“የታደለች ንግሥት ፣ የተመረጠች እመቤት”

81

ባሕር ዳር: መስከረም 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ)አንዳንድ ነገሥታት አሉ ቅድስና ከንግሥና ጋር ተጣምሮ የተሰጣቸው፣ አንዳንድ ነገሥታት አሉ በረከትና ረድዔት የማይለያቸው፣ አንዳንድ ነገሥታት አሉ የቤተ መንግሥቱ አጀብ እውነተኛውን መንገድ የማያስታቸው፣ አንዳንድ ነገሥታት አሉ የሠራዊታቸው ብዛት አምላክን የማያሥረሳቸው፣ አንዳንድ ነገሥታት አሉ የዓለሙ ነገር ሁሉ የማያታልላቸው፡፡

ብልሃትን የተቸሩ ነገሥታት በአልማዝ ያጌጠው ዘውዳቸው፣ በእንቁ የተንቆጠቆጠው ዙፋናቸው፣ በወርቅ የተለበጠው በትረ መንግሥታቸው፣ እጹብ የሚያሰኘው ካባቸው፣ በክብር የሚታዩበት ሰገነታቸው፣ በሕዝብ መካከል የሚረማመዱበት፣ ሠረገላቸው በፊት በኋላ፣ በግራና በቀኝ በተጠንቀቅ የሚቆም ሠራዊታቸው፣ እያረገደ አቤት ወዴት እያለ የሚታዘዝ አገልጋያቸው ፣ እጅግ ያማረውና የተዋበው ቤተ መንግሥታቸው ሁሉ አያኩራራቸውም፡፡ አጀቡም እንደሚያልፍ፣ ሰልፉም እንደሚቀር፣ እነርሱም አላፊ ጠፊዎች እንደኾኑ ያውቃሉና፡፡

ይልቅስ በልባቸው አምላክን ያስቡታል፣ ይሰግዱለታል፣ ስማቸውን ከሕይወት መዝገብ ላይ እንዳያጠፋ ይማጸኑታል፣ በምድርም ስማቸው የሚዘከርበት፣ ትውልድም የሚመካበት፣ ሀገርና ሕዝብም የሚኮራበት መልካም ሥራ ይሠሩ ዘንድ አብዝተው ይጠይቁታል፡፡

ከልጅነት ጀምራ አማላኳን በልቧ አሰበችው፣ በሰርክ አመሰገነችው፣ በረከትን እንዳይለይባት፣ ሃይማኖቷን እንዲጠብቅላት፣ ጥበብና ሞገስን እንዳይነሳት ለመነችው፣ በመከራ ዘመንም እንዲያጸናት ተማጸነችው፡፡

እርሷ ከምድራዊ ይልቅ ሰማያዊ ዓለም ያጓጓታል፣ እርሷ ከአላፊው ምድራዊ ቤተ መንግሥት ይልቅ የማያልፈው ሰማያዊ መንግሥት ያሳስባታል፣ እርሷ በሰርክ ጌታዋን ታስባለች፣ በደግነትም ትጠብቀዋለች ኢሌኒ ንግሥት፡፡ እርሷ ንግሥናን ከቅድስና አጣምራለች፣ ልቧን በመልካም ሀሳብ መልታለች፡፡

መስቀል በተነሳ ጊዜ ሁሉ አብራ ትነሳለች፡፡ በአበው አንደበት ትዘከራለች፡፡ አበው የእርሷን ታሪክ ሲዘክሩ ሁለት ደጋግ ክርስቲያኖች ተጋብተው ይኖሩ ነበር፡፡ ኢሌኒ እና ተርቢኖስ ይባላሉ፡፡ ተርቢኖስ የብስ በግመል እያቋረጠ፣ ባሕር በመርከብ እየሰነጠቀ ሩቅ ሀገር እየሄደ የሚነግድ ነጋዴ ነበር፡፡ ለንግድ ሩቅ ሀገር ይሄዳል እና በሄደበት ሥፍራ ለረጅም ጊዜ ይቆያል፡፡ በዚህም ጊዜ ባለቤቱ ንግሥት ኢሌኒ አምላኳ ባሏን በሰላም እንዲመልስላት እየጸለየች በተከበረው ግቢዋ ትኖራለች፡፡

