
ጎንደር: መስከረም 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የመስቀል በዓል በድምቀት ከሚከበርባቸው የሀገሪቱ ከተሞች መካከል አንዷ የኾነችው ጎንደር ከተማ መስከረም 17/2016 ዓ.ም የምታከብረውን የመስቀል በዓል ለማከናወን ዝግጅት እያደረገች ነው፡፡ ከተማዋ በየዓመቱ የመስቀልን በዓል በምታከብርበት ከአፄ ፋሲል ቤተ መንግሥት ግርጌ በተለምዶ ‹‹መስቀል አደባባይ›› ተብሎ የሚጠራው አካባቢ ለማክበር ነው ዝግጅት አድርጋለች፡፡
ይህ አካባቢ ለበዓል እያሸበረቁ ከሚገኙ የከተማዋ አካባቢወች መካከል አንዱም ነው፡፡
በዓሉ ያማረ እንዲኾንም የከተማዋ ወጣቶች ድርሻ ከፍተኛ ኾኖ ተስተውሏል፡፡
ወጣቶቹ የአደባባይ በዓሉ የሚከበርበትን የመስቀል አደባባይ ከማሳመር ባሻገር የበዓሉ አካል ኾነው ደመራውን ደምረዋል፡፡
ለበዓሉ ዝግጅት ሲያደርጉ አሚኮ በስፍራው ተገኝቶ ያነጋገራቸው ወጣት ናትናኤል ደሳለኝ እና ወጣት አበራ የኔሁን የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዲከበር ጥረት እያደረጉ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ የመስቀል በዓል በዩኒስኮ ከማይዳሰሱ ቅርሶች የተመዘገበ የሀገር ኩራት መኾኑን አንስተው ክብሩን በሚመጥን አግባብ እንዲከበር ሁሉም የበኩሉን እንደሚወጣ ነው ያስገነዘቡት፡፡
የዘንድሮው የመስቀል በዓል ጎንደር በአስቸኳ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ኾና የምታከብረው ቢኾንም ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ በሰላም እንዲከበር የኩላቸውን እየተወጡ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!