“መስቀል ተከበረ፣ ፍቅር ተበሰረ”

61

ባሕርዳር፡ መስከረም 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ምድር መድኃኒቷን አገኘች፣ በተስፋ የጠበቀችውን አየች፣ ከእስርና ከመከራ ሰንሰለት ተላቀቀች፣ የጨለማውንም ካባ አውልቃ የብርሃኑን ካባ አጠለቀች፡፡ የብርሃኑን ካባ የሰው እጅ አልሠራውም፣ የሰው ልቡናም አይመረምረውም፤ በመስቀሉ የበራው ከብርሃናት ሁሉ ይበልጣል፣ እጅግ ከነጡትም ይልቃል፡፡

እነኾ አዲሱ ዓመት አብቷል፣ መብረቃት የሚበዙበት፣ ብርድና ቆፈን ያለበት፣ ማዕበልና ጉም የሚበረክትበት የክረምቱ ወራት አልፏል፤ ምድር ፍሬዋን የምታፈራበት፣ ያጎጡት አበባ የሚኾኑበት፣ አምላኩን አምኖ ዘሩን የበተነ ገበሬ የተስፋውን ፍሬ የሚያይበት፣ ምድር በውበት የምትጎናጸፍበት ዘመንም ተተክቷል፡፡

ተራራዎች አጊጠዋል፣ ሜዳና ሸንተረሮች ተውበዋል፣ አፍላጋት ድፍርሱን አጥርተው ባዘቶ መስለዋል፡፡ ሰዓታትን እያስተካከለች፣ ቀናትን እየቆጠረች፣ ሳምንታትን እያመቻቸች፣ ወራትን እየቀመረች፣ ዓመታትን እና ዘመናትን የምትቆጥረው ኢትዮጵያ አሮጌውን ዘመን ሸኝታ አዲሱ ዘመንን ተቀብላለች፡፡ ለአዲሱ ዓመት ብሥራት ነጋሪት ጎስማለች፤ እንኳን ከዘመን ዘመን አሸጋገራችሁ ብላ አዋጅ አውጃለች፣ የአዲሱን ዘመን ብሥራት አብስራ ተቀብላለች፡፡

የኢትዮጵያ ሊቃውንት ቀናትን፣ ወራትን እና ዓመታትን በምስጢር አስቀመጧቸው፣ በጥበብ ከፋፈሏቸው፣ በረቀቀ እውቀት ሰየሟቸው እንጂ ዝም ብለው አልደረደሯቸውም፤ ዝም ብለው አልጠሯቸውም፡፡ ያለ ትርጉም የሰየሙት፣ ያለ ምስጢር የቀመሩት፣ ያለ ረቂቅ እውቀትና ጥበብ የከፈሉት የለም፡፡ ሁሉም በምስጢር ተቀመረ፣ በጥበብ ከበረ እንጂ፡፡

ኢትዮጵያ በዓላትን ከእነ ሥርዓታቸው እና ከእነ ሕጋቸው ጠብቃ ታከብራለች፣ ጠብቃም ትኖራለች፣ ለትወልድም ታስተላልፋለች፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በወረኃ መስከረም የኢየሱስ ክርስቶስን ብርሃነ መስቀል ታከብራለች፡፡ በዓለ መስቀል በደረሰ ጊዜም ክርስቲያኖች ይሰባሰባሉ፣ የአምላክ ስም በሚመሰገንበት፣ በረከትና ረድኤት በሚገኝበትም ሥፍራ ይገናኛሉ፡፡ በረከትንም ይቀበላሉ፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በወርኃ መስከረም መስቀልን በልዩ ልዩ ቀናት ታስበዋለች፣ ታከብረዋለች፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በባሕርዳር ሀገረ ስብከት የአራቱ ጉባያት መምህር ሊቀ ሊቃውንት ስመዓኮነ መልአክ በቤተክርስቲያን ሥርዓት መስከረም ከባተ ጀምሮ እስከ ስምንት ድረስ ያለው ዮሐንስ ተብሎ ይጠራ ነበር፡፡ ከስምንት ጀምሮ እስከ አሥራ አምስት ያለው ፍሬ ይባላል፡፡ ከአሥራ ስድስት እስከ መስከረም ሃያ አራት ድረስ መስቀል ተብሎ ይጠራል ይላሉ፡፡ በእነዚያ ቀናት የሚዜመው ዜማ፣ የሚዘመረው ዝማሬ ሁሉ መስቀልን የሚያስታውስ ነው፡፡