በአንድ ወቅት ተርቢኖስ ለንግድ ሄዶ ወደ ሀገሩ እየተመለሰ እያለ ከነጋዴዎች አንደኛው ከሽፍታና ከማዕበል ተርፈን፣ ነግደን አትርፈን በሰላም ተመለስን፣ ነገር ግን ሚስቶቻችን ሌላ ሳይለምዱና ሳይወዱ እናገኛቸው ይኾንን ? ብሎ ጠየቀ፡፡

የኢሌኒ ባለቤት ተርቢኖስም እንኳን በሰላም ተመለስን እንጂ ሚስቴንስ በዚህ አልጠረጥራትም አለ፡፡ ለምን ቢሉ ከልቡ የሚያምናት፣ ከልቡም የሚታመንላት ናትና፡፡ በዚህ ጊዜ ጓደኛው የአንተ ሚስት ከማን ትበልጣለችና ነው አሁን ሄጄ ከሚስትህ ጋር ለምዳኝ ለምጃት ብመጣስ ምን ትቀጣለህ አለው፡፡

ተርቢኖስም ሚስቱን አብዝቶ ያምናት ነበርና ይሄን ብታደርግ ሃብቴን ከነትርፉ ውሰድ አለው፤ ነጋዴውም ባይሳካለት ሃብቱን ከነትርፉ ሊሰጠው ተስማማ፡፡ በዚሁ ተስማምተው መርከቡ ወደ ወደብ ከመድረሱ አስቀድሞ ወደ ኢሌኒ ቤት ደረሰ፡፡ በቤት በደረሰ ጊዜም የኢሌኒን አገልጋይ ኢሌኒን እንደምፈልጋት ንገሪልኝ አላት፡፡ አገልጋዩዋ ግን ኢሌኒ ይሄን አታደርግም ስትል ነገረችው፡፡ ነጋዴው ግን ትጠይቅለት ዘንድ ለመናት፡፡ አገልጋዩዋም የተባለችውን ለኢሌኒ አደረሰች፡፡ ኢሌኒ ግን ከመቼ ወዲህ ነው እንዲህ የማደርገው ስትል አይኾንም አለች፡፡ አገልጋዩዋም አይኾንም ማለቷን ለነጋዴው ነገረችው፡፡

ነጋዴውም ተሸንፎ ሃብቱን እንደሚወረስ ባወቀ ጊዜ ሌላ ተንኮል አሰበ፡፡ ለአገልጋዩዋም ባልና ሚስቱ ብቻ የሚያቁትን አንድ ምስጢር ብቻ ትነግረው ዘንድ አጥብቆ ለመናት፡፡ ከሰጠችውም ብዙ ገንዘብ እንደሚሰጣት ቃል ገባላት፡፡ አገልጋዩዋም እመቤቴና ጌታዬ ብቻ የሚያውቁት አንድ የወርቅ ሀብል አለ ያን አመጣልሃለሁ፡፡ አንተ ግን ወደ ከተማ ሂድና ነጋዴዎች መጡ፣ የብስ ረገጡ እያልክ ንገር፣ ከዚያም ተመልሰህ ና አለችው፡፡

ነጋዴውም የተባለውን አደረገ፡፡ ይሄን የሰሙት የነጋዴ ቤተሰቦችም ነጋዴዎችን ለመቀበል ሽርጉድ ማለት ጀመሩ፡፡ አገልጋዩዋም ወደ ኢሌኒ ሄዳ እመቤቴ ነጋዴዎች ስለመጡ ለመቀበል ይዘገጃጁ አለቻት፡፡ ኢሌኒም ባለቤቷን ለመቀበል ለመዘገጃጀት ተነሳች፡፡ ገላዋን ትታጠብ ዘንድም ወደ መታጠቢያ ክፍል ገባች፡፡ በዚያም ጊዜ እርሷና ባለቤቷ ተርቢኖስ ብቻ የሚተዋወቁበትን ሀብል አስቀምጠው ነበር፡፡ አገልጋዩዋም ባልና ሚስቱ ብቻ የሚተዋወቁበትን ሀብል አንስታ ለነጋዴው አቀበለችው፡፡

