“በመስቀል በዓል ላይ የሚበረከት የትውልድ አደራ”

46

ባሕርዳር፡ መስከረም 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የክረምቱ ከባድ ዝናብ እና ጎርፍ ምጥጥ ብሎ እንደልብ መንቀሳቀስ ይጀመራል፡፡ በጉም የተሸፈነችው ፀሐይ የከለላት ደመና ተገፎ ብርሃኗ ያለከልካይ ለምድር ይደርሳል፡፡ አፈር ተሸክመው ሲገማሸሩ የከረሙ ወንዞች ሸክማቸውን አራግፈው የጠራ ውኃ ሲፈስባቸው ይታያል፡፡

ሜዳው፣ ሸለቆው እና ሸንተረሩ በአደይ አበባ ተውቦ ለተመልካቹ ቀልብ አንጠልጣይ ይሆናል፡፡ የአበቦቹ መዓዛ እና ሽታ ምድርን ያውዳታል፡፡ ተራርቀው የከረሙ ሰዎች ያኔ መገናኘት ይጀምራሉ፡፡ ይህ ሁሉ ሲስተዋል አሮጌው ዓመት እየተጠቀለለ አዲሱ ዓመት በአዲስ ተስፋ የዘመን ስሌቱን መቁጠር ይጀምራል፡፡

ሰዎች እንኳን አደረሳችሁ በመባባል የመልካም ምኞት መልዕክቶቻቸውን ይለዋወጣሉ፡፡ ከዚያ ከባድ እና ጨለማ ከሆነ የክርምት ድባቴ ወጥቶ በአዲስ ዓመት ንጋት አዲስ ነገር ማለም ይጀመራል፡፡ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ሁሉም የየራሱ ህልም ቢኖረውም የተማሪዎች ህልም ግን ይለያል፡፡ ትምህርት ቤቶቻቸው ለአዲስ ዓመት ትምህርት ዝግጁ ከመሆናቸው በፊት በየሰፈራቸው የሚጠብቁት አንድ አስደሳች ነገር ልባቸውን ይንጠዋል፡፡ በመስቀል በዓል ዝግጅት ላይ የሚበረከት የጀግና ተማሪ ገጸ በረከት፡፡

ይህ ዓመታዊ የጀግና ተማሪዎች ማበረታቻ በባሕር ዳር ከተማ አስተዳዳር ቀበሌ 16 ቤዛ ብዙኃን አካባቢ የሚገኙ ተማሪዎች ዓመታዊ የማበረታቻ ዝግጅት ደግሞ ከሌሎችም ይለያል፡፡ ተማሪዎቹ ባለፈው ዓመት የትምህርት ቆይታቸው ላገኙት የላቀ ውጤት የመስቀል ዕለት ከቤተሰቦቻቸው እና ጎረቤቶቻቸው የጀግና ተማሪ ሽልማት ይጠብቃቸዋል፡፡ ልጆቹ ደግሞ ያንን ቀን አብዝተው በናፍቆት ይጠብቁታል፡፡

እንደ ዋዛ የተወሰኑ ተማሪዎችን ለማበርታት የተጀመረው ሽልማት አሁን ላይ እጅግ ሰፍቶ እስከ 25 ተማሪዎችን በአንድ ዓመት መሸለም ተችሏል፡፡ ሽልማቱ እንደ ትምህርት ደረጃቸው ከአፀደ ሕጻናት እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ የሚወሰን መኾኑ ደግሞ ተማሪዎችን ይበልጥ ያጓጓቸዋል፡፡

በመስቀል ዋዜማ ሌሊቱን ሁሉ እንደ ተደመረ የሚያድረውን ደመራ ተሰባስበው ደምረው፤ በደመራው ዙሪያ ተሰባስበው እየተጨዋዎቱ የሚበላ የሚጠጣው ነገር ሁሉ ከተጠናቀቀ በኋላ የሚከናወነው ሥነ ሥርአት የተማሪዎችን የአንድ ዓመት የትምህርት ዘመን ልፋት ውጤት ተናፋቂ የሚያደርግ ነው፡፡ ዘንድሮ ማን ይሸለማል? ምን ይሸለማል? ማን ይቀር ይኾን? የሚሉት ስሌቶች በአብዛኛው የሚጠናቀው ገና በወርሃ ሰኔ ቢሆንም እንደሚሸለሙ እያዎቁት እንኳን በጉጉት ይጠብቁታል፡፡

