ባሕር ዳር፡- ጥር 20/2012ዓ.ም (አብመድ) የትያትር ትምህርት ክፍል ለመክፈት በዝግጅት ላይ መሆኑን ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ከአስር በማያንሱ ዩኒቨርሲቲዎች የትያትር ትምህርት ክፍልን በመክፈት የኪነጥበብ እድገትን ለማጎልበት እየተሰራ ይገኛል፡፡ አማራ ክልል የበርካታ ትውፊቶች እና የጥበብ መፍለቂያ ቢሆንም በዋና ከተማው ባሕር ዳር እስካሁን በዘመናዊ መንገድ የተደራጀ የትያትር ማሰልጠኛና የትምህርት መስጫ ማእከል አለመኖሩ ጥያቄ ሲያስነሳ ቆይቶል፡፡
በተለይም ቀደምት የሆነው ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከተማዋ ላይ ቢገኝም እንደ ትያትር፣ ሙዚቃ፣ ስእል፣ ቅርጻቅርጽ እና የሲኒማ ትምህርትን የሚሰጥ የትምህርት ክፍል አለመክፈቱ የክልሉ እና የከተማዋ ትወፊቶች እንዲበለጽጉ እገዛ አላደረገም፡፡ አሁን ላይ ግን ዩኒቨርሲቲው ጉዳዩን አጥንቶ የትያትርና ሲኒማ ትምህርትን በማዋሀድ ለመጀመር በሂደት ላይ መሆኑን ገልጧል፡፡
በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ስነ-ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህር ስንታየሁ ገብሩ እንደገለጹት የትያትር ትምህርት ክፍሉን ለመክፈት አስፈላጊ ግብአቶችን በማጥናትና ትምህርቱን እየሰጡ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ልምድ በመውሰድ የስርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ውይይት ተደርጎበት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ይገኛሉ፡፡
ትምህርት ክፍሉ ለጊዜው ከጋዜጠኝነትና ሥነ ተግባቦት ትምህርት ክፍል ጋር በመተጋገዝ ሥራ እንደሚጀምር፣ ትምህርት ክፍሉም ኃላፊነቱን ወስዶ እየሠራ መሆኑን ነው መምህሩ ያስታወቁት፡፡ በቀጣይ የሙዚቃ እንዲሁም የስዕልና ቅርጻቅርጽ ትምህርት ክፍሎችን በመጨመር እራሱን ወደቻለ ትምህርት ቤት ለማድረግ እንደታሰበም ታውቋል፡፡
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ክፍሉን ለመክፈት ቀደም ብሎ የጀመረ ቢሆንም በተለያዩ ችግሮችና ለዘርፉ በሚሰጠው ትኩረት ማነስ መዘግየቱን የተናገሩት መምህር ስንታየሁ በ2013 የትምህርት ዘመን ተማሪወችን ተቀብሎ እንደሚስተምርም ነው የገለጹት፡፡
ዘጋቢ፡- አበባው እማኛው
