
ባሕርዳር፡ መስከረም 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሚታመን በጠፋ ዘመን ታመነች፣ ፍትሕ በታጣ ዘመን ፍትሕን ይዛ ተገኘች፣ ፍትሐዊ ንጉሥ አነገሠች፣ በፍትሕ ፈረደች፣ በፍትሕ ኖረች፣ በፍትሕም ተረማመደች፡፡ የተገፉትን ትደግፋለች፣ ያዘኑትን ታጽናናለች፣ የተራቡትን ታጎርሳለች፣ የተጠሙትን ታጠጣለች፣ መጠለያ ያጡትን ታስጠልላለች፣ የታረዙትን ታለብሳለች፣ የደከሙትን ታሳርፋለች፡፡
ፍትሕ ያጡ ፍትሕ አገኙባት፣ በሰላምና በፍቅር አረፉባት፣ የልባቸውን መሻት ፈጸሙባት፣ ክፉውን ዘመንም አሳለፉባት፡፡ ደጋጎች ይኖሩባታል፣ እውነት ጠባቂዎች ይወለዱባታል፣ ነጻነት አዋቂዎች ይገኙባታል፣ በነጻነት የኖሩ ጀግኖችም ያለማቋረጥ ይፈልቁባታል፡፡ እርሷን ወዳጆች ይመኩባታል፣ ደስም ይሰኙባታል፣ ጠላቶች አንገት ይደፉባታል፣ እጅም እየነሱ ይመለሱባታል፡፡
ወሰኗን የደፈሩ ሁሉ ወድቀዋል፣ ክብሯን የነኩ ሁሉ አልቀዋል፣ ያከበሯት ሁሉ ተከብረዋል፣ በክብር መዝገብ ላይም ሠፍረዋል፣ በማይጠፋ ቀለም ተቀርጸዋል፡፡ እርሷን የአምላክ ስውር ጥበብ ይጠብቃታል፣ ቸርነቱና ምህረቱ ይረብባታል፣ ከፍ ከፍም ያደርጋታል፣ በአምላክ የመወደዷ ግርማ ጠላቶቿን ይጥልላታል፣ ፈጥኖም ያስገዛላታል፡፡ የልጆቿ ጀግንነት፣ ነጻነት አዋቂነት፣ ፍትሕ ወዳድነት፣ አትንኩኝ ባይነት፣ የከበረ ሃይማኖት ሲጠብቃት ይኖራል፣ አስከብሯት ይዘልቃል፡፡
የፈጣሪ መልእክተኛ በአሻጋሪ ተመለከቷት፣ ፈጣሪ በሚያስመለክተው ልባቸው ተመልክተው ወደዷት፣ ከተመረጡትም መረጧት፣ በምድሯ ደኃ የማይበድሉ፣ ፍርድ የማያጓድሉ፣ ፍትሕን ያመዛዘኑ ንጉሥ ነበሩና ፍትሕ አዋቂ ንጉሥ የነገሠባት፣ ፍትሕም ያለባት ምድር አሏት፡፡ ለቃል ኪዳን የታመነች፣ እውነትን የጠበቀች፣ ለእውነት እና በእውነት የቆመች መኾኗንም አዩዋት፡፡ እርሳቸው ባሉበት ምድር ፍትሕ እስኪመጣ ድረስ ፍትሕ የተጠሙትን ላኩባት፣ ክፉ ዘመን እስኪያልፍ ድረስም ወዳጆቻቸው ይጠለሉባት ዘንድ መረጧት፡፡ ኢትዮጵያ ከተመረጡት የተመረጠች፣ ከተከበሩት የተከበረች፣ ከታመኑትም የታመነች ናትና፡፡
ኢትዮጵያ በማዕበል ወቅት ሰው የሚተርፍባት መርከብ ነበረች እና የጨነቃቸው ሁሉ ወደ መርከቧ ይገባሉ፣ ማዕበሉንም በመርከቧ ውስጥ ኾነው ያሳልፋሉ፡፡ ማዕበሉ ባለፈም ጊዜ ከመርከቧ እየወጡ ልባቸው ወደ ወደደው ይጓዛሉ፡፡
ነብዩ መሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) በመካ በፈጣሪያቸው መሪነት በተነሱ ዘመን ጠላቶቻቸው በዙባቸው፣ እሳቸውን ያሉ ደግሞ ተከተሏቸው፡፡ በወቅቱ ኀያላን የነበሩት እሳቸውን እና ተከታዮቻቸውን አሳደዷቸው፡፡ በዚያም ጊዜ የእርሳቸው እውነት ገብቷቸው የተከተሏቸውን፣ የሚመጣውን መከራ ሁሉ ለመቋቋም የፈቀዱትን ጊዜ እስኪያልፍ ድረስ ከጠላቶቻቸው ዓይን ያርቋቸው ዘንድ ወደዱ፡፡
የእርሳቸው መልእክተኞች ክፉውን ጊዜ ያሳልፉባት ዘንድ የመረጧት ምድር ደግሞ የሐበሻን ምድር ኢትዮጵያን ነው፡፡ በአቅራቢያቸው ሌሎች ሀገራት ነበሩ፣ ዳሩ እንደ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ግን የወደዷቸው እና የመረጧቸው አልነበሩም፡፡ በክፉ ቀን የምትታመን እና የምትመረጥ እርሷ ናትና፡፡ ወደ መረጧት ሀገር ወደ ኢትዮጵያም ላኳቸው፡፡
