
ባሕርዳር፡ መስከረም 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የመስቀል በዓል በሀገራችን ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ እና ብሔራዊ በዓላት መካከል አንዱ ነው። በዓሉ በተለየ ባሕላዊ ጭፈራ ታጅቦ በድምቀት ከሚከበርባቸው አካባቢዎች መካከል በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጃዊ ወረዳ አንዱ ነው።
የመስቀል በዓል ለረጅም ዓመታት ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ትውፊቱን ጠብቆ ሲከበር እንደዘለቀ የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ የወረዳዋ ነዋሪ የሆኑት አቶ ንጋቱ ዋሴ እንደሚሉት መስቀል በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ክብረ በዓል ነው። ማኅበረሰቡ በየአካባቢው አማካይ በኾነ ቦታ ላይ በጋራ ተሰባስቦ ያከብራል። በዓሉን በደመቀ ሁኔታ ለማክበርም አንድ ደመራ ተካይ ከማኅበረሰቡ መካከል ይመረጣል።
የሚመረጠው ደመራ ተካይ በሥነ ምግባሩ የተመሰገነ፣ አስተዋይ፣ ደግ፣ ሩህሩህ እና ይቅር ባይ የኾነ እና ለደመራ ተካዮች የሚያስፈልገውን ድግስ የማዘጋጀ አቅም ሊኖረው ይገባል ይላሉ። ደመራ ተካዩ ከአካባቢው ካለቀቀ፣ የጤና እክል ካላጋጠመው ወይም ደግሞ በፍላጎት በቃኝ ካላለ በስተቀር በሌላ አይተካም።
የመስቀል ክብረ በዓል ቀናት ሲቀሩት ደግሞ የአካባቢው ወጣቶች እንጨት ሰብስበው በየቤታቸው ያስቀምጣሉ፡፡ መስከረም 16 ቀንም በየቤቱ አባወራው የደመራውን ችቦ ያሥራል። የደመራ ተከላ ሰዓቱ ሲደርስም በአካባቢው የተመረጠው ደመራ ተካይ ማኅበረሰቡ እንዲሰባሰብ በጡሩምባ ታግዞ ጥሪ ያስተላልፋል፡፡ የአካባቢው ማኅበረሰብም የደመራ እንጨት በመያዝ ደመራው ወደሚተከልበት ቦታ ይሰባሰባል።
የተመረጠው ደመራ ተካይም ‹‹እዮሃ›› እያለ የደመራዋን ዋና ቋሚ ወይንም ምሰሶ መጀመሪያ ከተከለ በኋላ ማኅበረሰቡ ያመጣውን እንጨት በጋራ በመኾን ደመራውን ያቆማሉ። ደመራው ተደምሮ እንደተጠናቀቀ የተሰበሰበው ሰው በአራቱ አቅጣጫ አየዞረ ፈጣሪውን አመስግኖ መሬት ስሞ ይቀመጣል።
ጉምቱዎቹ የአካባቢው ሀገር ሽማግሌዎች ተነስተው ይመርቃሉ፡፡ ከተመረቀ በኋላ “እዮሃ” እየተባለ ደመራውን ዞረው ደመራ ተካዩን አጅበው እየጨፈሩ ወደ ደመራ ተካዩ ቤት ይሄዳሉ። ከደመራ ተካዩ ቤት እንደደረሱም የተዘጋጀው ባሕላዊ ምግብ እና መጠጥ ይቀርባል። እስከ መስከረም 17 ቀን ንጋት ደመራ እስኪለኮስ ድረስ በተለይም ወጣቶች የፊፊ ጨዋታ ሲጨፍሩ ያድራሉ።
ከንጋቱ 10 ሰዓት ገደማ ጀምሮም ችቦውን በመለኮስ በጡሩምባ በማድመቅ ወደ ደመራ ቦታ ይጓዛሉ፡፡ ደመራው ላይ ሁሉም ሰው ሲሰባሰብ ሽማግሌዎች ይመርቃሉ። ከምረቃ በኋላ ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ ፊታቸውን አዙረው ችቦው በማቀጣጠል ደመራው ይለኮሳል።
