“ሐረር የፍቅር ልዕልት፣ የመዋደድ ንግሥት”

82

ባሕር ዳር: መስከረም 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ፍቅር ያለማቋረጥ የሚፈልቅባት ዥረት፣ መዋደድ የነገሠባት ቤተ መንግሥት፣ አብሮነት የሚገለጥባት መስታውት ናት፡፡ እርሷ ጥላ ናት ሁሉም በጋራ የሚያርፍባት፤ እርሷ ጥንታዊት ምሥራቅ ናት የፍቅር ብርሃን የማይጠፋባት፣ እርሷ የፍቅር መሶብ ናት በአንድነት የሚመገቡባት፣ እርሷ ውበት ናት በአንድነት የሚያጌጡባት፣ እርሷ ሐይቅ ናት በፍቅር የሚዋኝባት፣ እርሷ ያማረች ምንጭ ናት የመውደድ ውኃ የሚቀዳባት፡፡

በፊት በኋላ፣ በግራ በቀኟ መወደድ ያከበራት የፍቅር ልዕልት፣ ስለ ፍቅሯ የእጅ መንሻ የሚቀርብላት፣ የመወደድ ስጦታ የሚሰጣት፣ ለመረማመጃዋ የወርቅ ምንጣፍ የሚጣልላት፣ ያማረውን ጫማ የሚያጫሟት፣ የተዋበውን ዘውድ የሚደፉላት የፍቅር ንግሥት ናት፡፡

ቢዘያች ምድር ሰዎች ከሰዎች ጋር አይደለም እንሰሳት ከሰዎች ጋር ይኖራሉ፣ ፍቅር ታስተምራለች እና ተናካሽ እንስሳት መናከስን ረስተው ፍቅርን ይሰጣሉ፣ ፍቅር ከኾኑት ፍቅርን ይቀበላሉ፣ በፍቅርም ይኖራሉ፣ በዚያች ከተማ የሚኖሩ ለሰዎች አይደለም ለዱር እንስሳት ቆርሰው ያጎርሳሉ፣ ቀድተው ያጠጣሉ፣ በዚያች ምድር ጨለማን ተገን አድርገው የሚወጡት፣ ከሰው ጋር የማይስማሙት እንስሳት ከሰዎች ጋር በከተማ ይኖራሉ፣ እንደ ሰዎቹ ሁሉ ፍቅር ተምረው ፍቅርን ያስተምራሉ፡፡

የመሥራቅ ኮከብ ናት ታሪክ ደምቆ የሚታይባት፣ ተወዳጅ ስም ናት ብዙዎች በፍቅር የሚጠሯት፣ ሐረር ቅርስ ናት የአበው የእጅ ሥራ ያደመቃት፣ ሐረር ምስክር ናት የዘመናት ታሪክ የሚነገርባት፣ ሐረር ድንቅ ናት የአበው ድንቅ ሥራ የጀጎል ግንብ ግርማን የሰጣት፣ ውበትና መውደድን ያላበሳት፡፡ ሐረር ስትነሳ ያ ረጅም ዘመንን ያስቆጠረው ጀጎል ይነሳል፣ ሐረር ስትታወስ ፍቅር ይታወሳል፣ ሐረር ስትዘከር መዋደድ ይዘከራል፣ ሐረር ሲነገርላት ጥንታዊነቷ ይነገራል፣ ይዘከራል፡፡

በዚያች ከተማ ከዘመን ዘመን የተሸጋገረ የፍቅር ዥረት አለ የደረሰ ሁሉ እየጠጣ የሚረካበት፣ በዚያች ከተማ ከጥንት እስከ ዛሬ የቆዬ የመዋደድ፣ የአብሮነት፣ የአንድነት፣ የግልጽነትና የደግነት ማዕድ አለ የደረሰው ሁሉ የሚጎርስበት፣ በዚያች ምድር ከዘመን ዘመን የማይደበዝዝ ውበት አለ የደረሰ ሁሉ በጋራ የሚያጌጥበት፡፡

