
ባሕርዳር፡ መስከረም 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሩፊኖስ እና ሶቅራጥስ የተባሉት ሁለት የዓለም ታሪክ ጸሐፊዎች ክርስትናን በዓለም ካስፋፋት የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋሪያት መካከል ማቴዎስ፣ ናትናኤል፣ በርተሎሜዎስ እና ቶማስ በኢትዮጵያ የተለያዩ አውራጃዎች እና አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው ወንጌል መስበካቸውን ይናገራሉ፡፡ ይህንንም መነሻ በማድረግ ከዘመነ ሐዋሪያት ጀምሮ ክርስትና በኢትዮጵያ መሰረቱን እንደጣለ ይነገራል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተመሰረተችው በ34 ዓ.ም መኾኑን ታላቁን የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊ እና ሊቅ አውሳብዮስን ጠቅሳ ትገልጻለች፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቷ ከዚያም በፊት እግዚአብሔርን በማመን ጸንታ መቆየቷን እና ክርስትና በመላው ዓለም ሲስፋፋም ቀድመው ከተቀበሉት ሀገራት መካከል አንዷ መኾኗን ትናገራለች፡፡
በዓለ መስቀል እና ደመራ ኢየሱስ ክርስቶስ ከተሰቀለበት መስቀል ጋር ተያይዞ የሚከበር በዓል ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ቤዛ የኾነ ደሙን ያፈሰሰበት እና ቅዱስ ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በፈቃዱ የለየበት ቅዱስ መስቀል እንደኾነ ይታመናል፡፡ በጊዜውም መስቀሉ በቅድስቲቷ ምድር ሀገረ እስራኤል ውስጥ በርካታ ተዓምራትን ይሠራ እንደነበር ቤተ ክርስቲያኗ ታስተምራለች፡፡ የመስቀሉን ተዓምራት ተከትሎም ደብዛው እንዲጠፋ የሚፈልጉ ወገኖች ተነስተው ነበር ይባላል፡፡
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የሰቀሉት የአይሁድ ወገኖች ምንም እንኳን ክርስቶስ ኢየሱስ ከመቃብር ቢነሳባቸውም ክርስቶስን እንደ ቀበሩት ሁሉ መስቀሉም ደብዛው እንዲጠፋ ቀብረውት እንደነበር ይነገራል፡፡ ቅዱስ መስቀሉ በተቀበረበት ቦታም አይሁዶች ቆሻሻው እየደፉ ተራራ እስከሚያክል ድረስ ያከማቹበት ነበር አሉ፡፡ ነገር ግን በ70 ዓ.ም ሮማዊያን አይሁዳዊያንን ከገዛ ሀገራቸው ማባረራቸውን ተከትሎ ለ300 ዓመታት ያክል መስቀሉ የተቀበረበት ቦታ ደብዛው ጠፍቶ እንደቆየ ይታመናል፡፡
