
ባሕርዳር፡ መስከረም 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የክርስቶስ መስቀል ለ300 ዓመታት ያህል ተቀብሮ ከቆየበት በደመራ ጢስ ጥቆማ አማካይነት የተገኘበትን ቀን ለማሰብ የደመራ በዓል መስከረም 17 ተከብሮ ይውላል።
በጎንደርና አካባቢው ደመራ የሚለኮሰው በዚህ ቀን ነው። በዓሉም “አፄ ደመራ” በመባል ይጠራል። ይህ ስያሜ የተሰጠው በንጉሠ ነገሥቱ ቤተ መንግሥት ፊት ንጉሱ በተገኙበት በአደባባይ ይከበር ስለነበር ነው። የንጉሠ ነገሥቱ ደመራ እንደማለት እንደኾነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ጃንተከል ዋርካ ከመሥቀል በዓል ባለፈ ዐዋጅ የሚነገርበት፣ ሹም ሽር የሚፈጸምበት፣ ለወንጀለኞችም ፍርድ የሚሰጥበት፣ ሊቃውንቱ ጉባኤ የሚያካሂዱበት፣ ለነገሥታቱ ደጅ የሚጠኑበት፣ ባላባቶች ተሰብስበው የተለያዩ ጉዳዮችን የሚመክሩበት ነበር። ባጠቃላይ ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች የሚካሄዱበት ስፍራ ነበር። ከ1966 ዓ.ም ጀምሮ የመስቀል በዓል “መስቀል አደባባይ” እየተባለ ከሚጠራው አካባቢ እንዲከበር ተደርጓል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በጎንደር የአራቱ ጉባዔያት መምህርና የጎንደር መንበረ መንግሥት መድሃኒት ዓለም አሥተዳዳሪ ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ አጼ ደመራ “አጼ መስቀል” እየተባለም እንደሚጠራም ገልጸዋል። ክርስቶስ ንጉሠ ነገሥትነቱን እና ሊቀ ካህንነቱን የገለጸው በመስቀሉ ላይ በመኾኑ የኢትዮጵያ ነገሥታትም የመሥቀል በዓልን ከጥንት ጀምረው እያስከበሩና እያከበሩ መምጣታቸውን ገልጸዋል።
ይህ የክርስቶስ ንጉሠ ነገሥትነቱ እና ሊቀ ካህንነቱ የተገለጸበት ደመራ የሚደመረው ደግሞ በንጉሠ ነገሥቱ አዛዥነት በመኾኑ አጼ ደመራ ወይም አጼ መስቀል የሚለውን ስያሜ እንዳገኘ አንስተዋል፡፡ አጼ ደመራ ጎንደር ላይ ይጉላ እንጅ ስያሜው በሌሎች አካባቢዎችም መኖሩን ነው ሊቀ ሊቃውንቱ የገለጹት። የቀድሞው የደመራ ቦታ በመጥበቡ ምክንያት አሁን ላይ “መሥቀል አደባባይ” እየተባለ በሚጠራው አካባቢ እንዲከበር መደረጉንም ነግረውናል።
የመስቀል በዓል ደመራው ከሚደመርበት መስከረም 16 ጀምሮ የበዓሉ አከባበር በየመንደሩ ባሉ ልጆች የሆያ ሆዬ ጭፈራ እና በሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ይደምቃል። እስከ በዓሉ ዕለት ድረስም ይቀጥላል። መስከረም 17 ንጋት ላይ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ምዕመናን እንዲሁም የከተማው ተወካይ በደመራው ስፍራ ይገኛሉ። ጸሎትና ምህላ ይደርሳል፤ ሊቃውንቱና የሰንበት ትምህርት ቤቶች ዝማሬ ያቀርባሉ።
በመቀጠል ዕለቱን በተመለከተ የወንጌል ትምህርት ተሰጥቶ ሊቀ ጳጳሱ ደመራውን ይባርካሉ። የከተማው ከንቲባ ደግሞ የንጉሰ ነገሥቱን ሚና ወስደው የተባረከውን ደመራ ከሃይማኖት አባቶች ጋር በመኾን በችቦ ይለኩሳሉ። የተሰበሰበው ሰው ምስጋና ያቀርባል። ደመራው አመድ እስኪኾን ድረስ ከተቃጠለ በኋላ የተጸለየበትንና የተባረከውን አመድ እና ትርኳሽ ሕዝቡ ወደ ቤቱ ይዞ ይሔዳል። በዓሉ ሳይበረዝ በዚህ መንገድ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ በድምቀት እየተከበረ እንደሚገኝም ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ነግረውናል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!