የመስቀል በዓልና ስለት!

33

ባሕርዳር፡ መስከረም 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የመስቀል ደመራ በዓል በኢትዮጵያ የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በአደባባይ ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ ነው። ከአደባባይ ክብረ በዓሉ ማግስት ወይም በኋላ ሰዎች በየመኖሪያ አካባቢያቸው እየተሰባሰቡ በዓሉን በጋራ ያከብራሉ።

በዓሉ በተለመደው ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ ሥርዓት ተከብሮ ሲጠናቀቅ “የዓመት ሰው ይበለን” ተብሎ በአባቶች ምርቃት እና በስለት ይጠናቀቃል። የልብ መሻት ሁሉ እንዲሳካ በአደባባይ ተነግሮ እና ይሳከልዎ ተብሎም ይጸለያል።

በመስቀል በዓል ቀን በሚኖር ልዩ ዝግጅት ስለት በስፋት የሚከናወን እና የተለመደ ባህል ነው። የስለት ሃይማኖታዊ መሰረት መሥቀሉ ከተቀበረበት ተራራ ተቆፎሮ እንዲወጣ ካደረገችው ንግሥት ኢሌኒ ጋር የተገናኘ ታሪክ አለው። ንግሥት ኢሌኒ የኢየሱስ ክርስቶስ መሥቀል በኢየሩሳሌም ተቀብሮ ለብዙ ዘመናት መኖሩን ትሰማ ነበርና ይህንን ለማውጣት ስለት ተስላለች።

ንግስት እሌኒ “ቁንስጣ” ከተባለ አሕዛባዊ ንጉሥ የወለደችው ቆስጠንጢኖስ የተባለ ልጅ ነበራትና “ልጄ ክርስቲያን ቢኾንልኝ ወደ ኢየሩሳሌም ሄጀ የክርስቶስን መሥቀል ከተቀበረበት አስቆፍሬ አወጣዋለሁ” በማለት ነበር የተሳለች። ይህም ተሳክቶላት መስቀሉን ለማውጣት መቻሏን ታሪክ ያስረዳል። የመስቀል ዕለት የሚደረገው ስለት ሃይማኖታዊ መሰረቱም ይሄው ነው።

አሁንም ዓመቱ የፍቅር እና የጤና ኾኖ እንዲያልፍ፤ ሀገርና ሕዝብ ሰላም እንዲከርም፤ በማሳ ላይ ያለው ሰብል በበረከት ወደ ቤት እንዲገባ እንዲሁም ሌሎች መሰል መልካም ምኞት እንዲሳኩ በዓሉን ለማክበር በተሰበሰቡ ሰዎች መካከል ተስለው ይመረቃሉ። የዓመት ውጥን እንዲሳካ፣ እቅድም በተግባር እንዲከናወን፣ እንደግለሰብ ወይም እንደሀገር የገጠመ ችግር መፍትሔ እንዲያገኝ ሁሉም የልቡን መሻት እየተናገረ ወይም በልቡ ይዞ ለፈጣሪው ብቻ እየተወ ስለት ይሳላል።

የአማራ ሕዝብ ሽምግልና ሥርዓት ማኅበር ፕሬዚዳንት እና የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ባሕር ዳር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚዳንት ሊቀ ኅሩያን በላይ መኮንን “ስለት” ማለት ወደ ፈጣሪ መለመን ወይም ጸሎት ማቅረብ ማለት እንደኾነ ይገልጻሉ።

ሰዎች የራሳቸው ወይም የጓደኛቸው መልካም ሃሳብ እንዲሳካ ወደ ፈጣሪ ጸሎት የሚያቀርቡበት እና ምኞታቸው ከተሳካ ደግሞ ለቀጣዩ ዓመት የአብሮነት የበዓል ዝግጅት የሚችሉትን የጥሬ ገንዘብ ወይም የአይነት አበርክቶ የሚያቀርቡበት ሂደት ነው ሲሉም ሊቀ ህሩያን በላይ ተናግረዋል።

ስለት ከሃይማኖታዊ ይዘትና ፋይዳው በተጨማሪም ጉልህ ማኅበራዊ ጠቀሜታ እንዳለውም ገልጸዋል። በስለት በሚሰበሰብ ገንዘብ የአንድ አካባቢ ሰዎች በጠበቀ ማኅበራዊ አንድነት ተሰባስበው በዓሉን ለማሳለፍ እንደሚያግዝም ሊቀ ህሩያን ተናግረዋል።

“የዛሬ ዓመት ሁላችንንም ሰብስቦ በሰላም ቢያደርሰን…” ተብሎ በሰዎች ፊት ቃል የሚገባ የስጦታ አይነት አንዱ ለሌላው ያለውን መተሳሰብ እና መልካም ምኞት የሚገልጽበት መንገድ እንደኾነ ሊቀ ህሩያን በላይ አብራርተዋል። ይህም የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት ይዞት የቆዩትን የአንድነት እና የመተሳሰብ እሴት የበለጠ የሚያጎለብት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ሊቀ ህሩያን በላይ መኮንን ስለት አንድነትን፣ መልካም ምኞትን እና ጠንካራ ማኅበራዊ ግንኙነትን ለመመስረት የሚያገለግል ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ እሴት እንደኾነ ገልጸዋል።

በስለት መልኩ ቃል የሚገባው የጥሬ ገንዘብ ወይም የአይነት ስጦታ የግለሰቡን አቅም የሚመጥን መኾን እንዳለበትም ሊቀ ህሩያን በላይ መኮንን መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጥንታዊው ነገረ መስቀል በኢትዮጵያ”
Next articleግማደ መስቀሉ ያረፈባት፣ ጥበቃው የማይለያት”