
ባሕር ዳር: መስከረም 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ውሻን የሚያሳብድ በሽታ ራቢስ በተባለ ቫይረስ የሚመጣ ገዳይ በሽታ ነው። በሽታው የሚከሰተው በቫይረሱ በተጠቃ ውሻ ንክሻ እና ከውሾች አፍ በሚወጣ ምራቅ መሰል ፈሳሽ ንክኪ አማካኝነት ነው።
በአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ ሰጭ ባለሙያ አቶ ኃይሉ አያሌው ውሻን የሚያሳብድ በሽታ በየትኛውም ጊዜ ሊከሰት የሚችል የኅብረተሰብ ጤና ስጋት ነው ብለዋል። በሽታው በተለይም ከነሐሴ አጋማሽ እስከ መስከረም መጨረሻ ድረስ በስፉት እንደሚከሰት ጠቁመዋል።
በወቅቱ የማይከተቡ እና ቁጥጥር የማይደረግባቸው ውሾች ለኅብረተሰብ ጤና ስጋት መኾናቸውን ባለሙያው ተናግረዋል። ውሻን የሚያሳብድ በሽታ ዋነኛ መከላከያ መንገድ “ውሻን በወቅቱ ማስከተብ እና ቤት ውስጥ አስሮ መቆጣጠር” መኾኑንም ባለሙያው ተናግረዋል።
የውሻ ክትባት አገልግሎት በሁሉም አካባቢዎች በቀላሉ እና በዝቅተኛ ዋጋ የሚገኝ ስለመኾኑም ባለሙያው ጠቁመዋል። አቶ ኃይሉ ማኅበረሰቡ ያለንበት የመስከረም ወር በሽታው በስፋት የሚከሰትበት ወቅት መኾኑ በማወቅ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግም መክረዋል።
በማንኛውም ኹኔታ የውሻ ንክሻ ከተከሰተ ወደ ጤና ተቋማት እስከሚደርሱም የተነከሰውን ቦታ በሳሙና በደንብ ማጠብ እና በፋሻ ወይም በንጹህ ጨርቅ ማሰር እንደሚገባ መክረዋል። ወደ ጤና ተቋማት ፈጥኖ በመሄድ ተገቢውን ሕክምና ማግኘት እንደሚገባም ባለሙያው ይመክራሉ።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!