
ባሕር ዳር: መስከረም 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የትውልድ ሥፍራ ናት ፤ በነብዩ ኢብራሂም (ዐለይሂ ሰላም) እንደተመሠረተችም ይነገራል። በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ቅዱሷ ከተማ እየተባለች ትጠራለች ፤ በምዕራብ ሳዑዲ አረቢያ “ሂጃዝ” አየተባለ በሚጠራው አካባቢ የምትገኘው መካ ከተማ።
ቅዱሷ ከተማ በተራራ የተከበበች ስትኾን በበጋው ወቅት የሙቀት መጠኗ እስከ 40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ይደርሳል፡፡
እ.አ.አ በ2020 በተደረገው ቆጠራ ከ2 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እንደሚኖርባት ይነገራል፡፡ በሕዝብ ብዛቷ ከሳዑዲ አረቢያ ከተሞች ከሪያድ እና ጅዳ በመቀጠል በሦስተኛ ደረጃ ላይ ትቀመጣለች፡፡
ከአፍሪካ እና ከሩቅ ምሥራቅ የሚመጡ ነጋዴዎች መተላለፊያ መንገድም ኾና አገልግላለች፡፡ በተለይም ደግሞ ከቀይ ባሕር በቅርብ ርቀት ላይ መገኘቷ ለየመን፣ ሶሪያ፣ ኢራቅ፣ ኢራን እና ለምሥራቅ አፍሪካ በተለይም ደግሞ ለኢትዮጵያ ባላት ስትራቴጅካዊ አቀማመጥ የንግድ ማዕከል እንድትኾንም አድርጓታል። ቅመማቅመም፣ መድኃኒት፣ ጨርቃጨርቅ፣ እህል፣ ሽቶ፣ ወርቅ፣ ብር እና ሀር የመሳሰሉ ሸቀጦች ልውውጥም ይካሔድባት እንደነበር ይነገራል፡፡
የሰው ልጆች አሏህን እንዲያመልኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በመላዕክቶች አማካይነት መስጅድ የተሠራባት ቦታ ናት፤ አደም ሰባት ጊዜ ተመላልሰው የጎበኟት ቅድስት ስፍራም እንደኾነች ይነገራል፡፡ ነብዩ መሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) ከአሏህ ውጭ የሚመለክ የእውነት አምላክ እንደሌለ በሚያስተምሩበት ጊዜ ሕዝቡ በማመጹ አሏህ ዓለምን በጎርፍ ሲቀጣ ከጥፋት የተረፈች ቅዱስ ቦታ ናት።
ነብዩ ኢብራሂም ልጃቸውን ኢስማኤልን እና ባለቤታቸውን ይዘው ወደ መካ እንዲጓዙ በአሏህ የታዘዘባት እና ነብዩ ኢብራሂምም የአሏህን ትእዛዝ ተቀብለው ሚስታቸውንና ልጃቸውን በምድረ በዳዋ ምድር ያኖሩባት ስፍራ ናት ቅድሷ ከተማ መካ።
በሙሳ፣ በኢሳ እና በሌሎች ነብያቶችም የተጎበኘች ቅዱስ ቦታ እንደኾነች የአማራ ክልል እስልምና ጉዳይ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሼህ ሙሐመድ አንዋር ከዚህ በፊት ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡
ተመራማሪው ፕሮፌሰር አደም ካሚልም እንዳሉት ደግሞ መካ የተቀደሰ የአሏህ ቤት ያለባት ትልቋ ከተማ ናት፡፡ አሏህ ለመጀመሪያ ጊዜ የአምልኮ ቦታ የአሠራባት እና ነብዩ ኢብራሂም ካዕባን ገንብተው ሲጨርሱ ሰዎች በቻሉት ሁሉ ወደዚህ ሥፍራ እንዲመጡ ጥሪ እንዲያደርጉ እና ቤቱ እንዲጎበኝ ያዘዘበት ቦታ ናት።
ሰዎች ተገናኝተው የሚማሩበት እና የሚወያዩበት እንዲኾን ፈጣሪ የባረካት ከተማ እንደኾነችም ነው የገለጹት፡፡ መካ ላይ የሚደረግ አንድ ሶላት በ100 ሺህ እንደሚታሰብ ተመራማሪው ገልጸዋል።
በዚህ ቅዱስ ስፍራ ምንም አይነት ሐጢአት መሥራት የተከለከለ ነው፡፡ ምን አልባትም በዚህ ቦታ ኾኖ ሐጢያት የሠራ ሰው ከሌላው ጊዜ በተለየ ቅጣቱ በእጥፍ ይጨምራል፡፡
በመካ ተገኝቶ ስግደት ማድረግ ከሌሎች ስፍራዎች ከመስገድ በ100 ሺህ እጥፍ ስለሚበልጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሙስሊሞች ከአራቱም የዓለም ማእዘናት ወደ ቅዱሷ ከተማ ይጎርፋሉ። በየዓመቱም ሙስሊሞች ሀጅ እና ዑምራ ለማድረግ ወደ መካ ያቀናሉ።
መካ ረጃጅም ህንጻዎች እና ትላልቅ መስጅድ ያሉባት ከተማም ናት፡፡ በእጅ የተሠሩ ጡቦችና ሌሎች ሃይማኖታዊ ሥፍራዎች መገኛ በመኾኗ በዓመት ከ15 ሚሊዮን በላይ የሚደርሱ ሙስሊሞች እንደሚጎበኟትም መረጃዎች ያሳያሉ።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!