ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለመስቀል በዓል በሠላም አደረሳችሁ!

49

ኢትዮጵያ የበርካታ ባሕል፣ ወግ እምነትና ቅርሶች ሃብት ባለቤት ናት፡፡ በዓለም ማኀበረሰብ ዘንድ ሀገሪቱን ካስተዋወቋትና ዝናን ካተረፉላት መካከል ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ለሀገሪቱ ብሎም ለክልላችን የቱሪዝም ሃብት ምንጭ በመሆን በየጊዜው የቱሪስቶችን ቀልብ በመሳብ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶቿ ህያው ምስክሮች ናቸው፡፡

በተለይ በክርስትና ሃይማኖት አማኞች ዘንድ በየዓመቱ መስከረም 16 እና 17 የሚከበረው የደመራና የመስቀል በዓል ከማይዳሰሱ ቅርሶች አንዱ ሲሆን ይህ በዓል የሀገሪቱን መልካም ገፅታ በማጉላት በኩል ፋይዳው የላቀ ነው፡፡ የመስቀልን በዓል ከሌሎች ሃይማኖታዊ በዓላት ለየት የሚያደርገው አሮጌውን ዓመት በምስጋና ሸኝተን አዲሱን ዓመት በተስፋ በተቀበልንበት ማግስት የሚከበር በዓል በመሆኑና የተስፋ፣ የልምላሜና ጥልን በመስቀሉ ድል የምናደርግበት እንዲሁም ለሥራ የምንነሳሳበት ወቅት በመሆኑ ነው።

በዓሉን ለመታደም በየዓመቱ ከሀገር ውጭ ለሚመጡ ጎብኝዎች መንፈሳዊ እርካታን ከመስጠት ባሻገር የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ የምናደርግበትና ትልቅ ሚና እንዲጫወት የምናደርግበት ነው፡፡

ሕዝበ ክርስቲያኑ የመስቀል በዓልን ሲያከብር በሃይማኖቱ አስተምህሮ መሰረት ጥልን በመስቀሉ አጥፍቶ፣ በላቀ መተሳሰብ፣ መረዳዳትና አንድነትን በማጉላት፣ የሃይማኖት አባቶች በየጊዜው የሚሰጡትን አባታዊ ምክርና የሰላም ጥሪ ተገቢውን ምላሽ በመስጠት፣ በመደማመጥ፣ ችግሮችን በውይይት በመፍታት እና የተረጋጋ ሠላምን ለማምጣት ጥረት በማድረግ ሊሆን ይገባል፡፡

በድጋሚ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ መልካም የመስቀል በዓል እንዲሆንላችሁ እንመኛለን!!

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ

መስከረም 16/2016 ዓ.ም

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሐረሪ ክልል 1498ኛው የመውሊድ በዓል እየተከበረ ነው።
Next articleእንኳን ለብርሃነ መስቀሉ አደረሳችሁ!