ነጋዴው ለአገልጋዩዋ ቃል የገባላትን ሰጥቶ ወደ ነጋዴዎች ተመለሰ፡፡ ለተርቢኖስም ሚስትህን ወድጃት ፣ ወዳኝ፣ ለምጃት፣ ለምዳኝ መጣሁ አለው፡፡ ባለቤቱን አብዝቶ የሚወዳትና የሚያምናት ተርቢኖስም ይሄስ ውሸት ነው ለዚህ ምን ምልክት አለህ አለው፡፡ ተንኮለኛው ነጋዴም ይህ ሀብል የሚስትህ አይደለምን? ብሎ ሰጠው፡፡ ተርቢኖስም ያን ባየ ጊዜ ደነገጠ፣ በውርርዱም ተሸነፈና ሀብቱን ሁሉ ሰጠ፡፡ በሀዘንም ወደቤቱ ሄደ፡፡ ባለቤቱ በናፍቆትና በታማኝነት ስትጠብቀው የኖረችው ኢሌኒ በባለቤቷ ሀዘን ግራ ተጋባች፡፡ ምን ኾነሃል፣ ለወትሮው እንኳን ይሄን ያክል ጊዜ ቆይተህ በጥቂት ቀናትም እንነፋፈቅ ነበር፣ አሁን ግን ከመጣህበት ጊዜ ጀምሮ አዝነህ አይሃለሁ አለችው፡፡ ተርቢኖስም ሃብትና ንብረቴን ማዕበል በላብኝ፡፡ እኔ ያላዘንኩ ማን ይዘን አላት፡፡

ኢሌኒም እግዚአብሔር ሰጠ፣ እግዚአብሔር ነሳ፣ አንተ እንኳን በሰላም መጣህ እንጂ ሃብቱ ይመጣል አለችው፡፡ ተርቢኖስም ከእንግዲህ በተከበርኩበት ሀገር ተዋርጄ፣ በሰጠሁበትም ሀገር ለምኜ ለመኖር አይቻለኝምና ወደማያውቁኝ ሀገር ልሂድ፣ አንቺ ግን ሁሉ ይወድሻልና ከወደድሽው ጋር ኑሪ አላት፡፡ ኢሌኒም በደስታህ ጊዜ አብሬህ እንደኖርኩ ሁሉ በሀዘንህም ጊዜ አብሬህ እሄዳለሁ እንጂ ከአንተ ተለይቼስ አልቀርም ስትል አብራው ለመሄድ ተነሳች፡፡

በመንገድ ላይም ተርቢኖስ በልቡናው ይዞት የነበረውን ተነፈሰው፡፡ ኢሌኒ ኾይ ስወድሽ የጠላሽኝ ሳምንሽ የከዳሽኝ ምን አድርጌሽ ነው ብሎ ጠየቃት፡፡ እርሷም አንተን አልጠላሁም፣ አልከዳውህምም ስለ ምን ይሄን ሃሳብ አሰብክ አለችው፡፡ ተርቢኖስም የኾነውን ሁሉ ነገራት፡፡ ኢሌኒ ግን እውነተኛውን ታሪክ ነገረችው፡፡ እየተጓዙም በባሕር ዳር በደረሱ ጊዜ በቁመቷ ልክ ሳጥን አሰርቶ በውስጡ አስገባት፡፡ እውነተኛ ከኾንሽም እርሱ ያውጣሽ፣ እውነተኛ ካልኾንሽም ትጠልቂያለሽ ሲል ሥራሽ ያውጣሽ ብሎ ወደ ባሕር ወረወራት፡፡

