
ባሕር ዳር: መስከረም 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የመስቀል ደመራ በዓል በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በሁመራ ከተማ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃይማኖቱ ተከታዮችና የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ተከብሯል።
በበዓሉ የመስቀል በዓልን ስናከብር ከመከፋፈል ወጥተን፣ ይልቁንም ስለአንድነት እና ስለፍቅር በማሰብና በመተግበር መኾን እንደሚገባው የሃይማኖት አባቶች አስገንዝበዋል።
በዓሉ እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት እርስ በእርስ የምንደጋገፍበት በመኾኑ የተቸገሩትን በመርዳት፣ የተራቡትን በማብላት እና የተጠሙትን በማጠጣት በአንድነት ልናከብር ይገባል ነው ያሉት።
የሃይማኖት አባቶች በአስተምህሯቸው ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብር ዥንጉርጉርነቱን ሊለውጥ አይችልምና ከአባቶቻችን የተረከብነውን ባሕል፣ እሴትና ትውፊት ወጣቱ ትውልድ ጠብቆ ሊያቆይ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በመስቀል ደመራ በዓል ላይ የተገኙት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪና የሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ከመቸውም ጊዜ በላይ አንድነታችን ልናጠናክር ይገባል ብለዋል። የመስቀል በዓል የእምነት ጽናት የተገለጠበት እንዲሁም አንድነት፣ ፍቅርና መሰባሰብ የታየበት ድንቅ በዓል ነው ሲሉም ተናግረዋል።
እርስ በእርስ ከመገፋፋት እና ከመጠፋፋት ይልቅ በኅብረት ቁመን ለሀገር አንድነት የበኩላችንን ኀላፊነት መወጣት አለብን ነው ያሉት ኮሎኔል ደመቀ።
የዞኑ ሕዝብ ከዓመታት በኋላ መልሶ ያገኘው አማራዊ ማንነቱ የጸና ኾኖ እንዲዘልቅ በአንድነት መቆም እና ለልማቱም መታተር እንደሚገባ አሳስበዋል።
ኮሎኔል ደመቀ በዓሉ የአንድነት፣ የመቻቻልና የመተሳሰብ በዓል እንዲኾንም ተመኝተዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!