“በበጀት ዓመቱ ለ1 ሚሊዮን 232 ሺህ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር እየተሠራ ነው” የአማራ ክልል ሥራና ሥልጠና ቢሮ

46

ባሕር ዳር: መስከረም 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት ለ1 ሚሊዮን 232 ሺህ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር እየሠራ መኾኑን የክልሉ ሥራና ሥልጠና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አወቀ ዘመነ ተናግረዋል።

የሥራ እድል ከሚፈጠርላቸው ዜጎች ውስጥ 50 በመቶው ሴቶች ናቸው ተብሏል። ከአጠቃላይ ቁጥሩ ውስጥ 80 በመቶ የሚኾኑት ወጣቶች እንደሚኾኑም አቶ አወቀ ገልጸዋል።

የሥራ እድል ተጠቃሚ ከሚኾኑት ዜጎች ውስጥ:-

👉 150 ሺህ የሚኾኑት የኮሌጅና የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን
👉 13 ሺህ ከስደት ተመላሾች እና
👉 2 ሺህ 160 አካል ጉዳተኞች ይገኙበታል።

ግብርና፣ ኢንዱስትሪ እና የአገልግሎት ደግሞ ለሥራ እድል መፍጠሪያ ትኩረት የተሰጣቸው ዘርፎች ናቸው። 2 ሺህ 600 ሼዶች ለመገንባት መታቀዱንም ምክትል ቢሮ ኀላፊው ተናግረዋል። ለዚህም 25 ሺህ ሄክታር የመሬት አቅርቦት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በበጀት ዓመቱ፦

👉 5 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር የገበያ ትስስር ለመፍጠር፣
👉 4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ብድር ለማሰራጨት ፣
👉 ለ50 ሺህ ዜጎች ደግሞ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ለመስጠት በትኩረት እየተሠራ ስለመኾኑ አቶ አወቀ ተናግረዋል።

የሚገነቡ ሸዶችን የመሰረተ ልማት ችግር ማሟላት አንዱ የትኩረት አካል መኾኑንም አንስተዋል።

ከሥራ እድል ፈጠራ እና ከብድር አቅርቦት ጋር ተያይዞ ከዚህ በፊት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ መመሪያዎች መውጣታቸውንም ገልጸዋል።

አት አወቀ የወጣቶችን የኢኮኖሚ ችግር ለመፍታት የክልሉን ሰላም ወደ ነበረበት መመለስ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። ለዚህ ደግሞ ወጣቶች አጋዥ ሊኾኑ እንደሚገባ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የአማራ ክልል ሥራና ሥልጠና ቢሮ ባለፈው 2015 በጀት ዓመት ከ1 ሚሊዮን 200 ሺህ በላይ ዜጎችን የሥራ እድል ተጠቃሚ ማድረጉን አስታውሷል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል የተፈጠረውን የጸጥታ አለመረጋጋት ተከትሎ የግሪሳ ወፍ ወረራን ለመከላከል የአውሮፕላን ርጭት ማከናወን እንዳልተቻለ ግብርና ቢሮ ገለጸ።
Next articleዜና ሹመት!