
ባሕር ዳር: መስከረም 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) መስኩ በልምላሜ ተሞልቶ በአደይ አበባ ሲያሸበርቅ ፣ ላሞች በልተው ጠግበው ወተት ሲታለቡ፣ ፀሐይን የጋረዳት ደመና ተገፍፎ ብርሃኗን ያለ ሥሥት ሥትሠጥ፣ አፍላጋት ከገመገማቸው ወርደው ድንፋታቸው ሲቀንስ፣ ዘመድ ከዘመድ መጠያየቅ ሲጀምር፣ አዝዕርት ማበብ እና ማፍራት ሲጀምሩ ምድሩ በአበቦች ሽታ ሲታወድ አሮጌው ዓመት ቦታውን ለአዲስ ዓመት ለቅቆ ይሰናበታል፡፡
ተራርቀው፣ ተነፋፍቀው የቆዩት ዘመዳሞች ሲገናኙ እንኳን አደረሳችሁ ይባባላሉ፡፡ በአዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ የተጀመረው መልካም ምኞት ሳይቀዘቅዝ መስቀል ደመራ ብቅ ይላል፡፡ የደመራው ችቦ ከአርሶ አደሩ ጓሮ ተቆርጦ በአግባቡ ተዘጋጅቶ ለገበያ ይቀርባል፡፡ ገበያተኛውም እንደአቅሙ ሲሸምት አሚኮ ተዘዋውሮ ተመልክቷል፡፡
የደመራው ድምቀት የኾነው አደይ አበባ መስክ ከመለቀም ወጥቶ ለገበያ ቀርቧል፡፡ ለመስቀል ደመራው ድምቀት የኾኑት ችቦ፣ ጨፌ፣ አደይ አበባ፣ በቆሎ፣ ዶሮ፣ ዘይት እና ሽንኩርት በገበያው ላይ ቀርበዋል፡፡
አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የበዓል ገበያውን ተመልክቷል፡፡
ወይዘሮ ዓመትባል ይታየው በሰሜን አቸፈር ወረዳ ጭንባ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ ወይዘሮ ዓመትባል በዓልን ጠብቀው ዶሮ ለከተማው ነዋሪ ያቀርባሉ፡፡ የዶሮ ገበያ ጥሩ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ የከተማው ነዋሪ ዓመትባሉን ለማድመቅ እየገዛ ነው ብለዋል፡፡ የመስቀል ደመራ በዓል በድምቀት እንዲከበር እና ማኅበረሰቡ የሚፈልገውን እንዲያገኝ የሚያደርጉት ሥራ እንደሚያስደስታቸውም ነግረውናል፡፡
ሌላው አስተያየት ሠጪ ዋሴ ሙሃባው ይባላሉ፡፡ መስቀል በመጣ ቁጥር ችቦ ከአርሶ አደሮች እየገዙ ለከተማ ነዋሪዎች ያቀርባሉ፡፡ ከችቦ ተጨማሪ ጨፌ እና አደይ አበባ እየሸጡም ነው፡፡ ወጣት ዋሴ ገበያው ሞቅ ደመቅ ያለ ነው ፤ ከአምናው ዘንድሮ የተሻለ ገበያ እየገበዩ እንደኾነም ነው የገለጹት፡፡
ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ሸማች በሰጡት አስተያየት የገበያው ድምቀት በዓሉን ሞቅ ደመቅ አድርጎ ለማክበር ይረዳል ብለዋል፡፡
ጨፌ ፣ዶሮ ፣ዘይት ፣ችቦ ፣በቆሎ በገበያው ላይ በብዛት የቀረቡ ሸቀጦች መኾናቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ዶሮ ከ400 ብር ጀምሮ እስከ አንድ ሺህ ብር እየተሸጠ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡ ዓመት ጠብቆ የሚመጣው የአደይ አበባ ለገበያ መቅረቡ ትዝታቸው ኾኖ እንዳይቀር እና ለልጆቻቸው ደስታን እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡ የደመራ ችቦም ከ50 ብር እስከ 60 ብር እየተሸጠ መኾኑን አስረድተዋል፡፡
አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በባሕር ዳር ከተማ ገዥ እና ሻጭ እኩል ገበያው ላይ ተገናኝተው እየተገበያዩ መኾኑንም ተመልክቷል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!