የታሪክና የባሕል ተመራማሪው አዩብ አብዱላሂ ስለ ነብዩ መሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) መልእክተኞች ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ሲገልጹ“ እሳቸው አላህ የመረጣቸው ነብይ ናቸው፣ የሚናገሩትና የሚያዩት አላህ ያስመለከታቸውን ነው፣ የሚያወሩት ነገር ሁሉ በስሜታቸው ሳይኾን አላህ አድርጉ ያላቸውን፣ አላህ በል ያላቸውን ነው፡፡ ስለ ኢትዮጵያም አላህ አሳውቋቸዋል፡፡ በወቅቱ ፍትሕ አዋቂና ፍትሕን የሚያደርግ ንጉሥ የነበረው በኢትዮጵያ ነበር” ይላሉ፡፡
ነብዩ መሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) በፈጣሪ ከተገለጠላቸው ውጭ ሌላ ነገር አይናገሩም፣ የሐበሾች ምድርም በእርሳቸው ዘንድ የተመረጠች፣ አላህም የወደዳት ምድር ናት ይሏታል ያን የቀደመ ዘመን ሲያስታውሱ፡፡ ነብዩ መሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) መልእክተኞቻቸውን ልከው በፍትሕና በፍቅር ለተቀበሏቸው የሐበሻው ንጉሥ ነጋሲ (ነጃሺ) ዱዓ ያደርጉላቸው እንደነበርም የታሪክ ተመራማሪው ይናገራሉ፡፡ “ ነብዩ መሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) ታላቅ ነገርን ተናግረዋል፣ የሐበሻን ምድር አትንኳት ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያን የነኳት ሁሉ በታሪክ እንደምናውቀው ተሸንፈዋል፣ ይህ ቃል የተነገረው ዝም ብሎ አልነበረም” ነው የሚሉት የነብዩ መሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) የአደራ ቃል እና የኢትዮጵያን መመረጥ ሲገልጹ፡፡
ኢትዮጵያና እስልምና ቁርኝታቸው የጀመረው በነብዩ መሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) የእውነት ቃልና በነብዩ መሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) መልእክተኞች ነውም ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያ ዝም ብላ የተመረጠች ሀገር ላለመኾኗ ማረጋገጫው ፍትሕ አዋቂ የተባሉት የሐበሻው ንጉሥ የነብዩ መሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) መልእክተኞችን በፍቅርና በሰላም ተቀበሏቸው፤ የልባቸውን መሻት ይፈጽሙ ዘንድም ፈቀዱላቸው፡፡ ስለ ንጉሥ ነጋሲ ፍትሕ አዋቂነት ሲናገሩ“ መልእከተኞቹ ወደ ሐበሻ ምድር በመጡ ጊዜ ጠላቶች ተከትለዋቸው መጡ፡፡ ለንጉሡም ሃይማኖትዎን የሚሳደቡና የሚያንቋሽሹ ኾነው ሳለ ስለ ምን ተቀበሏቸው? እነዚህን ሰዎች በሀገርዎ አያስቀምጡ ለእኛ ይስጡን እና ወደ ሀገራቸው እንወሰዳቸው አሏቸው፡፡ ንጉሡ ፍርድ ከመፍረዳቸው አስቀድሞ መልእክተኞቹን ሃይማኖታችሁ ምን ይላል ብለው ጠየቋቸው፡፡ እነርሱም ሃይማኖታቸውን ነገሯቸው፡፡ በዚያም ጊዜ ንጉሡ ልባቸው ተነካ፡፡ መልእክተኞቹንም እናንተ ሀቀኞች ናችሁ እና በሀገሬ ተቀመጡ አሏቸው፡፡ ለንጉሡ የእጅ መንሻ ይዘው የነብዩ መሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) መልእከተኞች ከንጉሡ ነጥለው ለመውሰድ የመጡትን ደግሞ የእጅ መንሻችሁን ይዛችሁ ወደ መጣችሁበት ሂዱ አሏቸው፡፡ እሳቸው ምን ያክል ፍትሕ አዋቂና ፍትሕ ወዳድ መኾናቸውን አሳዩ” ነው ያሉን፡፡