ከ300 ዓመታት በላይ ደብዛው ጠፍቶ የነበረውን የክርስቶስ መስቀል በንግሥት ኢሌኒ መንፈሳዊ ተጋድሎ ከተቀበረበት መገኘቱን ተከትሎ የበዓሉ መከበር ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል ይላሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተማሪ የኾኑት መምህር ማዕበል ፈጠነ፡፡ መምህሩ እንደሚሉት በሀገሪቷ የዘመን ቀመር በጥቢ ወቅት በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር በወርሃ መስከረም አራት ጊዜያት በሚከበረው የመስቀል በዓል ውስጥ ንግሥት ኢሌኒ ዋና ተዋናይ ተደርጋ ትወሰዳለች፡፡
ኢትዮጵያ የመስቀልን በዓል በየዓመቱ መስከረም 10 ቀን በቤተ ክርስቲያን፣ መስከረም 16 እና 17 ደግሞ በአደባበይ ታብረዋለች። በየዓመቱ መስከረም 21 ቀን ደግሞ በግሸን ደብረ ከርቤ ዓመታዊ የንግስ በዓል ሆኖ ይከበራል፡፡ የመስቀል በዓል ከሌሎቹ የዓለም ሀገራት በተለየ መልኩ በኢትዮጵያ ደምቆ የሚከበርበት የራሱ የኾነ ልዩ ምክንያት እንዳለውም የቤተ ክርስቲያን አበው አባቶች ያስተምራሉ፡፡
የክርስቶስ ኢየሱስ ግማደ መስቀል በንግሥት ኢሌኒ ብርቱ ተጋድሎ ከተገኘ በኋላ ልጇ ቆስጠንጢኖስ መስቀሉ የሚቀመጥበትን ታላቅ ቤተ መቅደስ በእየሩሳሌም አስገንብቶ መስከረም 17 ቀን በደማቅ ክብረ በዓል እንዲገባ አደረገው፡፡ መስቀሉ በቤተ መቅደሱ ውስጥም ለብዙ ዘመናት በካህናት እየተጠበቀ እንዲቀመጥም አድርጎት ነበር ይባላል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን “ትንሳዔ” በሚል ርእስ 1983 ዓ.ም ላይ ባሳተመችው ቁጥር 144 መጽሔት ላይ እንዳስነበበችው ከመስቀሉ መገኘት በኋላ የመስቀሉ ታላቅነት በመላው ዓለም ስለታወቀ የፋርስ ንጉስ መስቀሉን ማርኮ ወደ ፋርስ አሻገረው፡፡
ምንም እንኳን የእየሩሳሌም ምዕመናን የሮማ ንጉሥን እርዳታ በመጠየቅ ቅዱስ መስቀሉ ዳግም ወደ እየሩሳሌም እንደሚመለስ ቢያደርጉም ታላላቅ ነገሥታት መስቀሉን እኔ እወስድ እኔ እወስድ በማለት ጦርነት ፈጠሩ፡፡ የቆስጠንጥኒያ፣ የአንጾኪያ፣ የኤፌሶን፣ የአርመንያ፣ የግሪክ እና የእስክንድሪያ ሃይማኖት መሪዎች ግፊት አድርገው መስቀሉን ከአራት ከፋፍለው በእጣ ወስደው በየሀገራቸው አስቀመጡት፡፡ የክርስቶስ ቀኝ እጅ ያረፈበት የመስቀሉ ክፍል ለአፍሪካ ደርሶ ስለነበር በግብጽ የሚገኘው የእስክንዲሪያ ፓትርያርክ ተረክበው በማርቆስ ቤተ መቅደስ ውስጥ በክብር አስቀመጡት፡፡
የኢትዮጵያ ጥንታዊ ነገሥታት ቅዱስ መስቀሉ በንግስት ኢሌኒ ብርታት መገኘቱን እና የአፍሪካ ድርሻ የሆነው ግማደ መስቀል በግብጽ እስክንድሪያ እንደሚገኝ ይሰሙ ነበር፡፡ መምህር ማዕበል እንደሚሉት ከእነዚህ ኢትዮጵያዊያን ነገሥታት መካከል በ1 ሺህ 400 ዓ.ም የነገሡት አጼ ዳዊት በዘመኑ በሀገራቸው ለገጠማቸው በሽታ እና ችግር መፍትሄው ሀገራቸው በክርስቶስ መስቀል መባረኳ ነው ብለው ያምኑ ነበር፡፡ መስቀሉን መቼ እና እንዴት እንደሚያመጡት እያሰቡ እያለ የእስክንድሪያው ፓትርያርክ በግብጽ የመታሰራቸውን ዜና ሰሙ፡፡ ንጉሱ አጼ ዳዊትም የፓትርያርኩን መታሰር እንደሰሙም ጦራቸውን ከትተው ወደ ሱዳን ተጠጉ፡፡
