዲሁ።

የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና ቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት አሁንም ውስንነት እንዳሉ ተናግረዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየደም እጥረት በማጋጠሙ ዜጎች ደም እንዲለግሱ የኢትዮጵያ ደምና ኅብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ጥሪ ቀረበ።
Next article“ቅርሶችን በዓለም ቅርስነት ማስመዝገብ ለሀገር መልካም ገጽታ ያላብሳል” የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን