“የአጋቾችን ማንነት፣ ያገቱበትን ምክንያት እና እንዴትና ለምን ታገቱ? የሚለውን ጉዳይ ለማወቅ ከፍተኛ የምርመራ ቡድን ተዋቅሮ በቅንጅት እየተሠራ ነው፡፡” የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን

335

ባሕር ዳር፡- ጥር 19/2012ዓ.ም (አብመድ) የፌዴራል መንግሥት ልዑክ የታገቱ ተማሪዎችን በተመለከተ በደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ትናንት ተወያይቷል፡፡

በውይይቱ የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚልን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመከላከያ እና የደኅንነት ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡
በአካባቢው ባለሀብቶችን ጨምሮ ሌሎች ግለሰቦች ላይም እገታ እየተፈጸመባቸው እንደሆነ በውይይቱ ተገልጧል፡፡ የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ደግሞ ከታገቱት 17 ተማሪዎች መካከል 12ቱ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች መሆናቸውን ከተማሪዎች የመረጃ ሰነድ መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በበኩላቸው ከአሁን በፊት በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን የታገቱት ተማሪዎችን በተመለከተ የተሰጠው መረጃ ትክክል መሆኑን ነው ያረጋገጡት፡፡ “21 ተማሪዎች መለቀቃቸውን ስንገልጽ የታጋቾቹ ቁጥር በወቅቱ አሁን ከሚባለው በላይ ነበር፤ በዚህ ድርጊት እኛ የቁጥር ጨዋታ ሳይሆን በተጨባጭ ታግተው የነበሩ እና የተለቀቁ ሰዎችን ቁጥር ነው ያሳወቅነው፤ እየሠራን ያለነውም እንደ መንግሥት ኃላፊ ብቻ ሳይሆን እንደ ታጋች ቤተሰብ ሆነን ነው” ብለዋል አቶ ንጉሱ፡፡

“ተለቀቁ ብለን መግለጫ የሰጠነውም እውነት ነው፤ 21 የታገቱ ተማሪዎች ተለቅቀዋል፤ ቀሪዎቹን ለማስለቀቅ በትኩረት እየሠራን ነው” ሲሉም አረጋግጠዋል፡፡

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር እንደሻው ጣሰው ደግሞ የአጋቾችን ማንነት፣ ያገቱበትን ምክንያት እና እንዴትና ለምን ታገቱ? የሚለውን ጉዳይ ለማወቅ ከፍተኛ የምርመራ ቡድን ተዋቅሮ በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ለአብመድ ገልጸዋል፡፡

የታገቱ ተማሪዎችን ጉዳይ በተመለከተ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የሚመራ አጣሪ ኮሚቴ እየተከታተለው እንደሚገኝም በውይይቱ ተገልጧል፡፡

ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን- ከደምቢዶሎ

Previous articleበሥድስት ወራት ብቻ በዞኑ በትራፊክ አደጋ የ83 ሰዎች ህይወት አልፏል፤ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ንብረትም ወድሟል፡፡
Next articleሰላማዊ ሰልፎቹ በሠላም መጠናቀቃቸውን ፖሊስ አስታወቀ፡፡