
ባሕር ዳር: መስከረም 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ዓለማት ሁሉ የሚፈልጉትን እርሷ ይዘዋለች፣ ዓለማት ሁሉ የሚመኙትን እርሷ አሳርፈዋለች፣ በኀይሉ ትጠበቅበታለች፣ በብርሃኑ ትረማመድበታለች፣ በረከትና ረድኤትን ትቀበልበታለች፣ ኀይልና ብርታትን ታገኝበታለች፡፡ አሳዳጆቿን ሁሉ ድል ትመታበታለች፡፡
የተመረጠች፣ ለምስክርነት የተዘጋጀች፣ ክብሩንና ሞገሱን ለመግለጽ የተመቻቸች ናትና አብዝቶ ወደዳት፣ ለምድር የሰጠውን ታላቁን ነገር ሁሉ ለእርሷ ሰጣት፣ የተወደደውን ሁሉ አደረገላት፣ የማያልፈው ቃል ኪዳኑን አተመባት፣ በየዘመናቱ ከማይቋረጠው የጥፋት ወጀብ ባረካት፣ ጨለማውን በብርሃን እየለወጠ ክፉ ዘመናትን አሻገራት፣ ለማዕበል መሻገሪያ ድልድይ እየኾነ አሳለፋት፡፡ ከጥፋት መትረፊያ መርከብ እየኾነ አተረፋት፡፡
ለእርሷ በሲና ተራራ ላይ ለሙሴ የሰጠውን ጽላተ ሙሴ ጽዮንን፣ በድንግልና የወደለችው እናቱን፣ በቀራንዮ የተሰቀለበት መስቀሉን፣ በፈቃዱ የገደማቸው ገዳማትን፣ በደሙ የዋጃቸውን አብያተ ክርስቲያናትን፣ ጸጋን የሰጣቸውን ጻድቃንን፣ ቅጠል ለብሰው፣ ጤዛ ልሰው፣ ድንጋይ ተንተርሰው፣ ድምጸ አራዊትን ታግሰው የሚኖሩ ባሕታውያንን፣ ሃይማኖትን የሚያስተምሩ ካህናትን፣ ዲያቆናትን፣ መነኮሳትን፣ ሕዝብ የሚባርኩ መነኮሳትን ሰጣት፤ አብዝቶም ጠበቃት ይላሉ ፡፡
ኢትዮጵያ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ፍቅሩን የገለጸበት፣ አዳምና ልጆቹን ከባርነት ነጻ ያወጣበት፣ በተስፋ ለሚጠብቁት ሁሉ መድኃኒትን የሰጠበት መስቀሉ ያረፈባት፣ ጠብቆቱ፣ በረከቱና ረድኤቱ የማይለያት ሀገር ናት፡፡ እርሷ በሰርክ ጸሎትና ምሕላ ይደረግባታል፣ የአምላክ ስም ይጠራባታል፣ ፍቅርና ሰላም ይኾን ዘንድ ምሕላ ይደረስባታል፡፡ ኢትዮጵያ ሃይማኖትን፣ ታሪክንና እሴትን ስትጠብቅ ኖራለች፣ ክብር ለሚሰጠውም ክብርን ትሰጣለች፡፡
ኢሌኒ ንግሥት መስቀሉን ባገኘች ጊዜ በጎለጎታ ያማረ ቤተ መቅደስ አሠርታ አስቀመጠችው፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ ስጋ የተቆረሰበት፣ ደም የፈሰሰበት ቅዱስ መስቀል ህሙማንን እየፈወሳቸው፣ ለምጻሞችን እያነጻቸው፣ ብርሃን ለሌላቸው ብርሃንን እየሰጣቸው በዚያው ኖረ፡፡ ዘመናት ተከታተሉ፡፡ የፋርስ ንጉሥ ኀያል ኾነ፡፡ ወደ ኢየሩሳሌምም ዘመተ፡፡ ኢየሩሳሌምን መከራ አበዛባት፡፡ አብያተ ክርስቲያናትን አቃጣላቸው፣ ምዕመናኑን ሰየፋቸው፣ የመከራና የበደል ጽዋ አስጎነጫቸው፡፡
የፋርሱም ንጉሥ በቤተ መቅደስ የነበረውን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ወደ ሀገሩ ወሰደው፡፡ በሀገሩም አስቀመጠው፡፡ ሌላ ዘመንም መጣ፡፡ ንጉሥ ሕርቃልም ተነሳ፡፡ የፋርሱንም ንጉሥ ድል መትቶ ግማደ መስቀሉን ወደ ሥፍራው መለሰው ይላሉ፡፡
አሁንም ዘመናት አለፉ፤ ሌላ ዘመን አልፎ ሌላ ዘመን መጣ፡፡ ኀያላን መንግሥታት በየቦታው ተነሱ፡፡ መስቀሉ ለእኔ ይገባኛል የሚሉት በረከቱ፡፡ መስቀሉ ይገባኛል በሚል ምክንያት አስፈሪ ነገር ሊመጣ ኾነ፡፡ የሃይማኖት አባቶችም ነገሩ ይበርድ ዘንድ ሽማግሌ ኾነው አስታረቁ፡፡ እስክንድሪያ የጌታ ግማደ መስቀሉን አገኘች፡፡ በዚያም ተቀመጠ፡፡ የእስክንድሪያ ምዕመናን ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየተመናመነ ነበር፡፡ በዚሕም ምክንያት መከራ በረታባቸው፣ የግፍ ጽዋ በዛባቸው፡፡ የግብጽ ሹማምንት ምዕመናኑን አሳደዷቸው፣ ሕዝብ የሚባርኩትን፣ ስብሐተ እግዚአብሔርን የሚያደርሱትን ጳጳሳቱን አሠሯቸው፡፡
