
ባሕር ዳር: መስከረም 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ሰማዕታትን ለደም፣ ጻድቃንን ለገዳም፣ ሐዋሪያትን ለስብከት እና ሊቃውንትን ለድርሰት የሚያበቃቸው የመስቀሉ ኃይል እና ፍቅር ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ መከራና እና ፈተና በበዛበት ክርስቲያናዊ ሕይዎት ውስጥ ዲያቢሎስ የተረታው፣ የሰው ዘር ከፍዳ የዳነው፣ ከመከራ ያመለጠው እና ከመላዕክት ጋር በኅብረት የቆመበት ቤዛ፤ ነገረ-መስቀሉ እንደኾነ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያስተምራሉ፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ የክብር እና የመዳን ዘውድን የጫነለት በመስቀሉ ላይ በከፈለው መከራ ነው፡፡ የሰውን ልጅ ለማዳን በቤተልሔም ህጻን፣ በግብጽ ምድረ በዳ ስደተኛ፣ በገዳመ ቆረንጦስ ባህታዊ፣ በእለተ አርብ ሙሽራ፣ በቀራኒዮ በግ እና በሲኦል ወታደር ኾኖ ውድ ዋጋ ከፈለላቸው፡፡ ለዚያም ነው ክርስቲያኖች “መከራው ፈውሳችን፤ ቁስሉ መድኃኒታችን ነው” ሲሉ የሚያምኑት፡፡
ከፍጥረት ተቀዳሚው አዳም እስከ ሙሴ፣ ከሙሴ ልደት እስከ ክርስቶስ መምጣት፣ ከገነት እስከ ግብጽ እና ከግብጽ እስከ ቤተልሔም ያለፉት የመከራ ዘመናት ሲሰሉ 5 ሺህ 500 ገደማ ዓመታት ያስቆጥራሉ ተብሎ ይታመናል፡፡ በእነዚህ ሁሉ ዘመናት የሰው ልጅ መዳን በክርስቶስ መምጣት ላይ የተመሰረተ ነበርና በተስፋ ይጠባበቁ ነበር፡፡
ቀደም ብሎም ነቢያት በትንቢት፤ በኋላም ሐዋሪያት በስብከት የተናገሩለት ኢየሱስ ክርስቶስ ኤልያስን ከኤልዛቤል፤ ኤልሳዕን ከሶሪያውያን ሰውሮ ሲያድን አይተዋልና ፈጽሞ እንደማይተዋቸው እና እንደሚመጣላቸው እርግጠኞች ነበሩ ይባላል፡፡
ኢትዮጵያ በሕገ ልቦና፣ በሕገ ኦሪት እና በሕገ ወንጌል ክርስትቶስን እና ክርስትናን ተቀብላ ከጥንት ጀምራ ታመልክ እንደነበርም ይነገራል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ቤተ ክርስቲያኒቷ በሲኖዶስ ሕግ የኤጲስ ቆጶሳት መንበር ኖሯት እና የተደራጀ ማዕከል ይዛ በይፋ በቤተ ክህነት መሰረት የተቋቋመችው ግን በአራተኛው ምዕተ ዓመት እንደኾነ ታሪክ ይነግረናል፡፡ የአክሱም ሥርወ-መንግሥት ንጉሥ የነበረው ኢዛና ክርስትናን በኢትዮጵያ የተቀበለ የመጀመሪያው ንጉሥ ተደርጎም ይወሰዳል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት የሃይማኖት መሪዎችን ከግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ስታስመጣ እንደቆየች ይነግራል፡፡ ምንም እንኳን ቤተ ክርስቲያኗ የሃይማኖቱን መሪዎች ከውጭ ብታስመጣም የቤተ ክርስቲያኗ ሃይማኖታዊ ትውፊት ሀገረኛ እና በራሷ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን የዳበረ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት እና ትርጓሜ እንዲኖረው ተደርጎ መደራጀቱን የቤተ ክርስቲያኗ ጠቅላይ ቤተ ክህነት 2000 ዓ.ም ላይ ባወጣው ጽሑፉ አስነብቧል፡፡
ጥንታዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በመንፈሳዊ አገልግሎት ሂደት ውስጥ ሥርዓቶቿ ለሀገሪቷ ትሩፋት የኾኑ ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦዎችን አበርክታለች፡፡ የዘመን አቆጣጠር ፍልስፍና፣ ቀመር እና አጠቃቀምን አስተዋውቃለች፡፡ ለዘመን አቆጣጠር ተፈጥሯዊ ባህሪያትን አላብሳለች፡፡ ከሐሳበ ድሜጥሮስ፣ ከአቡሻከር፣ ከሐሳበ ቢዘን እና ከሐሳበ ጉንዳጉንዲ የተገኙ ፍልስፍናዎችን አፍልቃ አስርጻለች ይላሉ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አበርክቶዋን ሲያወሱ፡፡