የኹሉም ተማሪዎች ልብ ቀጥ ልትል ትደርሳለች፡፡ ሽልማቱ ዓመቱን በሙሉ ማበረታቻ ኾኗቸዋል ይላሉ ወላጆቻቸው፡፡ ብዙዎች ወላጆች ለልጆቻቸው የሚመኙትን ልጆቻቸውም ሆነውላቸው ተደስተዋል፡፡ ከልጅ ስኬት በላይ ለወላጅ ምንስ ደስታ እና ኩራት ሊኖር ይችላል፡፡

በርካቶቹ በዚህ ልማድ ተቀርፀው መምህር፣ የጤና ባለሙያ፣ የሒሳብ አዋቂ፣ መሃንዲስ፣ ሐኪም ኾነው ሕዝባቸውን እና ሀገራቸውን በቅንንት የሚያገለግሉ የጥሩ ሙያ እና የጥሩ ሥነ-ምግባር ባለቤት ኾነዋል፡፡ ደግሞ እነርሱም በተራቸው ሌሎች ልጆችን ይሸልሙ ዘንድ ዘመን እድል እና እድሜ ሰጥቷቸዋል፡፡

በባሕር ዳር ከተማ የሕዳሴ ቀበሌ ነዋሪ እና የዓመታዊ ሽልማቱ አስተባባሪ ወይዘሮ እናት መኮንን ትናንት ሸልመን ያሳደግናቸው ልጆች ዛሬ ታናናሾቻቸውን እየሸለሙ ነው ብለውናል፡፡

ወይዘሮ እናት ዓመታዊ ሽልማቱ መቼ እንደተጀመረ ትክክለኛ ጊዜውን ባያስታውሱትም ከ20 ዓመት በላይ እንደኾነው እና ሕጻን ኾነው የተሸለሙ ተማሪዎች ተመርቀው በመንግሥት ሥራ ላይ መሠማራታቸውን ነግረውናል፡፡ ሽልማቱ በርካታ ተማሪዎችን ለተሻለ ውጤት አነሳስቶ ለጥሩ ደረጃ አድርሷቸዋል ይላሉ፡፡

ሽልማቱ ያንን ያክል የበዛ ባይሆንም ልጆቹ ለሽልማት መጠራታቸው ብቻ እጅግ ያስደስታቸዋል የሚሉት የሽልማቱ አስተባባሪ መማሪያ ደብተር፣ እስክርቢቶ፣ አጋዥ መጽሐፍ እና ወደ ዩኒቨርሲቲ ለሚገቡ ተማሪዎቹም ደግሞ አንሶላ እና ሻንጣ በሽልማት መልክ ይበረከትላቸዋል፡፡

ለሽልማቱ ልጅ ያለውም ልጅ የሌለውም እኩል ያወጣል፤ በሰፈር ልጆች ጉዳይ ሁሉም ባለቤት ነውና ያጠፋ ሲኖር ተጠርቶ ይመክራል ብለውናል ወይዘሮ እናት፡፡ ኹሉም ሰው ልጆችን በባለቤትነት ሥሜት ተከታትሎ ካሳደገ በትምህርቱ የሚደክም እና አልባሌ ቦታ የሚውል ትውልድ አናፈራም ይላሉ፡፡

ሽልማቱ ምንም እንኳን በአንድ የተወሰነ አካባቢ የሚካሄድ ቢሆንም “በመስቀል በዓል ላይ የሚበረከት የትውልድ አደራ” ነው፡፡ ኹሉም እናቶች ልጆችን እንደራሳቸው ልጆች አድርገው እንዲቆጣጠሩ እና ለትምህርታቸው አጋዥ እንዲኾኑም ወይዘሮ እናት አሳስበዋል፡፡

በትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ለሀገራችን ኢትዮጵያ እና ለሕዝቧ ከምንም በላይ የሚያስፈልገው ልባዊና ተግባራዊ ሰላምና ይቅርታ ነው” ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ
Next article“ጃዊ በፊፊ መስቀልን ታደምቃለች፤ እርቅ አውርዳ ግጭትን ታርቃለች”