
ባሕርዳር፡ መስከረም 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የደረሰ የሰሊጥ ሰብል የመሰብሰብ ሥራ መጀመሩን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ አግደው ሞላ እንደገለጹት፤ በክልሉ በ2015/16 ዓ.ም የምርት ዘመን ግማሽ ሚሊዮን ሄክታር የሚጠጋ መሬት በሰሊጥ ለምቷል።
በምርት ዘመኑ በሰሊጥ ለማልማት ታቅዶ ከነበረው ከ349 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ማከናወን መቻሉንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
በክልሉ መኸር እርሻ የለማው ይኸው የሰሊጥ ምርት ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ሲሆን፤ ጥራቱን ጠብቆ እየተሰበሰበ ነው ብለዋል።
እየተሰበሰበ ያለው ምርት ቀድመው በተዘሩ ሰሊጥ አምራች አካባቢዎች የደረሰ 125 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ መሆኑን አስረድተዋል።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ በእስካሁኑ ሂደት ቀድሞ የደረሰ ከ5 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ያለ የሰሊጥ ሰብል መታጨዱን ተናግረዋል።
ምርቱን ከብክነት በፀዳና ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ተሰብስቦ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በየደረጃው ባሉ የግብርና ባለሙያዎች ለአምራቾች የቅርብ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በመኽር ወቅቱ ለምቶ እየተሰበሰበ ካለው ሰሊጥም ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።
የሰሊጥ ምርት የገበያ ዋጋ እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞም በሰሊጥ ሰብል የለማው መሬት ከቀዳሚው ዓመት በ149 ሺህ ሄክታር ብልጫ እንዳለው አስታውቀዋል።
የጉልበት ሠራተኞችም እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ሰሊጥ አብቃይ ወደሆኑ አካባቢዎች በስፋት ገብተው ምርቱን እንዲሰበስቡም ጥሪ አቅርበዋል።
የሰሊጥ ሰብሉ በዋናነት በምዕራብ፣ ማዕከላዊና ሰሜን ጎንደር ዞኖች እንዲሁም በአዊ ብሔረሰብ አስሥተዳደር የለማ መሆኑ ተመላክቷል።
በምዕራብ ጎንደር ዞን የምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ አርሶ አደር ብርሃኑ ሞገስ በሰጡት አስተያየት፤ በሰሊጥ ሰብል ካለሙት 3 ሄክታር መሬት ቀድሞ የደረሰውን እያጨዱ መሆኑን ተናግረዋል።
ዘንድሮ የሰሊጥ ሰብሉ ምርት አያያዝ ከባለፈው የተሻለ ሆኖ በመገኘቱ ከ10 ኩንታል በላይ ምርት አገኛለሁ ብለው እንደሚጠብቁም ገልጸዋል።
ከሶስት ሄክታር በሚበልጥ መሬት ያለሙትን የሰሊጥ ምርት እየሰበሰቡ መሆናቸውን የገለጹት ሌላው አርሶ አደር ታደሰ አይናለም ናቸው።
ኢዜአ እንደዘገበው ዘንድሮ ሰብሉ በተሻለ ቁመና ላይ በመገኘቱ እስከ 14 ኩንታል ምርት በማግኘት ተጠቃሚ እሆናለሁ ብዬ አስባለሁ ብለዋል።
በአማራ ክልል ባለፈው ዓመት በሰሊጥ ሰብል ከለማው ከ347 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለምቶ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱን ከግብርና ቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!