
ባሕር ዳር: መስከረም 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከትናንት ታሪካችን የተቀዳውን አሁናዊ ማንነታችን በውል መመርመር ሳያስፈልገን የቀረ አይመስልም፡፡
ወይ ትናንትናችን መምሰል፤ ካልሆነም ደግሞ ታሪካችንን ማንሰላሰል የሚጠይቀን ጊዜ ላይ ቆመናል፡፡ የትናንት ከፍታችን ቀና ብሎ መመልከት፤ ካልኾነ ደግሞ የወረድንበትን ቁልቁለት ዝቅ ብሎ መለካት ግድ ሳይል አልቀረም፡፡
እውነት ነው! ለስደተኞች እዝነትን ለተጠቁ ጉልበትን ከኢትዮጵያዊያን በላይ ማን አድርጎት ያውቃል፡፡
የተገፉን በመቀበል፤ አጥቂዎችን በማስታገስ ከኢትዮጵያ በላይ በምድር ላይ ማንስ የሰላም አምባሳደር ነበር፡፡
የጥቁር ሕዝቦች አርነት፤ የነጻ አውጭዎች ተምሳሌት ከምሥራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ኢትዮጵያ የተሻለ ዝና የትስ ነበር፡፡ ባርነትን አምርሮ የታገለ፤ ስለፍትሕ አብዝቶ የዘመረ ከኢትዮጵያዊያን የተሻለ ማን ነበር፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እ.አ.አ 1945 በሳንፍራንሲስኮ ሲመሰረት ጥቁሮችን ወክላ እና አፍሪካን ጠቅልላ አሻራዋን ያሳረፈችው ሀገር ኢትዮጵያ እንደነበረች አሁን ላይ እንደ ተረት የሚነገር እውነት ለመምሰል ተቃርቧል፡፡
1963 የያኔው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እና የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት ከብዙ ውጣ ውረድ እና ድካም በኋላ ሲመሰረት ኢትዮጵያ የነበራት ድርሻ ምን ያክል እንደነበር በወጉ ተሰንዶ ለትውልዱ መማሪያ ቀርቦ ይኾን፡፡ ሁላችንም ነጻ እስካልወጣን፣ እኩል እስካልኾንን እና የቆዳ ቀለምን መሰረት ያደረገ የበላይና የበታችነት ስሜት እስካልከሰመ ድረስ ዘረኝነት ባጠላበት የኦሎምፒክ መድረክ አልሳተፍም በማለት ለሌሎቹ ጠበቃ የቆመችው ሀገር ግን አሁናዊቷ ኢትዮጵያ ናት ብለው የሚጠይቁት በርካቶች ናቸው፡፡
በቅኝ ግዛት የጨለማ ዘመን ጥቁሮች የብርሃን ጭላንጭል እንዲመለከቱ የተስፋ እና ነጻነት ቀንዲል የኾነችው ሀገር በእርግጥስ ጥንታዊቷ አቢሲኒያ አሁናዊቷ ኢትዮጵያ ናት፡፡ “ታሪካችን እና ግብራችን፤ ስማችን እና ሰላማችን ግን ተጣጥመዋል?” እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ኢትዮጵያዊያን በየትኛውም የዓለም ሀገራት ቢጓዙ “ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ያከበሯቸው ሀገር ዜጎች” እየተባሉ ክብራቸው የላቀ እና አቀባበላቸው የደመቀ ነበር የሚሉት ፕሮፌሰር አደም ካሚል ሰላማዊ ዜጎች መባል መለያቸውም ነበር ይላሉ፡፡ እስከ ውጭው ዓለም ድረስ የሚከተለን መልካም ሥማችን ምንጩ ሀገራዊ ሰላማችን፣ የሰከነ ግንኙነታችን እና በውይይት የዳበረው ባሕላችን ነበር ነው ያሉት፡፡ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ አማኝ ሕዝብ ባለባት ሀገር ሰላም ማጣት እና በእርስ በእርስ ግጭት መናጥ ችግሩ የሕዝብ ሳይኾን ቤተ-እምነት እና ቤተ መንግሥት ላይ ያርፋል የሚሉት ፕሮፌሰር አደም የሃማኖት ተቋማት አስተምህሮ የሚፈተንበት ወቅት ላይ ናቸው ይላሉ፡፡
የመሪዎች ውስንነት እና ጉድለት እንዳለ ኾኖ የሃይማኖት አባቶች እና የሃይማኖት ተቋማት የተቋቋሙለትን ሰማያዊ ዓላማ እንዳልተወጡ ያመላክታል ብለዋል፡፡ በዓለም ላይ አንድ ሃይማኖት እና አንድ ቋንቋ ብቻ ያላቸው ሀገራት የእርስ በእርስ ጦርነት እና ግጭት ገጥሟቸው ምን ያክል እንደፈራረሱ ማየት ለኢትዮጵያዊያን ትምህርት ይኾናል ነው ያሉት ፕሮፌሰር አደም፡፡
ከሱዳን እስከ የመን፣ ከሊቢያ እስከ ሶማሊያ፣ ከኢራን እስከ ኢራቅ አሁን ላይ የገጠማቸውን የጦርነት ፈተና ማስተዋል ይገባል ነው ያሉት፡፡ ጦርነት እና ግጭት ሲገቡበት በሩ ሰፊ ቢኾንም መውጫ ቀዳዳው ጠባብ ነው የሚሉት ፕሮፌሰር አደም አንድ አካባቢ የሚነድ እሳት የሚጎዳው ሁሉንም ነው ብለዋል፡፡ የመሳሪያ ነጋዴዎች ሁልጊዜም የሚፈልጉት ክፍተት ነው፤ የእኛ ግጭት እና ጦርነት የመሳሪያ ነጋዴዎች ገበያ መኾኑን ማስተዋል ይገባል ነው ያሉት፡፡
ፕሮፌሰር አደም ከምንም በላይ ግን ሰላም አስከባሪ ልካ የሌሎችን ሀገራት ሰላም ያስከበረች ሀገር ዛሬ የራሷን ሰላም ማስከበር የሚሳናት ሀገር ኾናለች ሲባል መስማት መንግሥትን ብቻ ሳይኾን የሃይማኖት አባቶችን፣ የሃይማኖት ተቋማትን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን እና ምሁራንንም የሚያሳስብ ጉዳይ ሊኾን እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!