
ባሕር ዳር: መስከረም 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ለዘመናት የቆዬ በደል ተደመሰሰበት፣ ጥንተ ጠላት ድል ተነሳበት፣ የመከራው ዘመን ተቋጨበት፣ የጨለማው ዘመን አለፈበት፣ ብርሃን ሁሉ በዓለም በራበት፣ ሰማይና ምድር ታረቁበት፣ ሰውና መላእክት በጋራ ዘመሩበት፣ ፈጣሪያቸውን በአንድነት አመሰገኑበት፡፡
ሲዖል በብርሃን ተመላች፣ ከብርሃናት ሁሉ በሚልቀው ብርሃን ተጨነቀች፣ ተበረበረች፣ አብዝታም ደነገጠች፣ የአሰረቻቸውን ነፍሳት ተዘረፈች፣ የጭንቅ ዘመን ተፈጸመች፣ የሲዖል አለቃ ተጨነቀ፣ ብርሃኑን ባየ ጊዜ ወደቀ፣ የያዛቸውን ነፍሳት ለቀቀ፣ ለዓመታት በተስፋ የጠበቁ ነፍሳት የእናቱን ጡት እየጠባ እንደሚዘል የአንበሳ ደቦል ዘለሉ፣ ክብርና ምሥጋና ለአምላካችን ይሁን አሉ፣ አምላካቸውን አብዝተው አመሠገኑ፡፡
በደለኞቹን ይቅር ሊላቸው፣ በጨለማ ውስጥ ያሉ ነፍሳትን ወደ ብርሃን ሊመልሳቸው፣ በሲዖል የታሰሩትን ሊያስፈታቸው፣ የሰው እጅ ያልሠራውን የዘለዓለም የክብር ካባ ሊያለብሳቸው፣ ደስታና ተድላ ወደማይጠፋበት የዘለዓለም ርስት ሊመልሳቸው ዘመኑ በደረሰ ጊዜ አምላክ ምድርን በምህረት ዓይኖቹ ተመለከታት፡፡ ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም እንዳለ ቃል ኪዳኑን ሊፈጽም መጣላት፡፡ ከሰማየ ሰማያት ወረደ፣ በነብስም፣ በስጋም፣ በሃሳብም፣ ንጽሒት እና ብጽዒት ከኾነች እመቤት ዘንድ ዘር ሳይቀድመው፣ ድንግልናዋንም ሳይለውጠው ተጸነሰ፡፡ በረቀቀ ምስጢር ተዋሐደ፡፡ ድንግልናዋን ሳይለውጠው ተወለደ፡፡ በክብርና ሞገስም አደገ፡፡
በምድር ተመላለሰ፣ ምድርን ቀደሳት፣ ባረካት፣ ከመከራዋና ከስቃይዋ ፈወሳት፡፡ ምድር ግን መድኃኒቷን ሞት ደገሰችለት፣ ፈጣሪዋን ጦር አቀረበችለት፣ አምላኳን ኾምጣጣ ሐሞት አዘጋጀችለት፣ ሊያድናት መጥቶ ሳለ ወጋችው፣ ከጨለማ ሊያወጣት መጥቶ ሳለ አሳደደችው፣ ዓመተ ፍዳዋን ሊያሳልፍላት መጥቶ ሳለ ቸነከረችው፣ በችንካር ወጠረችው፤ እርሱ ግን በደል እየደረሰበት ይቅር አላት፣ በደሏን ይደመስስላት ዘንድ ሞተላት፡፡
እርሱ ሞትና ሕይወትን በእጁ የያዘን አምላክ እንዲሰቀል ፈረዱበት፣ ዓለማትን የፈጠረ፣ ዓለምን ከመፍጠሩ አስቀድሞ የነበረ፣ የፍጥረታት ሁሉ ጌታ፣ በፈቃዱ ለሞት ተላልፎ ተሰጠ፡፡ በችንካር ቸንክረው በመስቀል ሰቀሉት፣ በመስቀል ላይ ደሙን አፈሰሰ፣ ስጋውንም ቆረሰ፣ በተስፋ ይጠብቁት ለነበሩ የሲዖል ነፍሳት መድኃኒትን ሰጣቸው፡፡ የሲኦል ኀይለአጋንትን ከእግር በታች ጣላቸው፣ በሰው ልጆች ላይ እንዳይሰለጥኑ አሰራቸው፣ በኀይሉ አስጨነቃቸው፣ ከመስቀሉ ብርሃኑ ወጣ፣ ለዓለምም አበራ፣ የጨለማዋ ዓለም በብርሃን ተመላች፡፡ ያቺ የመዳን ቀን ደረሰች፡፡