ኢሌኒ ያለችበት ሳጥን እየተንሳፈፈ በፈቃደ እግዚአብሔር ወደ አንድ ወደብ ደረሰ፡ ሳጥኑን ያገኙ ሰዎችም በዚያች ሀገር ለነገሠ ንጉሥ ወሰዱት፡፡ ንጉሡም ሳጥኑን እንዲከፍቱት አዘዘ፡፡ ሳጥኑ በተከፈተ ጊዜ ያማረችና የተዋበች ሴት ተገኘች፡፡ ንጉሡም ሚሰቱ ትኾን ዘንድ ወደደ፡፡ በሃይማኖት ግን አይመስላትም ነበር፡፡ አገባት፡፡ ወንድ ልጅም ወለደችለት፡፡ የአባቱ ባለሟልም ኾኖ አደገ፡፡ በጦርነት የማይበገር፣ ጠላቶች የሚንበረከኩለት፣ ጥሩ የጦር መሪና ጦረኛ ነበርና ሠራዊቱ ይወደዋል፤ ያከብረዋል፡፡ ስሙም ቆስጠንጢኖስ ይሰኛል፡፡ አባቱ ባለፈ ጊዜም እርሱ በአባቱ ዙፋን ተተካ፡፡

ኢሌኒ ንግሥትም ልጇ ክርስቲያን የኾነላት እንደኾነ የጌታን መስቀል ለማውጣት ለአምላኳ ተሳለች፡፡ ይፈጸምላት ዘንድም ተማጸነች፡፡ ተፈጸመላትም፡፡ በዚያን ጊዜ በታላቅ አጀብ ከሮም ወደ ኢየሩሳሌም ገሰገሰች፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በባሕርዳር ሀገረ ስብከት የአራቱ ጉባያት መምህር ሊቀ ሊቃውንት ስመዓኮነ መልአክ የመስቀል በዓል በታሰበ ጊዜ ኢሌኒ ንግሥት ትታሰባለች፣ ኢሌኒ ንግሥት በታሰበችም ጊዜ መስቀል ይታሰባል ይላሉ፡፡ ስለ ምን ቢሉ እርሷ መስቀሉን ቆፍራ አግኝታለች፣ አግኝታም በደማቅ አክብራለችና፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በአይሁድ ቅናት ተቀብሮ ይኖር ነበር፡፡ ያንም ፈልጎ ማግኘት የኢሌኒ ንግሥት ፍላጎትና ምኞት ነበር፡፡ የልቧን መሻት እግዚአብሔር ፈጽሞላት መስቀሉን አገኘች ነው የሚሉት፡፡

መስቀሉን ባገኘች ጊዜም አብዝታ ተደሰተች፡፡ የመስቀሉን በዓልም አከበረች፡፡ በጎለጎታም ቤተ መቅደስን አሳነጸች፡፡ ንግሥት ኢሌኒ ከመስቀሉ ጋር ስለሁለት ነገር ስሟ አብሮ ይነሳል የሚሉት ሊቁ ለዓመታት የጠፋውን መስቀል ቆፍራ ስላገኘች እና ቤተ መቅደስ አሳንጻ በታላቅ ክብር ስላከበረች ስሟ አብሮ ይነሳል ይላሉ፡፡

ይህች የታደለች እና የተመረጠች እመቤት ቆፍራ ያገኘችው፣ ባገኘችውም ጊዜ አብዝታ የተደሰተችለት እና ያከበረችው መስቀል በክርስቲያኖች ዘንድ ይታሰባል፡፡ ከፍ ከፍም ይደረጋል፡፡ ይከበራል፡፡ የመስቀሉ በዓል በተከበረም ጊዜ ኢሌኒ ትነሳለች፣ ኢሌኒም አብራ ትዘከራለች፡፡ እርሷ ጥበበኛ ንግሥት ናት ስሟ በትውልድ ሁሉ ሲነሳ የሚኖር፣ ታላቁን ነገር ነው እና የፈጸመችው፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የበደል መደምሰሻ፣ የጠላት ድል መንሻ”
Next article“እሞታለው ብየ ስባባ ስባባ፣ እሰይ መስቀል ጠባ”