ንጉስ ዳዊት በሱዳን አካባቢ እያሉም በእስክንድሪያ የሚፈጸመው ግፍ እንዲቆም እና ፓትርያርኩም በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠየቁ፡፡ ይህ ካልኾነ ግን የዓባይን ወንዝ አቅጣጫ እንደሚያስቀይሱት እና ጦርም እንደሚያዘምቱ ተናገሩ፡፡ የንጉሱ መልእክት በግብጽ እንደደረሰም ብርቱ ጭንቀት ተፈጠረ፡፡ ጸቡን በሰላም ማብረዳቸውን እና ፓትርያርኩንም የመፍታታቸውን መልእክት ከ12 እልፍ ወርቅ እና ዲናር ገጸ በረከት ጋር ለንጉሥ ዳዊት ላኩ፡፡ ንጉሥ ዳዊት ግን ከተላከላቸው ስጦታ ይልቅ የክርስቶስ ግማደ መስቀል እንዲሰጣቸው በድጋሚ መልእክት ላኩ፡፡
የግብጹ ንጉሥ እና ሊቀ ጳጳሱም ፈቅደው ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ግማደ መስቀል ከሌሎች ንዋየ ቅድሳት ጋር በአቡነ ሚካኤል እጅ ለንጉሥ ዳዊት ተላከ፡፡ ንጉሥ ዳዊትም አስዋን ድረስ ወርደው ክቡር መስቀሉን በክብር ተቀበሉ፡፡ ነገር ግን ጉዞው እጅግ አድካሚ ስለነበር ንጉሡ ግማደ መስቀሉን ወደ ሀገራቸው ሳያስገቡ መንገድ ላይ አረፉ፡፡ በአባታቸው እግር ዙፋኑን የወረሱት ዓጼ ዘርዓ ያቆብም የክርስቶስን ግማደ መስቀል እና ከአባታቸው አጽም ጋር ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት ቻሉ፡፡
ዓጼ ዘርዓ ያዕቆብ ከግብጽ የመጣውን የክርስቶስ ግማደ መስቀል ለጊዜው የመንግሥታቸው መቀመጫ በነበረችው ደብረ ብርሃን አስቀምጠው የዘላቂ መቀመጫውን ፈቃደ እግዚአብሔርን ሲጠባበቁ ቆዩ ይሉናል መምህር ማዕበል፡፡ በመጨረሻም “መስቀሌን በመስቀለኛ ሥፍራ አስቀምጥ” ስለተባሉ ከብዙ ድካም እና ውጣ ውረድ በኋላ የግሸን አምባ ተገኘች፡፡ ንጉስ ዘርዓ ያዕቆብም በስፍራው የእግዚአብሔር አብን ቤተ ክርስቲያን አሳድሰው እና ዋሻ ፈልፍለው ግማደ መስቀሉን በግሸን ደብረ ከርቤ እንዳስቀመጡት ይነገራል፡፡
ከቀራኒዮ እስከ ጎለጎታ፣ ከእየሩሳሌም እስከ ፋርስ፣ ከሮም እስከ ግብጽ ከዚያም እስከ ኢትዮጵያ የተዘረጋውን “ጥንታዊው ነገረ መስቀል በኢትዮጵያ” ዘወትር በየዓመቱ በጥቢ ወቅት የምታከብረው ቤተ ክርስቲያን ስለሀገር እና ሃይማኖት ጽናትን፣ እምነትን እና አንድነትን ታስተምርበታለች፡፡ “አባት ያበጀው ለልጅ ይበጀው” እንዲሉ ከጥንት እስከ ዛሬ ሳይቆራረጥ እና ሳይዛነፍ የምታከብረው የመስቀል ደመራ በዓል ትውፊትም ሃይማኖት የሚጸናው እና ሀገር የሚሻገረው በተሰናሰለ የትውልድ ቅብብሎሽ እንደኾነ ያሳያል ይላሉ ሊቃውንቱ፡፡
በታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