አበው መስቀል የመዳን ቃል ነው ይላሉ፣ በመስቀል ዓለም ድናለች፣ በደል ተደምስሳለች፣ ሲዖል እርቃኗን ቀርታለች እና፡፡ መስቀል የጥል ግድግዳ የፈረሰበት ነውም ይላሉ፡፡ ለዘመናት የተጣሉት ታርቀዋል፣ ለዘመናት የተጣሉት ተነስተዋል፣ ለዘመናት በጨለማ የኖሩት ብርሃንን አይተዋልና፡፡ ጌታ ሞትን ድል አድርጎ ተነሳ፡፡ በአርባኛውም ቀን ወደ ሰማይ አረገ፡፡ እርሱ የተሰቀለበት መስቀል ግን በምድር ያበራል፣ ታዕምራትን ያደርጋል፣ እንደ ፀሐይ እያበራ ሕሙማንን ይፈውሳል፣ አጋንንትን ይቀጠቅጣልና ይሄን ያዩ ሁሉ እያመኑ ወንጌልን ይማሩ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝነት እና ጌትነት ይመሰክሩ ጀመር፡፡ በዚያን ጊዜ የሰቀሉት ጨነቃቸው አብዝቶም ጠበባቸው ይላሉ አበው፡፡
አይሁዳውያን ግን መስቀሉን ያጠፉትና ይሰውሩት ዘንድ ወደዱ፡፡ ስጋው የተቆረሰበትን፣ ደሙ የፈሰሰበትን፣ የመከራ ዘመን የተፈጸመበትን፣ ድል የተመቱበትን ፣ የጥል ግድግዳ የተደረመሰበትን መስቀል ሊያጠፉት ተነሱ፡፡ ጉድጓድ አስቆፈሩ፣ መስቀሉንም ቀበሩ፤ በተቀበረበትም ሥፍራ የከተማው ቆሻሻ ሁሉ ይጣልበት ዘንድ አዘዙ፡፡ ሕዝቡም የታዘዘውን አደረገ፡፡ ዓመታት ነጎዱ፣ መስቀሉ የተቀበረበት ሥፍራ እንደተራራ ኾነ፡፡ ያ ዓለም የዳነበት መስቀል ተቀብሮ ዓመታት እየተከታተሉ አለፉ፡፡
ሌላ ዘመን መጣ፡፡ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እና ንግሥት ኢሌኒ ነገሱ፡፡ ኢሌኒ ንግሥት ልጇ ቆስጠንጢኖስ ከአረማዊ ንጉሥ የተወለደ ክርስትና ሃይማኖትን ያልተቀበለ ነበርና ክርስትናን የተቀበለ እንደኾነ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዤ የጌታዬን መስቀል አወጣለሁ፣ ስሙ የሚመሰገንበት፣ ክብሩም የሚነገርበት ቤተ መቅደስ አሠራለሁ ብላ ተሳለች፡፡ ስለቷም ደረሰ፡፡ ስለቷን ትፈጽም ዘንድም የንጉሥ እናት ንግሥት ናትና በታላቅ አጀብ ከሮም ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘች፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በጎንደር የአራቱ ጉባያት መምህር እና የጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አሥተዳደሪ ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ ስለ መስቀሉ ሲናገሩ ኢሌኒ ጌታ ሆይ ፈቃድህ ቢኾን መስቀልህን አወጣለሁ ብላ ተሳለች፣ ጌታም ስለቷን ሰማት፡፡ ኢሌኒ ኢየሩሳሌም በደረሰች ጊዜ መስቀሉ ያለበትን ሥፍራ የሚያሳያት ሰው ጠየቀች፡፡ የሚያሳያት ግን አልነበረም፡፡ ብዙ ደከመች፡፡ ከብዙ ድካም በኋላም ኪራኮስ የተባለ አረጋዊ አገኘች፡፡ እርሱም ከአያት ቅድመ አያቶቹ የሰማውን ሁሉ ነገራት፡፡ ነገር ግን በእውነት ከየትኛው ተራራ ላይ እንዳለ ግን ማወቅ አልተቻለም፡፡
ኢሌኒም ጸለየች፡፡ መስቀሉ ያለበት ሥፍራ ይገለጥላት ዘንድም ሱባኤ ያዘች፡፡ በዚያም ጊዜ የእግዚአብሔር መላአክ ወደ እርሷ መጣ፡፡ የእግዚአብሔር መላአክም የመስቀሉ ነገር ድንቅ ነው፣ እኛ የመላእክት ነገዶች ስለመስቀሉ ብዙ እንነጋገራለን፣ እንጨት አሰብስበሽ፣ ደመራ አስደምረሽ፣ እጣኑን በሊቀ ጳጳሱ አስባርከሽ አስለኩሽው፡፡ ከደመራው የሚወጣው ጭስም ወደ ሰማይ ይወጣና ተመልሶ መስቀሉ ካለበት ቦታ ላይ ምልክት ይሰጥሻል አላት ይላሉ፡፡
