1 ሺህ 498ኛው የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የልደት በዓል በታላቁ አንዋር መስጅድ እየተከበረ ነው።

52

አዲስ አበባ፡ መስከረም 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ነብዩ ሙሐመድ የጥሩ ሥነምግባር ምሳሌ፣ አዛኝ፣ ይቅር ባይ፣ የሰላምና የፍቅር አባት፣ ትሁት፣ ትዕግስተኛ እና እውነተኛ መሪ ናቸው ይሏቸዋል የሃይማኖቱ መሪዎችና ምሁራን። በነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) አስተምህሮ መሠረት እኛም በመተዛዘን፣ በመተሳሰብ፣ አብሮ ተካፍሎ በመብላትና በአንድነት በመቆም ልደታቸውን ልናከብር ይገባል ተብሏል።

የታላቁ አንዋር መስጂድ ኢማም ሼህ ጡሐ መሐመድ ሕዝበ ሙስሊሙ መውሊዱን ሲያከብር የነብዩን በጎ ሥራዎች በማስታወስና በመተግበር ሊኾን ይገባል ነው ያሉት። በዓሉ በቁርዓን የተጀመረ ሲኾን የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አመራሮች፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዛዳንት እና የመጅሊሱ አመራሮች፣ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሃፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር እና ሌሎችም ተገኝተዋል።

የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ሊዲያ ግርማ ባስተላለፉት መልዕክት ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ይቅር ባይና የሰላም አባት መኾናቸውን አንስተዋል። በዓሉን ስናከብር በአብሮነትና በአንድነት መኾን አለበትም ብለዋል። በተጨማሪም ስለሰላም በመሥራት እና ስለሰላም በመስበክ በዓሉን ማክበር ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ዋና ጸሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ባደረጉት የእንኳን አደረሳችሁ ንግግር በዓሉ የነብዩ መልካም ሥራና አርዓያነት የሚታሰብበት ነው ሲሉ ተናግረዋል። ነብዩ በችግር ጊዜ ሰሃቦችን ወደ ኢትዮጵያ ሂዱ ብለው ኢትዮጵያ የሰላምና የፍትሕ ሀገር መኾኗን የገለጡበ መኾኑ ደግሞ ኩራታችን ነው ብለዋል። ፈጣሪ አብሮነታችንን እና አንድነታችንን ስለወደደ የመስቀልን ደመራና የመውሊድን በዓል በአንድ ቀን እንድናከብር አድርጓል ሲሉም ተናግረዋል። በዓላትን ስናከብር በመቻቻል፣ በአንድነት እና በፍጹም ሰላማዊነት መኾን እንዳለበትም ዋና ጸኀፊው መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፡- ድልነሳ መንግስቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleእንኳን ለብርሃነ መስቀሉ አደረሳችሁ!
Next article“የመስቀል ዋና መልዕክቱ ጥላቻን መግደል ነው” ዳንኤል ሰይፈሚካኤል የሥነመለኮት መምህር