“እዝነትን የሚያደርጉ፣ በፍትሕ የተከፉትን የሚያረጋጉ”

29

ባሕር ዳር፡ መስከረም 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በፈጣሪ ትዕዛዝ ተልከዋል፣ የፈጣሪን ትዕዛዝ ይፈጽሙ ዘንድ ተዘጋጅተዋል፣ በፈጣሪ ዘንድ የተወደደውን እና የተመረጠውን አድርገዋል፣ እኩልነትን ሰብከዋል፣ ሰዎችንም በእኩል ዓይን አይተዋል፣ በምድሯ ሁሉ እኩልነት ይኖር ዘንድ ሕግ አስቀምጠዋል፤ ፍቅርና ሰላምን አቅርበዋል፤ ዘረኝነትን እና ጥላቻን አርቀዋል ይሏቸዋል፡፡

በረሃ ባየለባት ምድር ጉልበታሞች ጉልበት የሌላቸውን ያሳድዷቸው፣ መከራና ስቃይ ያበዙባቸው፣ እንደፈለጉ ይገዛቿው እና ይነዷቸው ነበር፤ የነገሥታቱ፣ የመኳንንቱና የመሳፍንቱ ወገን የኾኑት ይከበራሉ፣ ከሃብት ላይ ሃብት ይደርባሉ፣ ከግርማ ላይ ግርማ ይጨምራሉ፣ የተዋበውን ለብሰው የሚጣፍጠውን ይመገባሉ፣ በእንቁ የተንቆጠቆጠውን ደርበው እጅግ የተወደደውን ይጠጣሉ፣ ለእግራቸው መጫሚያ በእንቁ የተዋበ ያደርጋሉ፣ ሲጠሩት አቤት፣ ሲልኩት ወዴት የሚል አሽከር እንደ አሻቸው ይገዛሉ፣ ይነዳሉ፡፡

ወገናቸው ከነገሥታቱ፣ ከመሳፍንቱና ከመኳንንቱ ያልኾኑት ደግሞ በባለጊዜዎች ይገዛሉ፣ ይሸጣሉ፣ ፍትሕን ተጠምተው በስቃይና በመከራ ይኖራሉ፡፡ አድራጊ ፈጣሪዎቹ ባለጊዜዎቹ ናቸው፡፡ ሌሎች ግን ባለጊዜዎቹ አድርጉ የሚሏቸውን ያደርጋሉ፣ የታዘዙትን ሳያጓድሉ ይፈጽማሉ፡፡ ያን ባያደርጉ ግን ቅጣታቸው የከፋ ነበር፡፡

ያቺ በረሃ የበዛባት፣ እንዳሻ ጉሮሮን የሚያርስ ውኃ የማይቀዳባት፣ አናት የምትበሳን ፀሐይ ይጠለሉባት ዘንድ ልምላሜ ያላቸው ዛፎች እንደ ፈለጉ የማይታዩባት የበረሃ ምድር፣ ድርቅና ችግርም በርትቶባት ነበር ይባላል፡፡ እንስሳትና ሰዎችም በረሃብ ይሞታሉ፤ ሹማምንቱ ግን በደስታና በፌሽታ ዓለማቸውን ይቀጫሉ፡፡ ከቤተመንግሥታቸው በአጀብ እየወጡ፣ በአማረ ሰረገላ ተቀምጠው፣ በየጎዳናዎቿ ይመላለሳሉ፡፡ ምድር አዝመራ በከለከለችበት፣ ርሃብና ጠኔ በበረከተበት፣ መከራና ጥም ባየለበት በዚያ ዘመን ሰዎች ሁሉ ፍትሕን ናፍቀው፣ እኩልነትን ተጠምተው ነበር ይላሉ አባቶች፡፡ እንደ አባቶች ገለጻ በዚያች ምድር አምላክን ማምለክ ቀርቶ ለጣዖታት መስገድ፣ ጣዖታትንም ማምለክ ተበራክቶ ነበር፡፡

