
ባሕርዳር፡ መስከረም 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ቅጠሎች አብበዋል፣ አበቦችም ፍሬን ሰጥተዋል፣ ፍሬውም አሽቷል፣ ዘራቸውን በምድር ላይ በትነው በተስፋ የጠበቁ ተስፋን አይተዋል፣ ከእሸቱም ቀምሰዋል፣ የምኅረት ዝናብን አዝንቦ ምድርን ያረሰረሳትን፣ በልምላሜ የሸፈናትን፣ ፍሬ ትሰጥ ዘንድም የባረካትን፣ አዝዕርት ባርኮና ቀድሶ እሸት ያቀመሳቸውን አምላካቸውን ያመሠግኑታል፡፡
እርሱ በቸርነቱ ፍጥረታትን ይመግባቸዋል፣ ሌሊቱን እያሳለፈ ማዕልቱን ያሳያቸዋል፣ ጨለማዋን እያሻገረ በብርሃን ይመላቸዋል፣ ማዕበሉን እያሳለፈ በለመለመው መስክ ያሰማራቸዋል፣ ነጎድጓድ የሚበዛበትን፣ አስፈሪ ጉምና ጭጋግ የሚታይበትን፣ አስፈሪ ማዕበል የሚደነፋበትን ክረምት እያሳለፈ ወንዞች ባዘቶ ወደሚመስሉበት፣ ተራራዎችና ኮረብታዎች ወደ ሚዋቡበት ወራት ያሸጋግራቸዋል፡፡
አሮጌውን ዘመን እያሳለፈ፣ ዘመናትን በቸርነቱና በምህረቱ ያቀዳጃቸዋል፣ ተስፋና በረከትም ይሰጣቸዋል፡፡ እነሆ አሮጌውን ዘመን አሳልፎ አዲስ ዘመንን አቀዳጅቷል፡፡ መስከረም ጠብቷል፡፡ አበቦች አብበዋል፣ ፍሬንም ሰጥተዋል፡፡ በዓለ መስቀልም ደርሷል፤ ደመራው ተደምሯል፣ ችቦው ተበርቷል፣ ነገረ መስቀሉ እየታሰበ ተለኩሷል፡፡
በዓለ መስቀል በሃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ በረከትን እና ረድኤትን ይዞ እንደሚመጣ ይታመናል፡፡ አዝርዕቱን ይባርከዋል፣ ልጆችን ያሳድጋቸዋል፣ ከብቶችና ፍየሎችም፣ በጎችና ፈረሶችን፣ በቅሎና ግመሎችን ሁሉንም ከወረርሽኝ ጠብቆ እንዲያገለግሉ እና እንዲጠቅሙ ያደርጋቸዋል፣ በምድር ላይ መቅሰፍትን ያርቃል፣ ጎተራውን በምርት ይመላል፣ ፍቅርና ሰላምን ያወርዳል ተብሎ ይታመናል፡፡
ክርስቲያኖች መስቀል በደረሰ ጊዜ “እንጎሮጎባሽ” እየተባባሉ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ይለዋወጣሉ፡፡ በተለይም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ይህ ቃል ይዘወተራል፣ በበዓለ መስቀልም ተደጋግሞ ይጠራል፡፡ በአመሻሽ የሀገሬው ሰዎች በማዕከል ሥፍራ ተገናኝተው፣ ደመራ ይደምራሉ፣ ደመራው ተሠርቶ በተጠናቀቀም ጊዜ ደመራውን በሃይማኖት አባቶች እና በሀገር ሽማግሌዎች መሪነት ዙረው ሌሊት ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘው ይለያያሉ፡፡
ሌሊቱ ሊነጋ ሲቃረብ፣ ዶሮ ሲጮህ ሁሉም በየቤቱ ችቦውን እየለኮሰ ፣የቤቱን በር እና የበሬውን ግንባር እየተረኮሰ ፣እንደዚህ ተርኩሰው እየተባባለ “ እዮሃ መስቀል ጠባ” እያለ ይወጣል፡፡ ልጆች አባታቸውን ተከትለው ችቦ አቀጣጥለው ይጓዛሉ፣ ችቦ ሳይዝ ወደ ደመራው የሚሄድ የለም፡፡
