
ባሕር ዳር፡- ጥር 20/2012ዓ.ም (አብመድ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳድር ከ10 ዓመታት በፊት የተመሠረተው “ሰቆጣ ሚሲግ” የእግርኳስ ክለብ ባለፉት ዓመታት ከውጤት ርቆ ነበር፡፡
ቡድኑ በሥራ ዕድል አማራጭነት ምክንያት ከየወረዳው ተጫዋቾችን በየዓመቱ መሰብሰቡ፣ ተጨማሪ ገቢዎች ባለመኖራቸው ተጫዋቾችን አለማስፈረም እና ጠንካራ ኮሚቴ አለመኖር በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡ በ2012 ዓ.ም ግን ጠንካራ ኮሚቴዎች እንደገና ተቋቁመው የክለቡን ገቢ ማሳደጋቸውን የክለቡ ዋና አሰልጣኝ አቶ ልዑል ሰገድ ይማም ተናግረዋል፡፡ አቶ ልዑል ሰገድ የእግር ኳስ ክለቡ ጠንካራ ተጫዋቾችን ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች መልምሎ በማስፈረሙ ጥሩ ቡድን መመሥረት መቻሉን ገልጸዋል፡፡ ለተጫዋቾቹ ማረፊያ እና መመገቢያ ‹‹ካምፕ›› መገኘቱም የተጫዋቾችን ቡድናዊ ስሜት ከፍ አድርጎታል ብለዋል፡፡ የተሻለ ትጥቅና መለያ እንዲኖር ኮሚቴው ያደረገው ጥረት የሚያስመሰግን እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡
በምስራቅ አማራ ካሉ ስምንት ቡድኖች ሥር የተመደበው ሰቆጣ ሚሲግ ባለፉት ጊዚያት ባደረገው ጨዋታ በደብረታቦር 2ለ1 ሲሸነፍ ወልዲያ ‹‹ቢ ቡድንን›› አምስት ለዜሮ አሸንፏል፡፡ ተጫዋቾቹ ባሳዩት አጨዋወት መደሰታቸውን የገለፁት አሰልጣኙ ለተጫዋቾች የተሻለ ክፍያ መከፈሉ ለቡድኑ ውጤት ከፍተኛ እገዛ አድርጓል ብለዋል፡፡ ክለቡ ብሔራዊ ሊግ ለመግባት ብዙ መደላድሎች በኮሚቴው በመፈጠሩ እቅዱን ለማሳካት እየሠሩ መሆናቸውን ገልጸው ወልዲያ ቢ ላይ ያሳዩትን ከፍተኛ የጨዋታ ብልጫና ግብ ሌሎች ላይም ለመድገም አቅም እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
ሚሲግ ሰቆጣ ሲቋቋም በወረዳዎች ድጋፍ በመሆኑ ወረዳዎች እስከ አሁን ገንዘቡን ገቢ አለማድረጋቸው እንቅፋት እንደሆነባቸው የተናገሩት አሰልጣኙ ኮሚቴው ከተለያዩ ድርጅቶች ባገኘው ገቢ እስከ አሁን መቆየት እንደቻለ ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ ግን ከበጀት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ጥያቄ መሆን ስለሌለባቸው የውስጥ ገቢዎችን ማሳደግ ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡
የክለቡ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሙሉጌታ ንጋቴ ለክለቡ ውጤታማነት ኮሚቴው 755 ሺህ ብር ከዳሽን ቢራ ፋብሪካ በማግኘቱ የተሻሉ ተጫዋቾች እንዲፈርሙ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ የእራሳቸው ‹‹ካምፕ›› እንዲኖርና የተሻለ ደሞዝ እንዲከፈላቸው በመደረጉ ለውጤታማነቱ እገዛ እንዳደረገ ገለጸዋል፡፡ የውስጥ ገቢ ለማሰባሰብ የደጋፊዎች ማኅበርን በቅርብ ጊዜ በማቋቋም፣ ስታዲየሙን በማሳጠር እና መለያ በማሳተም ገቢ ለመሰብሰብ እቅድ ይዘው እየሠሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
የብሔረሰብ አስተዳደሩ ስፖርት መምሪያ ኃላፊ እና የክለቡ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሙሉቀን ሞላ ወረዳዎቹ ለክለቡ የሚያደርጉትን እገዛ እስከ የካቲት ወር ድረስ እንዲያስገቡ መነጋገራቸውን ለአብመድ ተናግረዋል፡፡ ለዘላቂ መፍትሔም በየዓመቱ የወረዳዎች ገንዘብ ሲላክ የክለቡን ድርሻ ቆርጦ ለማስቀረት ቦርዱ መወሰኑን ገልጸዋል፡፡
‹‹የሚሲግ ሰቆጣ›› አምበል ሙላት ደባሽ ከፍተኛ የአጨዋወት መሻሻል እንዳለ ከዚህ በፊት በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች መታየቱን ተናግሯል፡፡ ከሌሎች የአማራ ሊግ ክለቦች አንፃር ሲታይ ብሔራዊ ሊግ ለመግባት ሚሲግ የበለጠ አቅም እንዳለው በማመን ለተሻለ ውጤት እየሠሩ እንደሆነም ነው የተናገረው፡፡ ከሁለት ወራት በላይ በተሠራ ልምምድ ቡድኑ ከፍተኛ መናበብ እና ቡድናዊ ስሜት ያለው እንደሆነም የቡድኑ አምበሉ ተናግሯ፡፡ ቡድኑን ከተቀላቀሉ አዲስ ተጫዋቾች መካከል ዩሐንስ ጌትነት ጥሩ ልምምድ እና መናበብ በመኖሩ ብሔራዊ ሊግ የመግባት አቅማቸው ከፍተኛ እንደሆነ ገልጧል፡፡
ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