‹‹ፍትህ ለታገቱ ተማሪዎች፡፡›› የዋሽንግተን ዲሲ ሠላማዊ ሰልፈኞች

198

ባሕር ዳር፡- ጥር 20/2012ዓ.ም (አብመድ) በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ የተፈጸመውን እገታ እና የመንግሥትን ዝምታ በማውገዝ በዋሽንግተን ዲሲ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዷል፡፡

መንግሥት የታገቱ የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን እንዲያስለቅቅ እና የህግ የበላይነትንም እንዲያስከብር የሚጠይቅ ሠላማዊ ሰልፍ ትናንት በዋሽንግተን ዲሲ ተካኪዷል፡፡ የታገቱ ተማሪዎች እና ቤተሰቦቻቸው ፍትህ እንዲያገኙም ነው የጠየቁት፡፡

ሰላማዊ ሰልፈኞቹ የታገቱ ተማሪዎች ስላሉበት ሁኔታ ግልጽ መረጃ እንዲሰጥ፣ በሀገሪቱ የህግ ጥሰት የፈጸሙ አካላትም ተጠያቂ እንዲሆኑ ጠይቀዋል፡፡ ዘር ተኮር ፖለቲካ በህግ እንዲታገድም ነው ሰላማዊ ሰልፈኞች የጠየቁት፡፡ ጥያቄያቸውንም በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በመገኘት ካሰሙ በኋላ በተወካዮቻቸው አማካኝነት ለአምባሳደር ፍጹም አረጋ አቅርበዋል፡፡

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ በበኩላቸው ጥያቄውን ለመንግስት በማቅረብ ምላሹን ተከታትለው እንደሚያሳውቁ በማኅበራዊ የመረጃ ገጻቸው ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያውያኑ ዲያስፖራዎች ባለፉት የጭቆና ዓመታት ከሕዝባቸው ጎን በመቆም ለውጥ እንዲመጣ ብዙ ደክመዋል፡፡

ለውጥ ሲመጣም ከተጀመረው ለውጥ ጎን በመቆም አጋርነታቸውን ገልጸዋል፤ አብረው ለመስራት እና ሀገራቸውን ለማበልጸግ የአንድነት ድምጻቸውንም አሰምተዋል፡፡ በለውጥ ሂደቱ ላይም በሚታዩ ችግሮች ላይም ማስተካከያ አንዲሰጥ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው በተለያየ አጋጣሚ ሲጠይቁም ይስተዋላል፡፡

ትናንት በሠላማዊ ሰልፎቹ የተስተጋቡ ድምጾችም ዋነኛ ትኩረታቸው የታገቱ ተማሪዎች እንዲለቀቁ መጠየቅ ሆኖ በሀገሪቱ የሚስተዋሉ የህግ ጥሰቶች እና የተጠያቂነት አለመስፈን እንዲስተካከሉ፣ የዜጎች ሥቃይና መፈናቀል እንዲቆም የሚሉ ነጥቦች ላይ ነበር፡፡

በምስጋናው ብርሃኔ

Previous article“ሰቆጣ ሚሲግ” ለብሔራዊ ሊግ የተስፋ ጉዞ መደላድሎች ተፈጥረውለታል፡፡
Next articleበ11ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ የሸገር ደርቢ ይጠበቃል፡፡