የደም እጥረት በማጋጠሙ ዜጎች ደም እንዲለግሱ የኢትዮጵያ ደምና ኅብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ጥሪ ቀረበ።

52

👉በበጀት ዓመቱ 427 ሺህ 526 ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዷል

ባሕርዳር፡ መስከረም 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሕክምና የሚውል የደም እጥረት በማጋጠሙ ማኅበረሰቡ ደም እንዲለግስ የኢትዮጵያ ደምና ኅብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ጥሪ አቀረበ፡፡ በ2016 በበጀት ዓመት 427 ሺህ 526 ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዷል።

የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ታዬ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከመስከረም ወር 2016 ዓ.ም ጀምሮ የደም እጥረት በማጋጠሙ አቅሙ ያላቸው ዜጎች ደም በመለገስ ክቡር የሆነውን የሰው ሕይወት ሊታደጉ ይገባል፡፡

እንደ አቶ ሀብታሙ ገለጻ፤ በሀገሪቱ የሚከበሩ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ በዓላት መደራረብ፣ ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ አለመከፈት እንዲሁም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ስጋት ለእጥረቱ መከሰት ምክንያቶች ናቸው።

ደም የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ከመሆኑም በተጨማሪ ወደሕክምና ተቋማት የሚገባው የደም መጠን መቀነሱ በሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑን አቶ ሀብታሙ አስረድተዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲታይ በ2015 ዓ.ም የክረምት ወራት ላይ የነበረው የደም ክምችት ከባለፉት የክረምት ወራት የተሻለ መሆኑን አንስተው፤ መስከረም ወር ከገባ በኋላ የታየው መቀዛቀዝ እጥረቱን እንደፈጠረ አመላክተዋል፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የደም ልገሳ ክለቦችን በማጠናከር የደም እጥረቱን ለመቅረፍ እንደሚሠራ ገልጸው፤ በአዲስ አበባ በሥራ ላይ የሚገኙ 37 የደም ልገሳ ክለቦች የራሳቸው ዕቅድ ኑሯቸው በሚፈለገው ደረጃ ደም እንዲለግሱ የማድረግና ሌሎች ተመሳሳይ ክለቦችን የመጨመር ሥራ እንደሚከናወን አስረድተዋል፡፡

ደም የማሰባሰብ ሥራው ላይ ጉድለት የሚታይባቸውን አካባቢዎች በመለየት ድጋፍ የማድረግ ሥራ ይከናወናል ያሉት አቶ ሀብታሙ፤ የባለሙያዎች ቡድን ወደተለያዩ አካባቢዎች በመላክ ሥልጠና በመስጠት፣ ድጋፍና ክትትል በማድረግ የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖራቸው ይደረጋል ብለዋል፡፡

በትግራይ ክልል የአክሱምና መቀሌ ደም ባንኮች የአካባቢያቸውን የደም ፍላጎት በራሳቸው አቅም እየሸፈኑ እንደሆነም አቶ ሀብታሙ ጠቁመዋል።

በ2016 በበጀት ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ 427 ሺህ 526 ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ፤ በሁለት ወራት ውስጥ 55 ሺህ ዩኒት ደም መሰብሰብ መቻሉንም አስታውቀዋል፡፡

አንድ ሰው 450 ሚሊ ሊትር ደም ሲለግስ የሦስት ሰው ሕይወት ማዳን እንደሚችል ማኅበረሰቡ ሊረዳ ይገባል ያሉት አቶ ሀብታሙ፤ በየሕክምና ተቋማቱ የደም ሕክምና ለሚፈልጉ ታካሚዎች የሚተካውን ደም በመስጠት የማይተካውን ሕይወት ማዳን እንደሚቻል በመረዳት ሁሉም ማኅበረሰብ በበጎ ፈቃደኝነት ደም ሊለግስ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የተፈጠረውን የደም እጥረት ለመቅረፍ በትምህርት ቤቶች፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማትና በተለያዩ ከተሞች በሚዘጋጁ ጊዜያዊ የደም መሰብሰቢያ ማዕከላት ላይ ኅብረተበሱ ደም እንዲለግስም ጥረት ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል።

ከጥቅምት ወር የመጀመሪያ ሳምንት ጀምሮም በትምህርት ቤቶች በተደራጀ ሁኔታ ደም ለማሰባሰብ የሚረዱ ሥራዎች እንደሚከናወኑም አስታውቀዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ውሻን በወቅቱ በማስከተብ ውሻን የሚያሳብድ በሽታን መከላከል ይገባል” የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
Next articleየዓለም ቱሪዝም ሳምንትን በማስመልከት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በኮንታ ዞን የመስህብ ሥፍራዎች ጉብኝት ተካሄደ።