
በደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ የተፈጸመውን እገታ ለማውገዝ የተካሄዱ ሠላማዊ ሰልፎች በሠላም መጠናቀቃቸውን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
የእገታ ድርጊቱን እና በጉዳዩ ላይ የመንግሥትን ዝምታ በማውገዝ በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች ሠላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል፡፡ ተማሪዎቹ ተለቅቀው ከወላጆቻቸው ጋር እንዲገናኙ፣ ኢ-ሰብዓዊ እና ከሞራል ያፈነገጠውን ድርጊት የፈጸሙት አካላትም ተጠያቂ እንዲሆኑ በሠልፎቹ ተጠይቋል፡፡
በኮሚሽኑ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር መሠረት ደባልቄ ለአብመድ እንደገለጹት በሁሉም አካባቢዎች የተካሄዱ ሰልፎች በሠላማዊ መንገድ ተጠናቅቀዋል፡፡ የየአካባቢው ማኅበረሰብ፣ ወጣቶች እና የጸጥታ አባላት ሠላማዊ ሰልፎች በሠላማዊ መንግድ እንዲጠናቀቁ ላደረጉት ጥረት ኮሚሽኑ አመሥግኗል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