“ሙስሊሞች የመውሊድ በዓልን ሲያከብሩ የነብዩ ሙሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) አበርክቶ በማወደስ እና አስተምህሯቸውን በማስታወስ ሊኾን ይገባል” ሼህ ሙሐመድ አብራር

55

ባሕር ዳር: መስከረም 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ)1498ኛው የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የመውሊድ በዓል በባሕር ዳር ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል፡፡ በዓሉ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ሲከበር ኢማሞች፣ የሃይማኖቱ ተከታዮች እና ጥሪ የተደረገላቸው የከተማ አሥተዳደሩ የመንግሥት የሥራ ኅላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

የነብዩ መወለድ የፀሐይን ያክል ለሰው ልጅ ዋጋ ነበረው ያሉት የሰላም በር መስጅድ ኢማም ሼክ ሙሐመድ አብራር የነፍሳችንና የአካላችን እንዲሁም ነብዩ የሃይማኖታችን መሠረት ናቸው ሲሉ ገልጸዋቸዋል፡፡ ከነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በፊት 123 ሺህ የሚደርሱ ነብያት እና መልዕክተኞች መጥተው ነበር ያሉት ኢማሙ አንዳቸውም እንኳን እስልምናን ማጽናት ሳይቻላቸው አልፈዋል ነው ያሉት፡፡

ለሰው ልጅ ሕይወት መልካምነትና ለእስልምና ሃይማኖት መስፋፋት መሰረት ኾነዋል። ለጣኦት አምልኮ መቅረት የነብዩ ነብይ ኾኖ መምጣት ምክንያት እንደነበርም ተነስቷል፡፡ የፈጣሪን መኖር ካለማወቅ ወደ ማወቅ ለመሸጋገር ድልድያችን ነብያችን ነበሩ ያሉት ሼክ ሙሐመድ አብራር ከራስ በላይ ለሰው ማሰብን አስተምረውን አልፈዋል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች የነብዩን ልደት ሲያከብሩ አበርክቷቸውን በማወደስ እና አስተምህሯቸውን በማስታወስ ሊኾን ይገባል ያሉት ኢማሙ የተቸገሩን መርዳት እና ህሙማንን መጎብኘት በልደታቸው ቀን ኢስላም ሊፈጽመው የሚገባ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ኢትዮጵያን የሚወዱ እና ሐበሾችን የሚያከብሩ የአሏህ መልዕክተኛ ነበሩ ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ መልካም ዝና እና ክብር ሰላማዊ ሀገር ከመኾኗ የሚመነጭ ነው ያሉት ኢማሙ ”ስለ ሀገራችን ሰላም ከዱዐ በተጨማሪ ተግባራዊ ትብብር ማደረግ ይገባል” ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአሁን ያለውን አንጻራዊ ሰላም ወደ አስተማማኝ ሰላም ለማሸጋገር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል” የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ
Next articleየመስቀል በዓል አከባበር በገጠሩ የአገው ምድር!