በመስከረም አሥር ቀን ተቀጽል ጽጌ እየተባለ የመስቀል በዓል ይከበራል፡፡ ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ተቀጸል ጽጌ ብሎ ዘምሯል፡፡ ያ መዝሙርም የተዘመረው በመስከረም አሥር ቀን ነበር፡፡ ይህ መዝሙርም በመስከረም አሥር ቀን ይዘመራል፡፡ በዓሉ ይታሰባል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ቅዱስ መስቀል ወደ ኢትዮጵያ የገባው በመስከረም አሥር ቀን ነበር፡፡ ይህም በዓል አፄ መስቀል እየተባለ ይከበራል፡፡ ቤተክርስቲያኗ በዚህች ቀን መስቀሉ የገባበትን እያሰበች፣ ከዚያም አስቀድሞ የነበረውን ሥርዓት እንደጠበቀች መስቀሉን ታስባለች፡፡

መስከረም አሥራ ስድስት በንግሥት ኢሌኒ አማካኝነት በጎለጎታ ላይ ቤተ መቅደሱ የታነጸበት ነውና የመስቀል በዓል ይከበራል፡፡ በጎለጎታ ንግሥት ኢሌኒ ባሳነጸችው ቤተ መቅደስ የመስቀል በዓል ከፍ ብሎ ተከብሮበታል፡፡ በመስከረም አሥራ ስድስት ደመራውም የተደመረበት ቀን ነው፡፡ መስከረም አሥራ ሰባት መስቀሉን ለማግኘት ቁፋሮ የተጀመረበት ነውና መስቀሉ ይከበራል፡፡ መስከረም አሥራ ስድስትና አሥራ ሰባት በኢትዮጵያ የመስቀል በዓል በድምቀት የሚከበርበት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በዚህ ብቻ አታበቃም፡፡ ምስጢር እያመሴጠረች፣ በመንፈስ ቅዱስ እየተመራች በዓላትን ታከብራለች እንጂ፡፡ መስከረም ሃያ አንድ ቀን ደግሞ መስቀሉ ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ የደረሰበት ቀን ነውና በታላቅ ድምቀት ታከብረዋለች፡፡ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችም መስቀሉ ወዳረፈበት ሥፍራ ይገሰግሳሉ፡፡ በዚያ በደረሱም ጊዜ በአንድነት ኾነው በግሸን ደብረ ከርቤ አጸድ ሥር ያከብራሉ፡፡ ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ መሄድ ያልቻሉትም በአቅራቢያቸው በምትገኝ የማርያም ቤተክርስቲያን እየሄዱ የመስቀሉን ነገር እየሳቡ ለአምላካቸውም ምሥጋና ያቀርባሉ፡፡

ኢትዮጵያ በዓላትን የምታከብራቸው ሥርዓቱን ጠብቃ ነው ይላሉ ሊቁ፡፡ ሃይማኖቱን ባሕል አድርጋ ትጎናጸፈዋለች፣ በዓላቱንም ሥርዓታቸውን ጠብቃ፣ የራሷን ውበትና ለዛ ሰጥታ ታከብራቸዋለች፡፡ ኢትዮጵያውያን የበዓላቱን አከባበር ሕይወት አድርገውት ይኖራሉ፡፡