በዚያ ሰዓት ድቅድቅ ጨለማው በብርሃን ይመላል፣ ከየመንደሩ የሚወጣው የችቦ ብርሃን እጹብ ያሰኛል፡፡ በደመራው ሥፍራም በተገናኙ ጊዜ ቀሳውስቱ ከፊት ቀድመው፣ ሽማግሌዎች ተከትለው፣ ሁሉም በየማዕረጋቸው እና በየደረጃቸው እየተከታተሉ “ ዓመታኩሾዬ፣ ኾዬ፣ መስቀል ኾዬ” እየተባለ ደመራው ይዞራል፡፡ ደመራው ከተዞረ በኋላ በቄሱ ተባርኮ ደመራው ይለኮሳል፡፡
ሌሊቱ በነጋም ጊዜ “ እንጎሮጎባሽ” ይባላል፡፡ እናቶች ያን ጊዜ የጓሮውን እሸት ይፈትሻሉ፣ እሸትም እየቆረጡ ደመራው ወደ ተቀጣጠለበት ሥፍራ ይጓዛሉ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በባሕርዳር ሀገረ ስብከት የአራቱ ጉባያት መምህር ሊቀ ሊቃውን ስመዓኮነ መልአክ “እንጎረጎባሽ” እንኳን ወደ ጓሮ ገባሽ የሚለው በዘመን መለዋወጥ የተለወጠ ነው ይላሉ፡፡ እናቶች እሸት ሊቆርጡ ወደጓሮ የሚገቡት የመስቀል ደመራ ከተቃጠለ በኋላ ነው፡፡
በአንዳንድ አካባቢ ከመስቀል አስቀድሞ እሸት መቅመስ ነውር ነው፡፡ መስቀል ሳይውል የጓሮ እሸት አይቀመስም፡፡ መስቀል አልደረሰም፣ ደመራ አልተለኮሰም ተብሎ ወደ ጓሮ አይገባም፡፡ መስቀል ደርሶ ደመራ ሲለኮስ ግን እናቶች ወደ ጎሮ ይገባሉ፣ እሸትም ቆርጠው በደመራው እሳት ይጠብሳሉ፣ እሸቱንም ያቀምሳሉ፣ ይቀምሳሉ፡፡
እሸትም መብላት የሚጀመረው ከዚያው ከደመራው ላይ ነው፡፡ የመስቀል ቀን የጓሮን እሸት በደመራው እሳት መጥበስና እሸት መቅመስ ያበረክተዋል፣ ምርቱንም ያሰፈዋል ተብሎ ይታመናል፡፡ ምርት ሲበረክት፣ ጎተራው ሲሞላ ገበያው ጥጋብ ይኾናል፡፡ ገበያውን አይራበው፣ ገበያውን ያጥግበው፣ የሀገሬውን ሰው የእለት ጉርስ የዓመት ልብስ አይንሳው እየተባለ ይመረቃል፡፡ ገበያው ጥጋብ ሲኾን የሚራብ አይኖርም፣ ገበያው ጥጋብ ሲኾን በችግር ጅራፍ የሚገረፍ ወገን አይታይም፡፡ ለዛም ነው ጎተራው ይሙላ፣ ገበያው ጥጋብ ይሁን እያሉ የሚመርቁት፡፡
ጎተራው የሚሞላው፣ ገበያው የሚጠግበው፣ ገበሬውን በክረምት ዝናቡን፣ በበጋ ፀሐዩን ሳይፈራ ሲያቀዘዠቨርስና ሲያንደፋርስ፣ አምላክም ቸርነቱን እና መግቦቱን ሲሰጠው ነው፡፡ ለዛም ነው የሀገሬው ሰው በረከት እንዳይለይበት መስቀል ሳይደርስ፣ ደመራ ሳይለኮስ እሸት አልቀምስም የሚለው፡፡
እሜቴ የጓሮው እሸት አሽቷል፣ ፍሬም አፍርቷል፣ መስቀልም ደርሷል፣ ደመራው ተደምሯል፣ ደመራውም ተለኩሷል እና እንጎረጎባሽ፣ እንኳን ወደ ጓሮ ገባሽ፣ እንኳን በአዲስ ዘመን አዲስ እሸት ለመቅመስ አበቃሽ፣ እንኳን አደረሰሽ እንኳን አደረሳችሁ፡፡ በረከትና ረድኤት የሚበዛበት፣ ደስታና ፍቅር የሚታወጅበት፣ ጥል ተሰብሮ አንድነት የሚበሰርበት ነውና እንኳን አደረሳችሁ፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!