ሐረር ሃይማኖት ይሰበክባታል፣ ታሪክ ይነገርባታል፣ የአበው ብልሃት ይገለጥባታል፣ የነዋሪዎቿ ሰው ወዳድነት ይታይባታል፡፡ በዚሕች ከተማ በዓላት ደምቀው ይከበራሉ፤ ሐረሬዎች በዓልን ማድመቅ ይችሉበታልና፡፡ ታሪኩን፣ ሃይማኖቱን እና እሴቱን ሳይለቅ በውብ ሰዎች ውብ ኾኖ ይከበራል፡፡

የታሪክና የባሕል ተመራማሪ ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ የሐረር ባሕልና ታሪክ ላይ ይመራመራሉ አዩብ አብዱላሂ፡፡ ሐረር ከእስልምና ሃይማኖት ጋር መቼ እንደተዋወቀች፣ የነብዩ መሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) የመውሊድ በዓልንስ እንዴት አድርጋ ስታከብር እንደኖረች ጠየቅናቸው፡፡ እሳቸውም ከጥንቱ እስከዛሬ ያለውን ነግረውናል፡፡ መቼም ስለ ሐረር በአንድ ጀንበር ተነገሮም፣ በአንድ ጀንበር ተጽፎም መጨረስ አይቻልም፤ ከጠለቀው ታሪኳ ጥቂቱን ነገሩን፣ እኛም ጥቂቱን ሰማን እንጂ፡፡

አዩብ አብዱላሂ ሐረር ፍቅር የሚኖርባት፣ ፍቅርም የመላባት ከተማ ናት ይሏታል፡፡ ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) እያሉ ሐረር ላይ እስልምና ተሰብኳል፣ በዚያ ዘመን ከሂጃዝ እስከ ሐረር የተዘረጋ ንግድ ነበር፡፡ ነጋዴዎችም ከአንደኛው ሀገር ያለውን ወደ ሌላኛው ሀገር ይወስዳሉ፣ ከዚያኛው ሀገርም ሌላ ይዘው ይመጣሉ፡፡ በዚህም ጊዜ ወደ ሐረር የሚመጡ ነጋዴዎች ስለ እስልምና ሃይማኖት ያወቁትን በሐረር ይመሰክሩ ነበር ነው ያሉን፡፡

ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በሐረር የሚባል አንድ አባባል አለ አሉን፡፡ እርሱም አባባል “ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ኾይ በዓይን አላየነወትም፣ በወሬ ነው የሰማነወት፣ ነገር ግን ተቀብለነወታል” የሚል፡፡ ሐረሪዎች ገና ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በሕይወት እያሉ በአስተምህሯቸው ተማርከው፣ በዓይን ሳያዩዋቸው፣ ከእግራቸው ስር ቁጭ ብለው ሳያስተምሯቸው ዝናቸውን ሰምተው እንደተቀበሏቸው እና በአስተምህሯቸው እንዳመኑ ሲናገሩ ነው ይሄን የሚሉት፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ከመጡት መልእክተኞች መካከል የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ልጅ ሩቅያ ነበረች፡፡ ሩቅያም ወደ ሀገሯ በተመለሰች ጊዜ ከባለቤቷ ጋር ወደ ሐረር መጥተው ነበር ይላሉ አዩብ የዚያን ዘመን ታሪክ ሲያነሱ፡፡

ሐረር ውስጥ ሰባት መንደሮች ነበሩ፡፡ ከሰባቱ መንደሮች መካከል አንደኛዋ ሩቅያ ትባል ነበር፡፡ እነዚህ መንደሮች አንድ ላይ ኾነው ሐረርን መሠረቷት ነው ያሉን ተመራማሪው፡፡ ከአመሠራረቷ ጀምሮ አንድነት ያለባት ይህች ጥንታዊት ከተማ በአንድነት እና በፍቅር ዘለቀች፡፡ ሩቅያ ሐረር ላይ እዳረፈች ታሪክ ይናገራልም ብለውናል፡፡ የታሪክና የባሕል ተመራማሪው እንደነገሩን ሐረር ላይ የተሰበከው የእስልምና ሃይማኖት ወደ ምሥራቅ አፍሪካ ሁሉ ተስፋፍቷል፣ በአፍሪካ ውስጥ ሦስት የእስልምና ሃይማኖት ማስፋፊያ ማዕከሎች አሉ የሚሉት ጋሽ አዩብ ሐረር ደግሞ አንደኛዋ ናት፡፡ ቲምቡክቱ እና ሞሮኮ ራባት ሌሎች የእስልምና ማዕከላት እንደበሩ ታሪክ ያስረዳል ይላሉ፡፡ የሐረር ማዕከልነት ግን ጥንታዊ ነው ይሉታል፡፡