ኢትዮጵያ ነጻነቷን ጠብቃ የቆየች በመኾኗ ባሕሏን፣ ሃይማኖቷን እና እሴቷን አላጠፋችም፡፡ ለዚህም ከሌሎች ዓለማት ትለያለች፡፡ ሌሎች በቅኝ ግዛት ጠፍቶባቸዋል፣ የራሳቸውንም አጥተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ግን ትናንት የነበረውን አክብራና አስከብራ አቆይተዋለች፡፡ አባቶች ነጻነታቸውን አስከብረው ለልጆቻቸው ነጻ የኾነች ሀገር አስረክበዋልና፡፡ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ከመስቀል ጋር ጥብቅ ቁርኝት አላቸው፡፡ ከመስቀል ጋር የተያያዘ ስም በማውጣት ያታወቃሉ፡፡ ገብረ መስቀል፣ ኀይለ መስቀል እያሉ፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ስመ መንግሥታቸውን ገብረ መስቀል ያሰኙ ነገሥታት ታይተዋል፡፡ ይሄም ለመስቀሉ ካለ ፍቅር የተነሳ ነው ይላሉ ሊቁ፡፡

አብያተ መቅደሶቻቸውን ሲሠሩ በመስቀል ቅርጽ ያንጻሉ፣ ቤታቸውን በመስቀል ቅርጽ ይሠራሉ፣ ልብሶቻቸውን በመስቀል ያስጌጣሉ፡፡ በዘመቻም ጊዜ ከፈረሶቻቸው አንገት ላይ መስቀል ማድረግ የተለመደ ነው ይላሉ አበው፡፡ መስቀልን አስቀድመው ይዘምታሉ፣ ድል አድርገውም ይመለሳሉ፡፡ መስቀል ባለበት ሁልጊዜም ድል አድራጊነት አለና፡፡

መስቀል ከሚከበርባቸው በዓላት መካከል በመስከረም አሥራ ስድስት ደመራ ይደመራል፣ ችቦ ይበራል፡፡ ሊቀ ሊቃውንት ስመዓኮነ ስለ ችቦ ማብራት ሲነግሩን “ በንግሥት ኢሌኒ ዘመን ደመራው ነበረ፡፡ ችቦው ግን በሰባተኛው ክፍለ ዘመን የተጀመረ ነው፡፡ የባዛንታይን መንግሥት በፋርስ መንግሥት ድል ኾነ፡፡ የፋርስ መንግሥት ኢየሩሳሌምን እና ሌሎች ሀገራትን ያዘ፡፡ በኢየሩሳሌምም በገባ ጊዜ አብያተ መቅደሶችን አጠፋ፤ ኢሌኒ ቤተ መቅደስ ሰርታ ያስቀመጠችውን መስቀልም ወደ ፋርስ ወሰደ፡፡ በኋላም የባዛንታይን መንግሥት የፋርስን መንግሥት መልሶ ድል ነሳው፡፡ ድል በነሳውም ጊዜ መስቀሉን አስመለሰ፡፡ መስቀሉ በተመለሰ ጊዜም ምዕመናን ችቦ እያበሩ መስቀሉን በደስታ ተቀበሉት፡፡ የችቦው ታሪክም ከዚያ ዘመን ይነሳል” ነው ያሉን፡፡

ይህ የችቦና የደመራ ትስስርም በአንድነት ቀጠለ፡፡ የችቦ ማብራት የክብሩም የደስታም መግለጫ ነው፡፡ ይህ ቅዱሱን መስቀል የማክበር ሃይማኖታዊ ሥርዓት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዛሬም እንደቀጠለ ነው፡፡ ቤተክርስቲያኗ በወርኃ መስከረም ብቻ በተለያዩ ቀናት መስቀሉን ታስባለች፣ ስለ መስቀሉ ታስተምራለች፣ በመስቀሉም ፍቅርን፣ ሰላምን፣ አንድነትን እና መዋደድን ትሰብክበታለች፡፡

በመስቀሉ አስተምህሮ የተጣሉትን ታስታርቅበታለች፣ የተለያዩትን አንድ ታደርግበታለች፣ ፍቅርና ሰላምን ታውጅበታለች፡፡ በመስቀሉ እየባረከች ምዕመናንን ትጠብቃለች፡፡ መስቀል ተከብሯል፣ ይከበራል፣ ፍቅር ተበስሯል፣ ጥላቻ ተሰብሯል፣ ጠላት አፍሯል፣ በደል ተደምስሷል፡፡ የፍስሃው ዘመን ቀርቧል፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየመስቀል በዓል በሁመራ ከተማ በድምቀት ተከበረ።
Next article“እንጎሮጎባሽ ”