ንጉሥ ነጋሲ ታምነው የተሰጧቸውን የአደራ እንግዶች በታማኝነት አኖሯቸው፡፡ ዘመን አልፎ እስኪመለሱ ድረስ ያለማንም ከልካይ ይኖሩ ዘንድ ፈቀደላቸው፡፡ ነብዩ መሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) መልእክተኞቻቸውን ሲልኩ ፍትሕ አዋቂ ንጉሥ ያለባት ምድር እንዳሉ ሁሉ መልእከተኞችም ፍትሕን ከንጉሡ አገኙ ይላሉ ጋሽ አዩብ፡፡ የኢትዮጵያውያን ፍትሕ አዋቂነት እና የተቸገረን ማስጠለል እስከ አሁን ድረስ አልጠፋም ነው ያሉኝ፡፡
ኢትዮጵያ በሀገራቸው ውስጥ መኖር ያልቻሉ ደገኛ ሰዎችን የተቀበለች እና በሰላም ያኖረች ታላቅ ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ በቀላሉ መልእክተኞችን የተቀበለች ተብላ የምትገለጽ አይደለችም፡፡ ነብዩ መሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) ፈጣሪ አስመልክቷቸው የመረጧት ታላቅ ናት እንጂ፡፡ ኢትዮጵያ ታላላቅ ሃይማኖቶች የተሰበኩባት ሀገር መኾኗንም ነግረውናል፡፡ ኢትዮጵያ ከእስልምና ሃይማኖትና ከሃይማኖቱ መሪዎች ጥብቅና ምስጢራዊ ቁርኝት ያላት ሀገር ስለመኾኗም ጋሽ አዩብ ይገልጻሉ፡፡
የታሪክና የባሕል ተመራማሪው ስለ ኢትዮጵያ መመረጥ ሲናገሩ “ ኢትዮጵያን ፈጣሪ የመረጠበት አንድ ጉዳይ እንዳለ ግልጽ ነው፤ በየትኛውም ሃይማኖት አንድ ፈጣሪ እንዳለ ይታመናል፡፡ ሁሉም ፈጣሪ የመረጣትን ሀገር ማክበር አለበት” ነው ያሉት፡፡ ሃይማኖተኛ ሁሉ ሰው መግደል ስህተት እንደኾነ ያውቃል፣ የሰውን መብትና ጥቅምም መንካት ወንጀል እንደኾነ ያውቃል፣ ይህን የሚያውቅ ሁሉ ኢትዮጵያውያንን ማክበርና መውደድ ያስፈልገዋል ብለውናል፡፡ ኢትዮጵያ የሁላችንም ሀገር እንደኾነች ማሰብ እና የጋራ የኾነችውን ሀገር በጋራ መጠበቅ ይገባልም ነው ያሉት፡፡
“ኢትዮጵያ የሁሉም ሃይማኖተኛ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ሃይማኖት የሌለውም ሀገር ናት፤ ይሄን መረዳት ግድ ይለናል፡፡ ኢትዮጵያ ጥንታዊት ሀገር ናት፤ ለዘመናት የቆዬ መንግሥታዊ ሥርዓት የነበራት ታላቅ ሀገር ናት፤ እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ የሚለውን አባዜ ትተን፣ሀገር የጋራ ሃይማኖት ደግሞ የግል እንደኾነ ተገንዝበን፣ በጋራ ሀገራችን በጋራ እንኑር፣ በጋራም ለሀገራችን መቆም አለብን” የሚል መንፈስ መጎልበት አለበት ነው ያሉት ጋሽ አዩብ፡፡
ኢትዮጵያን ፍትሐዊት የኾነች ሀገር ኾና እንድትኖር፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በፈለገው የኢትዮጵያ ክፍል እንዲኖር ማድረግ ከኢትዮጵያውያን እንደሚጠበቅም አመላክተዋል፡፡ የውጭ ሀገር ዜጋ ኑ ሀገር ጎብኙልን እያልን ለምነን እያመጣን፣ የራሳችን ዜጋ በሀገሩ አይኖርም ማለት ከነውር በላይ ነውም ይላሉ፡፡ ወደ ቀልባችን፣ ወደ እምነታችን፣ ወደ ቀደመ ታሪካችን መመለስ አለብን፣ ሰላም የምንጫወትበት ነገር ሳይኾን የምንከባከበው ጉዳይ መኾን አለበት ብለዋል፡፡
የተመረጠችውን ሀገር ጠብቋት፣ የተከበረችውን ሀገር አክብሯት፣ ፍትሕ ያለባት የተባለችውን ሀገር ፍትሕ እንደ ወራጅ ውኃ ይፈስስባት ዘንድ አድርጓት፡፡ ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር፣ ድንቅ ምድር፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!