“በደብረ ብርሃን ከተማ በ721 ሚሊዮን ብር ወጪ የልማት ፕሮጀክቶች ይከናወናሉ” የአሥተዳደሩ ከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ

48

ባሕር ዳር: መስከረም 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር በበጀት ዓመቱ በ721 ሚሊዮን ብር ወጪ 87 የልማት ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ታቅዶ ወደተግባር መገባቱን የአሥተዳደሩ ከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ አስታውቋል። የመምሪያው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ነብዩ ባዩ እንደገለጹት የሚከናወኑት የልማት ፕሮጀክቶች የሕዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችሉ ናቸው። በተጨማሪም የልማት ሥራዎቹ በከተማዋ እየተስፋፋ የመጣውን የኢንዱስትሪ እድገት ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ አይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ጠቁመዋል።

ከሚከናወኑ የልማት ሥራዎች መካከል የ15 ኪሎ ሜትር ጌጠኛ ድንጋይ መንገድ ንጣፍ፣ 15 ኪሎ ሜትር አዲስ የጠጠር መንገድ ግንባታ፣ የስድስት ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ጥገና እንዲሁም 15 ኪሎ ሜትር የመንገድ ዳር የተፋሰስ ልማት ሥራ ይገኙበታል ብለዋል። በተጨማሪም ሌሎች የልማት ሥራዎች እንደሚከናወኑ የገለጹት አቶ ነብዩ፤ የሚገነቡ ፕሮጀክቶች ኅብረተሰቡን በማወያየት የተመረጡ መኾናቸውን ገልጸዋል። አቶ ነብዩ እንዳሉት ፕሮጀክቶቹ 5 ሺህ ለሚኾኑ ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር የሚያስችሉ ናቸው። ባለፉት ሁለት ዓመታት ግንባታቸው ተጀምሮ ያልተጠናቀቁ የልማት ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራም አስታውቀዋል።

የልማት ሥራዎቹ የሚከናወኑት ከክልሉ መንግሥትና ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ነው፤ ኅብረተሰቡም በገንዘብ፣ በጉልበት እና የግንባታ ቁሳቁስ በማቅረብ የበኩሉን እንዲወጣ ይደረጋል ብለዋል። በደብረ ብርሀን ከተማ ጠባሴ ክፍለ ከተማ የሚኖሩት መላዕከ ሰላም አባ ሀብተጊዮርጊስ ወልደገብረኤል ለአካባቢው ልማት መፋጠን የሕዝብ ተሳትፎ ወሳኝ መኾኑን ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት በክፍለ ከተማው ኅብረተሰቡ ባደረገው የጉልበት፣ የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ ሦስት ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱን አስታውሰዋል። በተጨማሪም የሦስት ኪሎ ሜትር የመንገድ ዳር መብራት ለመዘርጋት መቻሉን ጠቅሰው፣ በተያዘው ዓመትም በሕዝብ ተሳትፎ መሰል የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።

በከተማው የሚስተዋሉ የልማት ሥራዎች በመንግሥት ወጪ ብቻ የሚከናወኑ አለመኾናቸው የገለጹት ደግሞ አቶ ታምሩ ታደለ የተባሉ ነዋሪ ናቸው። በዚህ ዓመት በከተማው ለሚከናወኑ የልማት ሥራዎች የአቅማቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ጠቅሰው፤ ቀደም ሲል ለተገነቡ መሰረተ ልማቶች ተገቢውን ጥበቃ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ኢዜአ እንደዘገበው ከተማ አሥተዳደሩ ባለፈው ዓመት 362 ሚሊዮን ብር በመመደብ 47 የልማት ፕሮጀክቶችን ማከናወን እንደቻለም ታውቋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጊዮርጊስ በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የመልስ ጨዋታውን ዛሬ በካይሮ ያደርጋል
Next article“የኤሌክትሪክ ኃይል ብክነትን ለማስቀረት ተቋማትና ኅብረተሰቡ የድርሻቸውን አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይገባል” የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን