
ባሕር ዳር: መስከረም 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የመስቀል በዓል በሰቆጣ ከተማ በደማቅ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ተከብሯል። በበዓሉ ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ የሰቆጣ ከተማ እና የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችና የሃይማኖቱ ተከታዮች ተገኝተዋል።
የዋግኽምራ ሀገረ ስብከተ ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖደስ አባል ብፁዕ አቡነ በርናባስ በተደበቀው መስቀል ድኀነት እንዳገኘን ኹሉ ዛሬ በሀገራችን እየታየ ያለውን የሰላም መደፍረስ ችግሮችን በመለየት ሰላማችንን እንደ መስቀሉ ፈልገን ማግኘት አለብን ብለዋል።
ብፁዕ አቡነ በርናባስ “ዛሬም በዓለም የተደበቀ ሰላም አለ እሱን እንደ መስቀሉ ፈልገን ማግኘት ነው ያለብን” ብለዋል። የተቀበረውን መስቀል በአንድነት ተባብረው እና ቆፍረው እንዳገኙት ሁሉ እኛም ሰላማችንን ለማግኘት መለያየት ሳይኾን አንድ መኾንና መተሳሰብ አለብን ነው ያሉት።
በመስቀል ላይ ያሳየነውን አንድነትና ፍቅር ለሌላው ጊዜም አጠናክረን መቀጠል አለብን ሲሉም ብፁዕ አቡነ በርናባስ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ:- ሰሎሞን ደሴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!