በዚያ ዘመን በኢትዮጵያ ንጉሥ ዳዉት ነግሠው ኢትዮጵያን ያሥተዳድሩ ነበር፡፡ እንደ አበው ገለጻ መከራ የበዛባቸው የግብጽ ምዕመናን በኢትዮጵያ ነግሠው ሲገዙ ለነበሩት ለአፄ ዳዊት መልእክት ላኩባቸው፡፡ ተጨንቀናልና ድረስልን ብለው፡፡ አፄ ዳዊትም ይሄን በሰሙ ጊዜ መኳንንቱን፣ መሳፍንቱን፣ መነኮሳቱን፣ ካህናቱንና የጦር አበጋዞችን ጉባኤ ጠሩ፡፡ ስለ ግብጽ ክርስቲያኖችም መከሩ፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በጎንደር የአራቱ ጉባያት መምህርና የጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አሥተዳደሪ ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ ንጉሡ የክርስቲያኖችን ስቃይ በሰሙ ጊዜ ለግብጹ ንጉሥ ሊቀ ጳጳሳቱን እንዲፈታ፣ በክርስቲያኖች ላይ የሚያደርሰውን በደልም እንዲያቆም መልእክት ላኩበት፡፡ እምቢ ካለ ግን ዓባይን እንደሚገድቡትና ግብጽን እንደሚቀጧት ነገሯቸው ይላሉ፡፡
ግብጽ ያለ ዓባይ ምንም ናትና ይሄን የሰማው የግብጹ ንጉሥ አብዝቶ ደነገጠ፡፡ የተባለውን ለማድረግም ተስማማ፡፡ ጳጳሳቱን ፈታቸው፡፡ ክርስቲያኖችንም አከበራቸው፣ ስቃይና መከራውን ተወላቸው፡፡ በሰላምና በፍቅር እንዲኖርም አዋጅ አስነገረላቸው፡፡ ለአፄ ዳዊትም የእጅ መንሻ ላከላቸው፡፡ የግብጽ ክርስቲያኖችም በቁጥራቸው ትንሾች ስለነበሩ መስቀሉን ይወስዱብናል ብለው ሰጉ፡፡ መስቀሉ ወደ ኢትዮጵያ ሄዶ እንዲቀመጥ ለንጉሡ ዳዊት ሰጧቸው ይላሉ አበው፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ንጉሡ ዳዊት ዓባይን ልገድብ ነው በማለታቸው ዓባይን ይተውልን የእጅ መንሻ እንስጠዎት ተባሉ፡፡ እሳቸውም ከግማደ መስቀሉ ውጭ የትኛውንም የእጅ መንሻ እንደማይቀበሉ ነገሯቸው፡፡ ከብዙ ምክር በኋላ መስቀሉን ለአፄ ዳዊት ሰጧቸው ይላሉ፡፡
አፄ ዳዊት ዓለማት ሁሉ የሚፈልጉትን መስቀሉን ተቀበሉ፡፡ ነገር ግን ንጉሡ ዳዊት መስቀሉን ይዘው ወደ ዙፋናቸው ሳይመለሱ በስናር አለፉ፡፡ ንጉሡ ባለፉ ጊዜ የታላቁ ንጉሥ ልጅ ሊቁ ንጉሥ አፄ ዘርዓያቆብ በአባታቸው ዙፋን ተቀመጡ፡፡ በነገሡም ጊዜ ወደ ስናር ተጉዘው ግማደ መስቀሉን እና ሌሎች የከበሩ ንዋየ ቅድሳትን ይዘው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ፡፡
ሊቁ እንደነገሩን መስቀሉ ወደ ኢትዮጵያ የገባበት ጊዜም መስከረም 10 ቀን ነበር፡፡ ይህችም ቀን ተቀጸል ጽጌ ተብላ ትከበራለች፡፡ ይህ ሥርዓት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዘንድ ዛሬም እንደከበረ ቀጥሏል፡፡ አጼ ዘርዓያቆብም መስቀሉን በተቀበሉ ጊዜ መስቀሌን በመስቀለኛ ቦታ አስቀምጥ ተብለው በራዕይ ተነገራቸው፡፡ ንጉሡም ሠራዊታቸውን አስከትለው፣ ሊቃውንቱን ይዘው፣ መስቀሉን አሸክመው መስቀሉን በመስቀለኛ ቦታ ለማኖር የኢትዮጵያን