መስከረም 17 በደመራው ቦታ የተመራጩ ደመራ ተካይ ባለቤት ሽሮ፣ ጉዝጉዞ፣ እርጎ እና ጠላ ቀድማ ለተሰበሰበው ሰው ታቀርባለች፡፡ የተሰበሰበው ሰው የቀረበውን ምግብ እና መጠጥ እየተስተናገደ ሌሎች ሰዎችም ምግብና መጠጥ እንዲያቀርቡ ይደረጋል።
የቀረበው እየተበላና እየተጠጣ ወጣቱ የፊፊ፣ አንበሳ የገደለ የአንበሳ ገዳይ ጭፈራ እና ሌሎችም የጭፈራ አይነነቶች ሲጨፈር ይውላል። አመሻሽ አካባቢ በበዓሉ ላይ የዋሉት ሁሉ በጋራ ሆነው እየጨፈሩ ወደ ደመራ ተካይ ቤት ጉዞ ያደረጋሉ፡፡ ከደመራ ተካይ ቤት ከተገባ በኋላም እየተበላና እየተጠጣ አሁንም ጭፈራው ይቀጥላል፡፡
በዓሉ እስከ መስከረም 19 ቀን ድረስ በተለያዩ ዝግጅቶች እና ጭፈራዎች ዝግጅቱ ይቀጥላል። መስከረም 19 ቀን ደግሞ ወጣቶች ፊፊ እየተጫወቱ በየቤቱ በመዞር ገንዘብ ይቀበላሉ፡፡ በተሰበሰበው ገንዘብ ፍየል ተገዝቶ ይታረድና ፊፊው በፍየል ደም ተቀብቶ ይያዛል “ለቀጣይ ዓመት በሰላም ያድርሰን” እየተባለ ተመራርቆ እና ለበዓሉ በተዘጋጀው ምግብ እና መጠጥ ተስተናግደው ክብረ በዓሉ ይጠናቀቃል፡፡ ፊፊው በፍል ደም የሚቀባውም ተጫዋቹ ጉልበት እንዲኖረው፤ ፊፊውም ኃይል እንዲያገኝ በማሰብ እንደኾነ አቶ ንጋቱ ነግረውናል።
የመስቀል በዓልን በጃዊ የተለየ የሚያደርገው ግን አንድ ሌላ ውብ ክስተትም አለ፡፡ የሰው ልጅ አብሮ ሲኖር በተለያዩ ምክንያቶች ግጭት መኖሩ ተፈጥሯዊ ክስተት ነው፡፡ ግጭቱን የሀገር ሽማግሌዎች አይተውት የበደለ ክሶ የተበደለ ተክሶ እርቅ ማውረድ ደግሞ የኢትዮጵያዊያን የቆየ ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ሥርዓት እንደሆነ ይነገራል፡፡
ጃዊዎች መስቀልን በጋራ ሆነው ሲያከብሩ በተለያየ አጋጣሚ ተጋጭተው ያልታረቁ ሰዎች ቢኖሩ ቅድሚያ እርቅ እንዲፈጽሙ ይደረጋል፡፡ “ቂም ይዞ ጸሎት ሳል ይዞ ስርቆት” እንዲሉ አበው ኢትዮጵያዊያን ቂም ተያይዞ እና ተኮራርፎ በመስቀል በዓል ላይ መሰባሰብ ፈጽሞ የተከለከለ ነው። በዓሉን በሰላምና በፍቅር በጋራ ተሰባስቦ ለማሳለፍ ቢያንስ ከዓሉ በፊት ባሉ 15 ቀናት የአካባቢው የሀገር ሽግሌዎች የተጣሉ ሰዎችን በመለየት እስከ ዋዜማው ድረስ ያስታርቃሉ።
የመስቀል በዓል የሰላም እና የአንድነት ምሳሌ ተደርጎ ስለሚወሰድ ለመስቀል በዓል የታረቁ ሰዎች እርቃቸው የጸና ይኾናል ይላሉ። ለቂም እና ጥላቻ ጊዜ እና ቦታ መስጠት ሃይማኖታዊም ኾነ ማኅበራዊ መሠረት የለውም የሚሉት አቶ ንጋቱ ማኅበረሰቡ ለመስቀል በዓል ሲል የሚያወርደውን እርቀ ሰላም በማጠናከር የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በማንኛውን ወቅት ላይ መፍታት እና አንድነቱን ማጠናከር ይገባልም ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!