በዚያም የከፋ ዘመን ከፈጣሪ ዘንድ የተመረጡ ነብይ ወደ ምድር መጡ፡፡ ፍትሕ ያጡ ወገኖችም የልባቸውን መሻት የሚፈጽሙ ነብይ አገኙ ይላሉ አባቶች፡፡ ምድርም ጥላዋን አገኘች፣ የተጠማችውን ፍትሕ ማግኛዋን፣ የተራበችውን እዝነት መመገቢያዋን አገኘች ይላሉ የእምነቱ አስተማሪዎች፡፡ እሳቸው ለረህመትና ለእዝነት የተላኩ ነብይ ናቸውና፡፡ ትዕግሥታቸው ይሄን ያክል ተብሎ አይገለጽም፣ ለፍጥረታት ሁሉ ያዝናሉ፣ ያስባሉ ይላሉ፡፡

የፈጣሪን መልእክት ያደርሱ ዘንድ የተላኩት፣ በፈጣሪም ዘንድ ለዓለማት እዝነትን ላክን የተባሉት ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) እዝነታቸው፣ ጥበባቸው፣ ትዕግሥታቸው፣ አስታዋይነታቸውና አርቆ አሳቢነታቸው ግሩም ነው ይሏቸዋል፡፡ አብዝተው የታመኑ ነበሩና ስማቸው ሙሐመድ ኾኖ ሳለ በታማኝነታቸው ታማኙ የሚል ስም ተጨመረላቸው፡፡ እሳቸው አደራን የሚያከብሩ ታላቅ ናቸውና፡፡

በዚያች ፍትሕ በታጣባት ምድር የመጡት ነብይ መከራ በዛባቸው፣ መከራም ጸናባቸው፣ እሳቸውን ብለው የተከተሏቸው፣ ቃላቸውን ሰምተው ሞታችን ከእርስዎ ጋር ያድርገን፣ የእርስዎ ፈጣሪ ይጠብቀን ያሉ ሁሉ መከራ ደረሰባቸው፡፡ እሳቸው ግን ለታላቅ ነገር የተመረጡ ነበሩና መከራውን እና ችግሩን በጽናት ቻሉት ነው የሚሏቸው፡፡

በሐረር ታላቁ ጃሚ መስጂድ ኢማም ዑስታዝ አብዱልሀኪም ሙሐመድ፣ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የጠለቀ የአመራር ብቃት ያላቸው፣ በሁሉም ባሕሪያቸው፣ በሁሉም ሕይወታቸው ለሰዎች ሁሉ አርዓያ የሚኾኑ ናቸው ይሏቸዋል፡፡ ለእሳቸው ከኀይል ይልቅ ፍቅርን፣ ከጥላቻ ይልቅ ሰላምን፣ ከመለያየት ይልቅ አንድነትን የመረጡ፣ ያንም ያስተማሩ በሁሉም ተምሳሌት የኾኑ ናቸው፡፡ ተከታዮቻቸው ጥበብ በተመላበት መንገድ መምራት ብቻ ሳይኾን ዝቅ ብሎ መምራትንም ያስተማሩ፣ ዝቅ ብሎ በመምራት ከአላህ ዘንድ ክብር እንደሚገኝ ያሳዩ ናቸው ይሏቸዋል፡፡

ፍትሕ በተጓደለበት፣ ባለስልጣናቱ እና ባለሃብቱ ብቻ በሚደሰቱባት ምድር ተወልደው ሁሉም እኩል ይኾን ዘንድ አስተማሩ፣ አዋጅ ነገሩ፡፡ እርስ በእርስ የሚጨፋጨፉትን መለሷቸው፣ ለሴቶች ክብርና መብትን ሰጧቸው፣ ሰዎችም ሁሉ እኩል ይኾኑ ዘንድ አደረጓቸው ነው የሚሏቸው፡፡

እሳቸው ሰው የመኾንን ትርጉም ያስተማሩ፣ ከራሳቸው በላይ ለሰዎች የሚያስቡ፣ ታናናሾችንም ፣ታላላቆችንም የሚያከብሩ፣ የሚያዝኑትን የሚያስተዛዝኑ ለሰዎች ብቻም ሳይሆን ለእንስሳትም የሚያዝኑ ታላቅ ነብይ ናቸውም ይላሉ፡፡ እሳቸው ለሰዎች አይደለም፣ ለእንስሳትም ፍትሕን ያደርጋሉ፣ ስቃይ እንዳይደርስባቸውም ይከለክላሉ፡፡ ሁሉም እኩል እንዲኾኑ በድንቅ ጥበብ ያስተማሩ፣ የመሩ ናቸው፡፡ የማያዝን አይታዘንለትም፣ የሚያዝን ግን አላህ ያዝንለታል የሚል ትምህርት መስጠታቸውንም ነግረውናል፡፡

ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በራሳቸው ላይ በደል ያደረሱባቸውን ሰዎችም በደል እንዲደርስባቸው ሳይኾን ይቅር ይባሉ ዘንድ ለፈጣሪያቸው የሚለምኑ ነብይ ናቸውም ይላሉ፡፡ ነብዩ ሙሐመድ ፍትሕ በተናፈቀባት ምድር፣ ፍትሕም በናፈቁ ሕዝቦች መካከል የተገኙ ናቸው ይላሉ የሃይማኖቱ አባቶች፡፡

ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ለነብይነት ከመላካቸው አስቀድሞ ታማኙ ሙሐመድ እየተባሉ የሚጠሩ ታማኝነትን ከልጅነት ዘመናቸው ጀምረው ጠብቀው የኖሩ ታላቅ ሰው እንደኾኑም ነግረውናል፡፡ እሳቸው ለነብይነት አስቀድመው የተመረጡ፣ ታማኝነትን የራሳቸው ያደረጉ፣ ትዕግሥተኛ፣ ብልሃተኛ እና ደግ አድራጊ ናቸው፡፡ ዑስታዝ አብዱልሃኪም ስለ እሳቸው ሲናገሩ ሰዎች በተጣሉ ጊዜ ወደ እርሳቸው ይሄዳሉ፣ እሳቸውም በፍትሕ አዋቂነታቸው ፍርድን ይፈርዳሉ፣ በፍርዳቸው ሁሉም ተስማምተውና ተደስተው ይመለሳሉ ነው ያሉን፡፡

በፍርድ አዋቂነታቸው እና በፍትሐዊነታቸው የሚተማመኑት ሰዎችም የጨነቀ ነገር በገጠማቸው ጊዜ ወደ እርሳቸው እየሄዱ ትክክለኛ ፍርድን እየተቀበሉ ይመለሱ ነበር፡፡ እሳቸው አንድ ሰው ሊያናድዳቸው በሞከረ ጊዜ አይናደዱም፣ ይልቅስ ሊያናድዳቸው የመጣውን ሰው መልካም ነገርን አድርገው ይመልሱታል፤ ክፉውን በክፉ አይመልሱም ነው ያሉኝ ዑስታዝ አብዱልሀኪም፡፡

ነብዩ ሙሐመድ ድሆች እንዲረዱ የሚያዝዙ፣ ለድሆች በመስጠትም ደስታ እንደሚገኝ የሚያስተምሩ፣ ትርፍ ማለት ለተቸገረ መስጠት እንደኾነ የሚያሳዩ፤ የሰውን ሀቅ አትንኩ፣ ሀቅንም ስጡ፣ ሰውንም በክፉ ነገር አትናገሩ የሚሉ ናቸው ይላሉ መምህሩ፡፡

በቤታቸውም ቢኾን፣ በሌሎች ሰዎችም ቢኾን እዝነትን እና ደግነትን ያደርጋሉ፡፡ እሳቸው ካላቸው ነገር የሚቆጥቡት የላቸውም፣ ያላቸውን ሁሉ ለሌሎች ይሰጣሉ ነው ያሉኝ፡፡ በአንድ ወቅት ለተቸገሩ ስጡ ብለው አዘዙ፤ ታዛዦችም የተባሉትን አደረጉ፡፡ የተረፈውንም ወስደው ነብያችን ይሄው ይሄ ተርፏል ብለው አሳዩዋቸው፡፡ እሳቸው ግን የተረፈው ያመጣችሁት ሳይኾን ለሰዎች የሰጣችሁት ነው፡፡ ያ ከአላህ ዘንድ ይቆያልና አሏቸው ነው ያሉት፡፡

እሳቸው በትዳርም አርዓያ ናቸው፣ ሃይማኖትን በመምራትም አርዓያ ናቸው፤ ሀገር በመምራትም አርዓያ ናቸው፤ የተስተካከለ ፍርድ በመፍረድ፣ ፍትሕን በማወቅም አርዓያ ናቸው ነው ያሉን፡፡ የተስተካከለውን ፍርድ ይፈርዳሉ፣ የተስተካከለውንም ያደርጋሉ፣ እዝነትን እና ፍትሕን ሁልጊዜም ይሰጣሉ፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleቅዱሷ ከተማ – መካ
Next article“ሐረር የፍቅር ልዕልት፣ የመዋደድ ንግሥት”