መንፈሳዊቷ እና ጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን ቋንቋን አርቅቃ ብራና ፍቃ፤ ቀለም በጥብጣ ፊደላትን ቀርጻ፤ ታሪክ ሰንዳ እና ሰዋሰውን አዋዳ ትምህርት በኢትዮጵያ እንዲስፋፋ ያደረገችው አስተዋጽኦ ዘመን ተሻጋሪ አበርክቶዋ ነው ይባላል፡፡ ማንበብ እና መጻፍን በማሠልጠን ሀገሪቷ ጥንታዊ ድርሳናት እና ጸሐፍት እንዲኖሯት አድርጋለች፡፡ ዜማና የዜማ መሳሪያ፣ ላሊበላን የመሰለ ኪነ-ሕንፃ፣ የስዕል ዘይቤ፣ ሕግ፣ አሥተዳደር እና የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎቿ ለአበርክቶዋ ህያው አሻራ እና ምልክት ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡
ከላይ ከተነሱት የቤተ ክርስቲያኗ ሀገራዊ አሻራዎች በተጨማሪ ዋና ዋና በዓላቶቿ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት ያላቸው፤ የኢየሱስ ክርስቶስን ምድራዊ እና ሰማያዊ ፈለጎች የተከተሉ እንደኾኑ ይነገራል፡፡ የቤተ ክርስቲያኗ ሁሉም በዓላት ሃይማኖታዊ እና መንፈሳዊ መሰረት ያላቸው እንደኸኑ ይወሳል፡፡
ዲያቆን ብርሃኑ አድማሱ 1999 ዓ.ም ላይ “በዓላት” በሚል ርእስ ባሳተሙት መጽሐፋቸው የቤተ ክርስቲያኗ ክብረ በዓላት ዓበይት እና ንዑሳን ተብለው ይከፈላሉ ይሉናል፡፡ ዘጠኝ ዓበይት እና ዘጠኝ ንዑሳን ክብረ በዓላት ያሏት ቤተ ክርስቲያኗ መሰረታቸው ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ቢኾንም በርካቶቹ በዓላቶቿ ሕዝባዊ እና ብሔራዊ በዓላት ጭምር እየኾኑ መጥተዋል፡፡ ከእነዚህ በዓላት መካከል መስከረም 16 እና 17 የሚከበረው እና የአደባባይ ክብረ በዓል የኾነው የመስቀል ደመራ በዓል አንዱ ነው፡፡
ምንም እንኳን የመስቀል ደመራ በዓል በቤተ ክርስቲያኗ ሕግ እና ሥርዓት መሰረት ከዘጠኙ ንዑሳን በዓላት መካከል አንዱ ቢኾንም ድምቀቱ እና ተወዳጅነቱ ከዓበይት በዓላት ጋር የሚስተካከል እየኾነ መጥቷል ይባላል፡፡ የመስቀል ደመራ በዓል ሃይማኖታዊ ብቻ ሳይኾን ብሔራዊ ከሚባሉት ከልደት፣ ከጥምቀት፣ ከስቅለት እና ከትንሳዔ በዓላት ተራ የሚመደብ ክብረ በዓል ኾኗል፡፡
በቀራኒዮ አደባባይ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ከመተከሉ በፊት የነበሩ ጥንታዊ ኢትዮጵያዊያን ክርስቲያኖች በተስፋ እና በእምነት የመስቀሉን ነገር እያስታወሱ እራሳቸውን ለመከራ ያዘጋጁ ነበር ይላሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መምህር የኾኑት ሊቀ ሊቃውንት ስማዕኮነ መላክ፡፡
ክርስቲያኖች ነገረ መስቀሉን ሲያከብሩ ውለታውን እያስታወሱ ብዙ ዋጋ ይከፍላሉ፤ እንደ አብርሃም መርዓዊ ጫጉላቸውን፣ እንደ ዓጼ ካሌብ ቤተ መንግሥታቸውን እና እንደ አባ ጳውሊ ትዳራቸውን ይገፋሉ፡፡ ለዚያም ነው “በመስቀሉ ሁሉን አስታረቀ” የሚሉት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፡፡
ኢትዮጵያዊያን ዛሬ ላይ ኾነው የመስቀል ደመራውን በዓል ሲያከብሩም ሰለሀገር አንድነት ልዩነቶቻቸውን ማጥበብ፣ ስለሃይማኖታቸው ፍቅርንና ትህትናን ጫማቸው ማድረግ፣ ስለወገኖቻቸው ርህራሄን ማድረግ እና እራስ ወዳድነትን ማሸነፍ ግድ ይላቸዋል፡፡
ለብዙ ዘመናት ከጠፋው እና በክፉዎች ከተቀበረው መስቀል መገኘት የምንማረውም ትናንት የጠፋውን ኢትዮጵያዊ አንድነት፣ ፍቅር እና ጽናት አብዝቶ መፈለግን ሊኾን ይገባል፡፡
በታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!