ይህች ጥንታዊት ከተማ ከእስልምና ሃይማኖት ጋር የሚያቆራኛት ብዙ ነው፡፡ የቢላል አል ሐበሺ የዘር ግንድ የሚመዘዘው ከዚችው ድንቅና ጥንታዊት ከተማ እንደኾነም ነግረውናል፡፡ ሐረር እስልምናን በፍላጎት የተቀበለች፣ የሃይማኖት ማስፋፊያ ማዕከል ተብላ የተመረጠች፣ የቢላል የዘር ግን መነሻ የኾነች በመኾኗ ታላቅነቷን ያጎለዋል ይሏታል፡፡ ጋሽ አዩብ እንደነገሩን በሐረር ሰባ ሁለት አሚሮች ተነስተዋል፤ ሥርዓት፣ ሃይማኖት እና እሴት እየተቀባበሉ ሐረርን አስተዳድረዋል፡፡ በዘመናቸውም ደማቅ ታሪክ ጽፈዋል፡፡

የሐረር ሁለተኛው አሚር ሼህ አባድር ከሐረር ተነስተው በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች እየተመላለሱ፣ እየወጡ እየወረዱ የእስልምና ሃይማኖትን ማስተማራቸውንም ጋሽ አዩብ ታሪክ መዝዘው ይናገራሉ፡፡ ሐረር በሃይማኖት፣ በታሪክ እና በሥርዓት ታላቅ ስም ያላት ከተማ መኾኗንም ታሪክ ይዘክራል፡፡

ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በሕይወት እያሉ እስልምና የተሰበከባት ሐረር፣ ፍቅርና መዋደድ የነገሠባት ሐረር፣ መልካም ነገር የማይጠፋባት ሐረር ከመጀመሪያው አሚር ሀቦባ ጀምሮ እስከ ሰባ ሁለተኛው አሚር ድረስ አያሌ ታሪኮችን ቀርጻለች፣ ዓለምን ያስደነቀ፣ ኢትዮጵያን ያደመቀ ጀጎልንም አንጻለች፣ ያነጸች ብቻ አይደለችም ጠባቂም ናት እንጂ፤ ለዓመታት የአበውን ቅርስ ከእነ ውበቱ ስትጠብቀው ኖራለች፡፡ ዛሬም ታሪክ እየጠበቀች፣ መልካም ታሪክ እየሠራች፣ የትናንት እና የትናንት ወዲያ ሕያው ምስክር ኾኖ በግርማ ተቀምጣለች፡፡

ሐረር ከተማ ብቻ አይደለችም ታሪክ የሚነገርባት የታሪክ መጽሐፍ ናት፣ ጥንታዊነት የሚነበብባት፣ ሐረር ቀለም ናት የትናንት ውብ ታሪክ የተቀረጻባት፣ ደምቆም የሚታይባት፣ ሐረር ሥርዓት አክባሪ ናት ሥርዓት የሚነገርባት፣ ሐረር ቅርስ ናት ጥንታዊ ቅርሶች የሚገኙባት፣ ሐረር ከተማ ብቻ አይደለችም ፍቅር የሚቀዳባት ውቅያኖስ ናት፣ ሐረር መውደድ የሚለቀምባት የትርንጎ ዛፍ ናት፣ ሐረር ትናንትና ዛሬ የሚታይባት መስታውት ናት፡፡ ሐረር ጥንታዊት ብቻ አይደለችም ነገን ማያ የዘመን መስኮት ናት እንጂ፡፡