አውራጃዎች አካለሉ፡፡ መስቀለኛውን ቦታ ግን በቀላሉ ማግኘት አልተቻላቸውም፡፡ ሱባኤም ገቡ፡፡ ፈጣሪም የግሽን ተራራን አሳያቸው፡፡ በታያቸውም ጊዜ ሠራዊታቸውን አስከትለው፣ በሊቃውንቱ ተከበው በግሸን አምባ በመስቀለኛው ሥፍራ መስቀሉን አኖሩት ይላሉ፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በባሕርዳር ሀገረ ስብከት የአራቱ ጉባያት መምህር ሊቀ ሊቃውንት ስመዓኮነ መልአክ መስቀል በኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ እየከበረ ቢመጣም አምሮና ደምቆ መከበር የጀመረው ግን መስቀሉ ወደ ኢትዮጰያ ከገባ ጊዜ ጀምሮ ነው ይላሉ፡፡
እንደ ሊቀ ሊቃውንት ስመዓኮነ መስቀሉ የተገኘው በመጋቢት አሥር ቀን ነው፡፡ በመጋቢት አሥር ቀን የመስቀል በዓል በቤተ ክርስቲያን ይከበራል፡፡ በዓሉ መስከረም የመጣበትን ምክንያት ሲያስረዱም በመጋቢት ታላቁ ዓብይ ጾም የሚጾምበት ወቅት ነው፡፡ በዚህም ጊዜ ሱባኤ የሚያዝበት ነውና በዓላትን እንደሌላው ጊዜ አድምቆ ለማክበር አይቻልም፡፡ በሌላ በኩልም ኢሌኒ ለመስቀሉ ቤተ መቅደስ አስርታ ቤተ መቅደሱ የተከበረበት ስለኾነ በዓሉ ወደ መስከረም መጥቶ በታላቅ ሃይማኖታዊ ሥርዓት እንዲከበር መደረጉን ነግረውናል፡፡ መጋቢት አሥርም በዓሉ በቤተክርስቲያን ይከበራል፡፡
ኢትዮጵያ መስቀሉን ይዛለች፡፡ ሃይማኖትን፣ እሴትን እና ታሪክን በመጠበቅ ተክናለች እና በመስቀሉ አከባበር ከሌሎች ዓለማት ትለያለች፡፡ ኢትዮጵያ በመስቀሉ ትጠበቅበታለች፣ ከክፉ መከራና መቅሰፍትም ትድንበታለች፣ ጠላቶቿንም ድል ትመታበታለች ይላሉ አበው፡፡ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ሕይወታቸው ሁሉ ከመስቀል ጋር የተያያዘ ነው፡፡ መስቀልን በአንገታቸው በጥቁር ክር ያስሩታል፣ በግንባራቸው ይነቀሱታል፣ በልብሶቻቸው ያስጠልፉታል፣ ሊጥ አቡክተው ወደ እቃው ሲከቱ ሊጡን በመስቀሉ ይባርኩታል፣ ሁሉ ነገራቸው ከመስቀል ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ካህናቱም ምዕመናንን በመስቀል ይባርኳቸዋል፣ ምድርን በመስቀል ይባርኳታል፤ ይቀድሷታል፣ መስቀል የክርስቲያኖች መገለጫ፣ የክርስቲያኖች መለያም ነው፡፡
መስቀል በኢትዮጵያ ከመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሰላማ ዘመን ጀምሮ ይከበር እንደነበር ነግረውናል፡፡ የመስቀሉ ክብረ በዓል ከዚያ ዘመን ጀምሮ የመጣ ነው፡፡ በየዘመናቱ የነገሡ ነገሥታትም ከመኳንንቶቻቸው፣ ከመሳፍንቶቻቸው፣ ከጦር አበጋዞቻው ጋር እየኾኑ፣ ከጳጳሱ፣ ከካህናቱና ከምዕመናኑ ጋር ኾነው በጋራ መስቀልን ሲያከብሩት ኖረዋል፡፡
መስቀል በደረሰ ጊዜ በአደባባይ ተገኝተው ሥርዓቱን ይካፈላሉ፣ ለአምላካቸውም ምሥጋናና ውዳሴ ያቀርባሉ፡፡ ደመራው በተለኮሰም ጊዜ አምላካቸው በረከትን እና ረድኤትን እንዲሰጣቸው እየተመኙ በታላቅ አጀብ ወደ ቤተ መንግሥታቸው ይመለሳሉ፡፡
የመስቀል ክብረ በዓል በኢትዮጵያ ሥርዓቱን እንደጠበቀ ዛሬም ይከበራል፤ ዛሬም ነገረ መስቀሉ እየተነሳ ኢየሱስ ክርስቶስ ይመሠገናል፡፡ እነሆ ዛሬም እየተመሠገነ ነው፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!