
ባሕር ዳር: መስከረም 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ዛሬ የመስቀል በዓል ነው። በዓሉ በመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በአደባባይ ከሚከበሩ በዓላት ውስጥ አንዱና ዋነኛው ነው። ኢትዮጵያዊያን መስቀልን የባሕላቸው፣ የትውፊታቸው፣ የማኅበራዊና መንፈሳዊ እሴቶቻቸው አካል አድርገው ነው የሚያከብሩት፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የባሕርዳር ማዕከል ሰባኬ ወንጌል መምህር ለይኩን አዳሙ የመስቀል በዓል መከበር መንፈሳዊ መነሻው ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች መዳን በመስቀል ላይ ኾኖ ስጋና ክቡር ደሙን ማፍሰሱ ነው ብለዋል። መስቀል ሃይማኖታዊ በዓል ቢኾንም ኢትዮጵያውያን ግን ከባሕላቸው እና ከማኅበራዊ እሴታቸው ጋርም አቆራኝተው በድምቀት ያከብሩታል ነው ያሉት።
መስቀል በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት ዩኔስኮ እውቅና ተሰጥቶት የዓለም ሃብት እና ቅርስ ኾኖ ለመመዝገብ የበቃውም ከሃይማኖታዊ ኹነቶች በተጨማሪ በባሕላዊ እና ማኅበራዊ ቱሩፋቶች የታጀበ በመኾኑ ነው።
መምህር ለይኩን እንደሚሉት በመስቀል በዓል የደመራ እና ችቦው ብርሃን በርካታ ቱሩፋቶችን ይዞ ነው የሚመጣው። የተጣላ ወይም የተኮራረፈ ሁሉ ልባዊ እርቅ እና ይቅርታ ያወርዳል። ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ደሙ ቢፈስስም ይቅር ባይነቱ ግን የዓለም ሁሉ ምሳሌ ነውና መስቀልም የተኮራረፈውን፣ የተጣላውን፣ የተደማማውን እና የተገዳደለውንም ሁሉ ይቅር ያባብላል። ሁሉም እርቅ እና ይቅርታን አውርዶ ነው በዓሉን የሚያሳልፈው።
ከቤተሰብ የራቀ ሁሉ ለመስቀል በዓል ተሰባስቦ ይቀርባል። የተነፋፈቀ ይገናኛል። ወዳጅ ከዘመዱ፣ ጎረቤት ከጎረቤቱ ይገናኙና በመረጡት አደባባይ ላይ ኾነው እሸቱንም ሙክቱንም ይጋራሉ። የመስቀል በዓል በመጣ ቁጥር ከጎረቤታሞች ተነስቶ ለሀገር የሚበቃ ማኅበራዊ አንድነትን እና መንፈሳዊ ቁርኝትን እየተከለ ነው የሚያልፈው።
መምህር ለይኩን እንደነገሩን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የተሰቀለው የሰው ልጆችን ሕይወት ከመከራ ሁሉ አውጥቶ ወደ ፍስሃ ለመመለስ ነው። እናም መስቀል የመከራ ሁሉ ማብቂያ ፤ የፍስሃ ዘመን ደግሞ መጀመሪያ ነው።
የሀገሬው ሰውም የክረምቱ ዶፍ ፣ ጭጋግ እና ችግር ማለፉን፤ የጸደዩ ፀሐይ፣ አበባ፣ እሸት፣ እና ልምላሜ ደግሞ ጥጋብ ይዞ መምጣቱን በዜማ የሚያበስረው የመስቀል ዕለት ነው።
እሞታለው ብየ ስባባስባባ፣”
እሰይ መስቀል ጠባ
የጐመን ምንቼት ውጣ
የገንፎ ምንቼት ግባ ….በማለትም የችግሩን ጊዜ እየሸኘ የጥጋቡን ወራት በፍስሃ ይቀበላል።
ሰላም ፍቅር ግባ
ሸረኛ ምቀኛ ውጣ…..በማለትም መጭው ጊዜ ፍቅር የሚነግሥበት፤ ጥላቻ ደግሞ የሚራከስበት እንዲኾን በጥብቅ ይመኛል።
“መኾን ከመመኘት ይመነጫል” የሚሉት መምሕር ለይኩን የመስቀል በዓል መልካም ምኞቶች፣ እቅዶች እና ምርቃቶች ለአዲሱ ዓመት የሰላም፣ የፍቅር እና የቸር ነገር ሁሉ ስንቅ ስለመኾናቸው ተናግረዋል።
በመንፈሳዊነት የሚያጠነክረውን፣በዕርቅ ሀገር የሚያጸናውን፣ አብሮነትን በመትከል ማኅበራዊነትን የሚገነባውን፤ የክፋ ነገር ሁሉ መቋጫ ምልክትም የኾነውን የመስቀል በዓል ሀገራዊ እሴት እና ቱሩፋቶቹን በጠበቀ መልኩ እናክብረው ሲሉም መምህር ለይኩን መልእክት አስተላልፈዋል።
ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች መልካም በዓል ይሁንላችሁ!
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!