ዜጎችን ከገዳዩን የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል እየሠራ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገለጸ፡፡

221

ባሕር ዳር፡- ጥር 20/2012ዓ.ም (አብመድ) ኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ክትትል እና ቁጥጥር እያደረገ እንደሚገኝ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በድረ ገጹ እንዳስታወቀው ከቻይና እና አጎራባች አገሮች ለሚመጡ መንገደኞች በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የሙቀት ልየታ ተግባር እያከናወነ ነው፡፡ ጉዳዩ ከተሰማበት እስከ ጥር 18/2012 ዓ.ም ድረስም ለ20 ሺህ 802 መንገደኞች ቅድመ ልየታ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ የቅድመ ምርመራ ከተደረገላቸው መካከልም 552 ያክሉ የኮሮና ቫይረስ ካለባቸው ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ናቸው፡፡ ከነዚህም ውስጥ ከቻይና የመጡ አራት የበሽታው አስጊ ምልክት ይኖርባቸዋል የተባሉ ሰዎች በለይቶ ማከሚያ ማእከል ሆነው ክትትል እንደተደረገላቸው እንደሚገኙ ታውቋል፡፡

በበሽታው ከተጠረጠሩ ከአራቱ ሰዎች የላቦራቶሪ ናሙና ተወስዶ በደቡብ አፍሪካና በሀገር ውስጥ ምርመራ እንደተደረገና ከኮሮና ቫይረሶች ነጻ መሆናቸው መረጋገጡን ሚኒስቴሩ አሳውቋል፡፡ ‹‹ቫይረሱ ከተከሰተባቸው ሀገራት የመጡ ናቸው›› ተብለው የተለዩት ቀሪ መንገደኞችም ክትትል እንደሚደረግላቸው ነው የተገለጸው፡፡ መረጃው እንደሚያመለክተው ቫይረሱ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ ጥብቅ ክትትል እየተደረገ ነው፡፡

በበሽታው የተጠረጠሩ መንገደኞች ክትትል ለማድረግም የጊዜያዊ ማቆያ ማእከል በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተቋቁሟል፡፡ በጽኑ ለታመሙና ከፍተኛ የህክምና ክትትል ለሚያስፈልጋቸው ደግሞ በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል የተለየ ክፍል መዘጋጀቱን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል፡፡ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከሚደረገው ክትትል በተጨማሪ በሁሉም የሀገሪቱ ጠረፋማ ቦታዎች በሽታው እንዳይከሰት በተዋረድ ከሚገኙ የክልል ጤና ቢሮዎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት አየተሠራ እንደሆነም ሚኒስቴሩ አመላክቷል፡፡

የኮሮና ቫይረስ በሽታ በወርሃ ታኅሳስ መገባደጃ 2012 ዓ.ም መከሰቱ ከተረጋገጠበት ጊዜ ጀምሮ የበሽታው ምልክት ስድስት ሺህ በሚሆኑ ሰዎች እንደታየና 132 ለሚኑ የዓለማችን ነዋሪዎች ለህልፈት ምክንያት እንደሆነ ሲ ኤን ኤን ዛሬ ይዞት የወጣው መረጃ ያሳያል፡፡ ወረርሽኙ የተዛመተባቸው ሀገራት ቁጥርም ወደ 17 ከፍ ብሏል፡፡ እንደ ኬንያ፣ ናይጄሪያ፣ ዩጋንዳ እና ሴኔጋል ያሉ ሀገራት የበሽታው አጠራጣሪ ምልክት ታይቶባቸዋል ባሏቸው ተጓዦች ላይ የቅድመ ልየታና ክትትል ሥራዎችን እየሠሩ ይገኛሉ፡፡

በኃይሉ ማሞ

Previous articleየታገቱ ተማሪዎችን በተመለከተ መንግስት አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጥ በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የምሁራን መማክርት ጉባኤ በድጋሜ ጠየቀ፡፡
Next articleባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የትያትር ትምህርት ክፍል ሊከፍት ነው፡፡