“መስቀልን ስናከብር ከመለያየት ወጥተን አንድነትን፣ ከፀብ ይልቅ ፍቅርን፣ ከሁከት እና ብጥብጥ ወጥተን ሰላምን መስበክ ይጠበቅብናል” መምህር አብርሃም ሞላ

65

ባሕር ዳር: መስከረም 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ)የመስቀል ደመራ በዓል በየዓመቱ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በድምቀት የሚከበር በዓል ነው፡፡

መስቀል ጥሬ ትርጉሙ መስቀያ ፣ ማንጠልጠያ ማለት ሲኾን በብሉይ ኪዳን መስቀል የጥፋተኞች መቅጫ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል፡፡

ይሁን እንጅ መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን መከራ ያስወግድ ዘንድ ንጹህ ኾኖ ሳለ በቀራንዮ አደባባይ በጥፋተኞች መካከል ተሠቀለ፡፡ ይህም የሰው ልጆችንና የመስቀሉን ታሪክ ቀየረ፡፡ ይህ ኹኔታ የተዋረደውን መስቀል ከፍ አደረገው፡፡ መስቀል የክርስቲያኖች ዓርማ እንዲኾንም ኾነ፡፡ ከኢየሱስ ክርስቶስ መሰቀል በኃላ መስቀል የአጋንንት መቅጫ መሳሪያ ኾነ።

መስቀል የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 1ኛ ቆሮንጦስ ምዕራፍ 1 ከቁጥር 17 እስከ 19 “የመስቀሉ ጣዕም ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድነው ግን የእግዚያብሔር ኃይል ነው” ተብሎ ስለመቀመጡ ያነሱት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የፅረአርያም ደብረሲና በዓታ ለማርያም ገዳም የስብከተ ወንጌል ክፍል ኀላፊ መምህር አብርሃም ሞላ ናቸው።

ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮ ተራራ ላይ ከተሰቀለ ወዲህ መስቀል ደመ መለኮት የነጠበበት፣ ሥጋው ያረፈበት ሥለኾነ አጋንንትን ያወጣ፣ ሕሙማንን ይፈውስ ፣ ሙት ያስነሳ፣ ለምፃሞችን ያነጻ የእግዚአብሔር ምህረት ይገለጽበት እንደነበረ አስገንዝበዋል።

መስቀሉ ባደረገው ተዐምራት አይሑድ ተመቅኝተው በይሁዳ እና በኢየሩሳሌም መካከል ቀብረው የቤት ቆሻሻ የሚያወጣ ኹሉ በመስቀሉ መቃብር ላይ እንዲደፋ አዋጅ አስነግሩ። መስቀሉም ለ300 ዓመት ተቀብሮ ቆየ። ይሁን እንጅ መስቀሉ ለዓለም ያበራ ዘንድ ንግሥት እሌኒ ልጇ በገባላት ቃል መሠረት አስቆፍራ አስወጣችው።

መስቀል ማለት የፍቅር ምልክት ነው ፤ ኢየሱስም በወንጌሉ ‘የሚወደኝ ቢኖር ነገረ መስቀሉን ተሸክሞ ይከተለኝ ብሎ ስለመናገሩም አብራርተዋል፡፡

መስቀል ማለት አንድነት ማለት እንደኾነም መምህሩ አንስተዋል። ሀዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በኤፌሶን መልእክቱ ምዕራፍ 4 ቁጥር 5 ላይ “ሃይማኖት አንዲት ናት ፣ጥምቀትም አንዲት ናት ፣ክርስቶስም አንድ ነው፣ መስቀሉም አንድ ነው ” ተብሎ እንደተጻፈ መምህር አብርሃም ተናግረዋል።

መስቀል ማለት ክርስቶስ የነገሰበት እኛ አንድ የኾንበት ማለት ነው ፤ መስቀል ማለት ዙፋን ማለት ነው ፤ ንጉሥ የሚነግሰው በዙፋኑ እንደኾነ ኹሉ ክርስቶስም በመስቀሉ ላይ ነገሠ። መስቀሉ ሰው እና እግዚአብሔር ፣ ነፍስ እና ሥጋ፣ ሰው እና መላይክት ፤ ሰማይና ምድር የታረቁበት አንድነት የተፈጠሩበት መኾኑንም መምህሩ ተናግረዋል።

መስቀል በብሉይ ኪዳን የጥፋተኞች መቅጫ እንደነበረ ሁሉ ጥፋት የሌለበት ክርስቶስ ተሰቅሎ አንድነትን ፍቅርን ሰበከልን ፤ አንድ አደረገን ብለዋል። የፀብ ግድግዳ የፈረሰበት አጋንንት ተዋርደው የተጋዙበት ፣ እፀ መስቀሉ ነው። የሰው ልጅ ድኅነት ያገኙበት የምዕመናን ጋሻ ፣ የጻድቃን ዘውድ ፣ አክሊል የኾነው መስቀል ነው ብለዋል።

መምህር አብርሃም እንዳሉት በመስቀሉ ተጣልተው ተለያይተው የነበሩ አካላት አንድ ኾነዋል። እኛም መስቀልን ስናከብር ከመለያየት ወጥተን አንድነትን፣ ከፀብ ይልቅ ፍቅርን፣ ከሁከት እና ብጥብጥ ወጥተን ሰላምን መስበክ ይጠበቅብናል ነው ያሉት።

ዘጋቢ:- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የመስቀል ደመራ በዓል ድምቀቶች ገበያው ላይ በበቂ መጠን ቀርበዋል” ሸማቾች እና ሻጮች
Next article“በሻምፒዮናው ለሀገራችን የተሻለ ውጤት ለማምጣት ተዘጋጅተናል” አትሌቶች