በአማራ ክልል የተፈጠረውን የጸጥታ አለመረጋጋት ተከትሎ የግሪሳ ወፍ ወረራን ለመከላከል የአውሮፕላን ርጭት ማከናወን እንዳልተቻለ ግብርና ቢሮ ገለጸ።

109

ባሕር ዳር: መስከረም 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሰብልን በከፍተኛ ደረጃ የሚያወድም የግሪሳ ወፍ መንጋ በምሥራቅ አማራ መከሰቱ ይታወሳል። ይህንን አውዳሚ ወፍ በባሕላዊ መንገድ ለመከላከል አርሶ አደሮች የራሳቸውን ጥረት ሲያደረጉ ቆይተዋል።

በክልሉ የተከሰተውን ግሪሳ ወፍ ለመከላከል በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል ርጭት እየተደረገ ስለመኾኑም በተለያዩ ሚዲያዎች ሲነገር ቆይቷል። ይሁን እንጅ እስካሁን ድረስ ከባሕላዊ የመከላከል ዘዴ ውጭ ምንም አይነት የአውሮፕላን ርጭት እንዳልተጀመረ በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አግደው ሞላ ነግረውናል።

በአውሮፕላን የታገዘ ርጭት ለማድረግ ኬሚካል የማጓጓዝ ሥራ ቢከናወንም የተዘጋጀው አውሮፕላን ወደ ቦታው ደርሶ ተግባራዊ ሥራ እንዳልተከናወነ ነው የተናገሩት። የዚህ ምክንያት ደግሞ የአውሮፕላኑ ባለቤቶች ግሪሳ ወፉ የተከሰተባቸው አካባቢዎች የሰላም ሁኔታ አስተማማኝ ስለመኾኑ የማረጋገጫ ደብዳቤ በመፈለጋቸው ነው ብለዋል ዳይሬክተሩ።

አቶ አግደው የግሪሳ ወፍ መንጋው በአማራ ክልል ውስጥ በአራት ዞኖች ላይ ተከስቶ በሰብል ላይ ጉዳት እያደረሰ ስለመኾኑ ገልጸዋል። በሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ፣ ሸዋ ሮቢት፣ በረኸት እና አንጾኪያ የተባሉ አራት ወረዳወች ላይ ተከስቷል። ከሰሜን ወሎ ዞን ደግሞ ጉባላፍቶ ወረዳ ላይ ደርሷል። በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደርም ደዋ ጨፋ እና ጅሌ ጥሙጋ የተባሉ ወረዳወች ጉዳቱ እየደረሰባቸው ነው።

በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ ላይም ግሪሳ ወፉ ተከስቷል።

የአካባቢዎች ሰላም መረጋገጥ አውሮፕላኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ቦታው ዘልቆ ርጭት እንዲያደርግ እና የሚደርሰውን ጉዳት መቀነስ እንዲቻልም ያደርጋል ሲሉ ሃሳባቸውን ሰጠዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

Previous article“ከሦስት ሚሊየን በላይ ዜጎች ብሔራዊ መታወቂያ ለማግኘት ተመዝግበዋል” የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጽሕፈት ቤት
Next article“በበጀት ዓመቱ ለ1 ሚሊዮን 232 ሺህ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር እየተሠራ ነው” የአማራ ክልል ሥራና ሥልጠና ቢሮ