የታገቱ ተማሪዎችን በተመለከተ መንግስት አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጥ በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የምሁራን መማክርት ጉባኤ በድጋሜ ጠየቀ፡፡

337

ባሕር ዳር፡- ጥር 19/2012ዓ.ም (አብመድ) የምሁራን መማክርት ጉባዔው ጉዳዩን በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል፡፡

በደምቢደሎ ዩኒቨርስቲ ሲማሩ የነበሩ የአማራ ተወላጅ ተማሪዎች ባልታወቁ ሃይሎች ታገተው እስክ አሁን ድረስ ያሉበት ሁኔታ የማይታወቅ በመሆኑ የፌደራልና ኦሮምያ የክልል መንግሥታት በጉዳዩ ትክክለኛ መረጃ እንዲሰጡና በአፋጣኝ ችግሩ እንዲፈታ በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የምሁራን መማክርት ጉባኤ በድጋሜ አሳስቧል፡፡

የአማራ ምሁራን መማክርት በደምቢደሎ ዩኒቨርስቲ ሲማሩ የነበሩ ተማሪዎች መታገታቸውን የተመለከቱ መረጃዎች መውጣት በጀመሩበት ወቅት የፌዴራልና የክልል መንግስታት ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት አለመስጣቸውን በመገለጽ መንግሥታዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ በአፅንዖት ማሳሰቡን በመግለጫው አስታውሷል፡፡ ተማሪዎቹ ታግተው ያሉበት ሁኔታ አለመታወቁ እጅጉን ያሳሰበው መሆኑን በማስረዳት ለጉዳዩም ቅርበት ካላቸው የክልል መንግሥት ኃላፊዎች ጋር ውይይት ማድረጉን፣ የታገቱትን ተማሪዎች በሽምግልና ለማስለቀቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን እና በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊለቀቁ እንደሚችሉም መረጃ ተሰጥቶት እንደነበር የመማክርት ጉባኤው አስታውቋል፡፡

ነገር ግን እስከ አሁን ድረስ የታገቱት ተማሪዎች ስለመለቀቃቸውም ሆነ ስላሉብት ወይም ስለሚለቀቁበት ሁኔታ የሚጨበጥ መረጃም ሆነ ማስረጃ በአግባቡ ያልተሰጠ ከመሆኑም በላይ የፌዴራል መንግሥት የተለያዩ አካላት ‹ጉዳዩን አናውቅም› ከማለት ጀምሮ እርስ በርሱ የሚጣረስ መረጃ እየሰጡ እንደሚገኙ፣ ይህ አይነቱ ኃላፊነት የጎደለው ምላሽ ደግሞ እጅግ የሚያሳዝንና ግራ የሚያጋባ ከመሆኑም በላይ ዜጎች በመንግሥት ህግ የማስከበር አቅም እና ቁርጠኛነት እምነት እንዳይኖራቸው እንደሚያደርግ ነው የመማክርት ጉባኤው በላከው መግለጫ ያስታወቀው፡፡

አሳዛኝ ክስተቱ የፍትህ እና የጸጥታ አስከባሪ አካላት ኃላፊነታቸውን በትጋት እና ያለአንዳች አድልዎ እየተወጡ አለመሆናቸውን ግልጽ ማሳያ ነው ያለው የምሁራን መማክርት ጉባኤው የፍትህ እና የጸጥታ አስከባሪ አካላት የዜጎችን ደኅንነት በማረጋገጥ ረገድ እያሳዩት ያለው ቸልተኝነት እና አድልዎአዊነት በአፋጣኝ እስካልታረመ ድረስ ስርዓት አልበኝነት መስፋፋቱና መሰል ህገወጥ ተግባራት መፈጸማቸው አይቀሬ በመሆኑ ዜጎች መንግስትን ተማምነው በሀገራቸው በነጻነት የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ ፈጽሞ ሊፈጠር እንደማይችል ሥጋቱን ገልጧል፡፡

ስለሆነም መንግስት የጉዳዩን አሳሰቢነት ተረድቶ የታገቱት ተማሪዎች ያሉበትን ሁኔታ በተመለከተ በአስቸኳይ ግልጽና አሳማኝ መረጃ እንዲሰጥ እንዲሁም በአፋጣኝ ተጨባጭ ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ተማሪዎቹ በአስቸካይ ተለቅቀው ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉና ወደ ትምህርት ገበታቸውም እንዲመለሱ የመማክርት ጉባኤው በድጋሚ በአጽንዖት ማሳሰቡን ለአብመድ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

በመጨረሻም የታገቱ ተማሪዎችን በተመለከተ መንግስት አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጥ ዛሬ በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች እጅግ ሠላማዊ እና ስልጡን በሆነ መንገድ በተካሄዱ ሠልፎች ሕዝቡ ማሳሰቡን እያደነቀ መንግሥት በሰለጠነ መንገድ ለቀረበለት የሕዝብ ማሳሰቢያ ትኩረት በመሥጠት ወደ ቁጣ ከመቀየሩ በፊት በአስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጥ ምክር መሥጠቱን የምሁራን መማክርት ጉባዔው አስታውቋል፡፡

በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የምሁራን መማክርት ጉባኤ
ጥር 19/05/2012 ዓ.ም

Previous articleሰላማዊ ሰልፎቹ በሠላም መጠናቀቃቸውን ፖሊስ አስታወቀ፡፡
Next articleዜጎችን ከገዳዩን የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል እየሠራ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገለጸ፡፡