ሐረር የረቀቁ ቅርሶችን የሠራች፣ ቅርሶቿን ጠብቃ ያኖረች፣ ከአባት ወደ ልጅ በሚተላለፈው ጥበቧን እየጠበቀችና ለትወልድ እያስተላለፈች ያለች ጥንታዊት ከተማ ናት፡፡ ጋሽ አዩብ ሐረርን ሲገልጿት የአፍሪካ የእስልምና እምብርትና ወራሽ ናት ይሏታል፡፡

ሐረር የእስልምና ሃይማኖት በዓላት በድምቀት ይከበሩባታል፡፡ ከበዓላት አንደኛው ቀደም ብላ አስተምህሮታቸውን የተቀበለቻቸው የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የልደትን (መውሊድ) በዓል አድምቃ ታከብራለች፡፡ ጋሽ አዩብ እንዳሉኝ የሐረር ሰዎች ነብዩ መሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) አብዝተው ይወዷቸዋል፤ ለመውደዳቸው እና ለክብራቸው መገለጫ ይኾናቸው ዘንድም በሐረር አራት ወራት በነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የልደት ቀናት ይጠራሉ፡፡ ልደታቸውም በእነዚያ ወራት ይከበራል፡፡ አራቱም ወራት በእርሳቸው የመውሊድ ስም ይጠራሉ፡፡ መውሊድ አንድ፣ መውሊድ ሁለት፣ መውሊድ ሦስት እና መውሊድ አራት እየተባሉም ይጠራሉ፡፡

በነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የመውሊድ ቀን በሐረር የሚደረገውን ሲነግሩን “የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የመውሊድ ቀን የሐረር ሴቶች እጣን አጭሰው በአንድነት እልል ይላሉ፡፡ ልክ አዲስ ሕጻን እንደተወለደ ሁሉ በመውሊድ ቀን ምሽት አንድ ሰዓት ገደማ እልልታው ይቀልጣል፡፡ ጀጎል ከዳር እስከ ዳር በእልልታ ትመላለች፡፡ በደስታና በውዳሴ ድምጽ ትናወጻለች፣ ሴቶች የእሳቸውን ስም እየጠሩ በአንድነት እልል ይላሉ” ነው ያሉን፡፡

የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የመውሊድ በዓል በድምቀት መከበር ከአያት ከቅድመ አያት የቆዬና ዛሬም ልጆቹ ያስቀጠሉት መኾኑን ነው የነገሩኝ፡፡ በመውሊድ ቀን ምሽት ጀምሮ የእርሳቸው ታሪክ በዜማና በንባብ ይነገራል፡፡ ለእሳቸው የተገባው ውዳሴ ይቀርባል፡፡ የመውሊድ በዓል ነሺዳ እየተደረገ፣ ሙረሽዶች ነሺዳውን እያደረጉ፣ ዜማ እየተዜመ ደምቆ ይከበራል፡፡ የእርሳቸውን መውሊድ ለማሰብ የሃይማኖት አስተማሪዎች፣ ለሀገርና ለሕዝብ ዱዓ የሚያደርጉ ሽማግሌዎች ዘንድ እየተሄደ ይከበራል፡፡ ታላላቆቹ ይዘየራሉ፣ ዱዓም ይደረጋል፡፡

ታላላቆቹ፣ ታናናሾቹ ሁሉም በእርሳቸው መወለድ ደስ እየተሰኘ ያስባቸዋል፣ ስማቸውን እየጠራ ያወድሳቸዋል፡፡ ይሄንንም እያደረጉ ኖረዋል፣ ዛሬም ያደርጋሉ፡፡ ሐረር የፍቅር መንደር፣ የመዋደድ አድባር፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“እዝነትን የሚያደርጉ፣ በፍትሕ የተከፉትን የሚያረጋጉ”
Next articleመውሊድ በዓለም ላይ!