ኢሌኒ ንግሥትም የተባለችውን አደረገች፡፡ ደመራው ተለኮሰ፡፡ ጭሱ ወደ ሰማይ ወጥቶ ተመልሶ መስቀሉ ካለበት ሥፍራ ላይ ሰገደ፡፡ ኢሌኒም የልቧን መሻት በእግዚአብሔር መላአክ ረዳትነት አወቀች፡፡ መስቀሉ ያለበትን ሥፍራም ማስቆፈር ጀመረች፡፡
ከብዙ ድካም በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ወጣ፡፡ በወጣም ጊዜ ብዙ ታምራትን አደረገ። በዚያም ጊዜ ንግሥቷ ኢሌኒ እና አብረዋት የነበሩ ሁሉ ደስታን አደረጉ፡፡ ለእግዚአብሔር ዘመሩ፡፡ መስቀሉንም ተሸከሙ፡፡ መስቀሉም ድውያንን ይፈውሳል፣ ሙትም ያስነሳል፡፡ ኢሌኒ ንግሥት የአምላኳ መስቀል የሚያርፍበት ያማረ ቤተ መቅደስ አሳነጸች፡፡ ቅዳሴ ቤቱንም አከበረች፡፡ አስቀድማ የተሳለችውን ስለት ሁሉ አደረገች፡፡ ይህም መስቀል መድኃኒት ኾኖ ኖረ፡፡
ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ መስቀል በዓለመ መላእክትም ዘንድ አለ፡፡ አምላክ መላእክትን ፈጥሮ በተሰወረ ጊዜ ሳጥናኤል እኔ ነኝ አምላክ አለ፡፡ በዚያም ጊዜ በመላእክት ወገን ጠብ ተነሳ፡፡ እግዚአብሔርም በእርሱ ላመኑ መላእክት የብርሃን መስቀል ሰጣቸው፡፡ መላእክትም ጠላትን ድል መቱት፡፡ መስቀል ከሰው በፊት በመላእክት ፊት መከበር ጀምሯል፡፡ መላእክት ሲፈጠሩ በአርዓያ መስቀል ነው የተፈጠሩት፣ ሰውም የተፈጠረው እንዲሁ በመስቀል አምሳል ነው ይላሉ አበው፡፡ የመስቀል ታሪክ ከሥነ ፍጥት ጀምሮ ይነገርለታል፣ ይከበራል፡፡
እግዚአብሔር ለአዳም ቃል ኪዳን በገባለት ጊዜ በመስቀል እንደሚሰቀል ነግሮት ነበር፣ ይሄም ተስፋ ሲጠበቅ የኖረ ነው፣ መስቀል ለአዳም ቃል ከተገባለት ዘመን ጀምሮ ይታሰብና ይጠበቅ ነበር፡፡ ነብያት ስለ መስቀሉ ትንቢት ተናግረውለታል፡፡ መስቀል ያልታየበት፣ ያልተዘረጋበት፣ መስቀል ያልተከበረበት ዓለም የለም ይላሉ ሊቁ፡፡
ይህ ታላቅ መስቀልም ለክርስቲያኖች ምልክታቸው፣ አርማና መመኪያቸው ነው፡፡ መስቀል ኀይልነ እያሉ ይመኩበታል፣ ጠላታቸውንም ድል ይመቱበታል፡፡ ይሄን መስቀል ያከብሩታል፣ እነኾ ያ ጌታ የተሰቀለበት፣ ጨለማ ወደ ብርሃን የተለወጠበት፣ በደልም የተደመሰሰበት የመስቀል በዓል ደርሷል፡፡ ክርስቲያኖችም በመስቀሉ ያገኙትን ድኅነት እያሰቡ፣ ለአምላካቸውም ክብርና ምሥጋና እያቀረቡ ያከብሩታል፡፡
መስቀል እርቅ የተፈጸመበት፣ አንድነት የኾነበት፣ ሀጥያት የተደመሰሰበት፣ መለያየት የቀረበት፣ በሰማይና በምድር ለአምላክ ምሥጋና የተቀረበበት ነው፡፡ መስቀል ጥል የጠፋበት፣ ፍቅር የነገሰበት፣ የፍቅር ኀያልነት የተገለጠበት፣ አምላክ ለሰው ልጆች ምሕረትን እና መዳንን የሰጠበት ነው፡፡ በመስቀሉ ሰው እና እግዚአብሔር አንድ እንደኾኑት አንድ ሁኑ፡፡ በመስቀሉ እንደታረቁት ታረቁ፡፡ በመስቀሉ እንደተሰባሰቡት ተሰባሰቡ፡፡ መለያየት እና ጥልን አርቁ፡፡ በመስቀሉ ሰላም ወርዷልና ሰላምን አውርዱ፣ ሰላምን ስጡ፡፡ የሰላምን አምላክ አስቡ፣ ለምድርም ሰላምን ስጧት፣ ሰላም ትኾን ዘንድም በአንድነት ጠብቋት፤ እረፍትና ደስታንም ታገኝ ዘንድ አድርጓት፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!