ጠቅላይ ሚኒስትሩ በታገቱ የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጉዳይ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ ዓለም አቀፍ የአማራ ኅብረት ጠየቀ፡፡

209

ባሕር ዳር፡- ጥር 18/2012ዓ.ም (አብመድ) መንግሥት ጸጥታውን እንዲያስከብርና የሰዎች ህይዎት በከንቱ እንዲያልፍ አድርገዋል የተባሉ ግለሰቦችንም ተጠያቂ እንዲደርግ ዓለም አቀፍ የአማራ ኅብረት ጠይቋል፡፡

በኅብረቱ የአደረጃጀት ጉዳይ ተጠሪ አቶ ደህናሁን እምሩ ከአብመድ ጋር ባደረጉት ቆይታ በፀጥታ ስጋት ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲመለሱ የታገቱ የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጉዳይ እልባት ሊሰጠው እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡ ዓለም አቀፍ የአማራ ኅብረት ድርጊቱን እንደሚያወግዘውም ነው የተናገሩት፡፡ መንግሥት የተማሪዎቹን መለቀቅ ቢያሳውቅም ከወላጆቻቸው ጋር መገናኘት ባለመቻላቸውና ያሉበት ሁኔታም ባለመታወቁ ጉዳዩ ይበልጥ ውስብስብና አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱንም ተናግረዋል፡፡

የተማሪ ወላጆችና ሕዝቡ እየተጨነቁ ባሉበት በዚህ ወቅት መንግሥት ዝምታን መምረጡ ተገቢነት የለውም ብሏል ኅብረቱ፡፡ ስለ ጉዳዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ማብራሪያ ሊሰጡ እንደሚገባም ጠይቋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሃገሪቱን ሠላምና ደህንነት በተመለከተ ወደ ውጭ ሃገራት ሄደው ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ባነጋገሩበት ወቅት የገቡትን ቃል እንዲያከብሩ፣ የሰዎች ህይወት በከንቱ እንዲያልፍ አድርገዋል የተባሉ ግለሰቦችንም ተጠያቂ እንዲደርጉ ነው ኅብረቱ የተየቀው፡፡

መንግሥት ተማሪዎቹ ተለቅቀዋል ብሎ ከዚህ ቀደም መግለጫ ስለሰጠበት ጉዳይም በአደባባይ ለሕዝብ ማሳወቅ እንዳለበት አቶ ደህናሁን ተናግረዋል፡፡ ኅብረቱ በታገቱ ተማሪዎችና እየደረሱ ባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዙሪያ በዋሽንግተን ዲሲ ትናንት ሲመክር መቆየቱንም አስታውቀዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የአማራ ኅብረት በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መስኮች የአማራን ሕዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ ተበታትነው የሚሠሩ አካላት ወደ አንድ እንዲመጡና ጠንካራ ኅብረት እንዲፈጠር ያለመ የሲቪክ ኅብረት ነው፡፡

ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ

Previous article“ይህን የመሰለ ከባድ የእናቶች ሁለተኛ የምጥ ሰዓት ላይ እንዴት አስችሎዎት ዝም አሉ?” ታማኝ በየነ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
Next articleጠቅላይ ሚኒስትሩ በታገቱ የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጉዳይ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ ዓለም አቀፍ የአማራ ኅብረት ጠየቀ፡፡