“ለሀገራችን ኢትዮጵያ እና ለሕዝቧ ከምንም በላይ የሚያስፈልገው ልባዊና ተግባራዊ ሰላምና ይቅርታ ነው” ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ

47

ባሕር ዳር: መስከረም 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የመስቀል በዓል በጎንደር ከተማ ሃይማኖታዊ ስርዓቱን ጠብቆ በሰላም ተከብሯል።

ለበዓሉ ታዳሚዎችና አማኞች መልዕክት ያስተላለፉት የማዕከላዊ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ መስቀሉን ስናከብር ሰላምን እየተማርን የሰላም ጥቅምን እያወጅን፣ የሰላምን ዝማሬ እየዘመርን በሙሉ ልባችን ከመስቀሉ የተገኘውን ሰላም እየሰበክን መኾን አለበት ብለዋል።

ብፁዕነታቸው አክለውም “ለሀገራችን ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ ከምንም በላይ የሚያስፈልገው ልባዊና ተግባራዊ ሰላምና ይቅርታ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከገበሬ እስከ ነጋዴ ከመንግሥት ሠራተኛ እስከ ከፍተኛ የመንግሥት አካላት ለሀገራችን ሰላም አጥብቀው እንዲሠሩ የጠየቁት ብፁዕነታቸው ከዳግም ጥፋትና ሃዘን ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን እንዲታደግ ተመኝተዋል።

የመስቀል በዓል በሰላም ተከብሮ መጠናቀቁን የገለጡት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተወካይ ከንቲባ ግርማይ ልጃለም ያጋጠሙ ችግሮችም በሰላም ለመፍታት መነሳሳት ይጠበቃል ብለዋል።

የበዓሉ ታዳሚዎች በሊቃውንት ታጅቦ በምዕመኑ ደምቆ በተከበረው የመስቀል በዓል መታደማቸው እና በሰላም በመጠናቀቁ ደስታቸውን ገልጠው ፣ አሁንም ሠላምን አበክረው እንደሚሹ ጠቁመዋል።

ዘጋቢ:- አገኘሁ አበባው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ዛሬም በዓለም የተደበቀ ሰላም አለ፤ እሱን እንደ መስቀሉ ፈልገን ማግኘት አለብን” የዋግኽምራ ሀገረ ስብከተ ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖደስ አባል ብፁዕ አቡነ በርናባስ
Next article“በመስቀል በዓል ላይ የሚበረከት የትውልድ አደራ”