“የነብዩን መልእክተኞች በሰላም ለማሳረፍ ሀገር ኾና የተመረጠችው ኢትዮጵያ፤ ሰው ኾነው የተገኙት ደግሞ ሐበሾች ናቸው” ፕሮፌሰር አደም ካሚል

27

ባሕር ዳር: መስከረም 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ)ዛሬ 1498ኛው የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የልደት በዓል (መውሊድ) ነው። መውሊድ የመከበሩ ዓላማ አስተማሪ ፣ አርዓያ ፣ ፍቅርና ሰላምን ሰባኪ የኾኑትን የነብዩ ሙሐመድን ሥራ ለማስታወስ ነው።

ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ከኢትዮጵያ ጋር የተለየ ግንኙነት ነበራቸው። ኢትዮጵያ ከዓረቡ ዓለም ጋር ያላትን ታሪክ በስፋት ያጠኑት ፕሮፌሰር አደም ካሚል ኢትዮጵያ ነብዩ የመረጧት እና አብዝተውም የሚወዷት ሀገር ስለመኾኗ ማስረጃዎችን ይጠቅሳሉ። ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ኢትዮጵያን “የሐበሻ ምድር” ብለው ነው የሚጠሯት። ችግር ያጋጠማቸው ተከታዮቻቸው መሸሻ እና መደበቂያ ሲያጡ ታላቁን ነብይ “ወዴት እንሂድ” ብለው ጠይቀዋል። የነብዩ ምርጫ አንድ እና ያው ኢትዮጵያ ነበረች። “ፍትሕና ሃቅ ወዳለበት ወደ ሐበሻ ምድር ሂዱ” ነው ያሏቸው። ኢትዮጵያዊያንም በሰላም ተቀብለው አሳርፈዋቸዋል።

ኢትዮጵያውያንም ስደተኞችን በሥርዓቱ ተቀብለው በማስተናገድ ትልቅ ውለታ ውለዋል። ፕሮፌሰር አደም እንደሚሉት ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ከማንም የዓረቡ ዓለም በበለጠ ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነት ነበራቸው። የመጀመሪያውን አዛን (የሶላት ጥሪ) ያሰማው ኢትዮጵያዊው ቢላል ነበር። ከነብዩ ጋር የነበሩ አገልጋዮች፣ የእርሳቸውን ሐዲስ የሚመዘግቡ ሰዎች፣ ታማኝ የጦር መሪዎቻቸው እንዲሁም የሚያማክሯቸው ሊቃውንት ኢትዮጵያዊያን ነበሩ። ይህ ሁሉ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ከኢትዮጵያዊያን ጋር ያላቸውን ልዩ ግንኙነት የሚያሳይ ነው ብለዋል ፕሮፌሰሩ።

የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) እና የኢትዮጵያን ቁርኝት ያጠበቀው ሌላው ጉዳይ “ከእናቴ ቀጥሎ እናቴ” ብለው የሚጠሯት ሐበሻዊቷ አሳዳጊያቸው እሙ አይመን የተባሉ ሴት ኢትዮጵያዊ መኾናቸው ነው። ነብዩ በኢትዮጵያዊዋ ሞግዚታቸው እቅፍ ማደጋቸው ለኢትዮጵያዊያን ትልቅ ክብር እና ፍቅር እንዲኖራቸው አድርጓል።

ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያንን ውለታ አልረሱም። ሀገሪቱን ከመውደድ እና ከማፍቀርም አልፈው “ሐበሾችን አትንኩ” እያሉ ጥብቅናም ይቆሙ እንነበር ፕሮፌሰር ሐጂ አደም ገልጸዋል።

“በዚያ አስቸጋሪ ጊዜ የነብዩን መልእክተኞች ተቀብላ በሰላም ለማሳረፍ ሀገር ኾና የተመረጠች ኢትዮጵያ ፤ ሰው ኾነው የተገኙት ደግሞ ሐበሾች ናቸው” ሲሉም ይገልጻሉ ፕሮፌሰር አደም ካሚል። በዓለም ላይ ለሚገኝ መላው ሙስሊም ሁሉ ኢትዮጵያ ባለውለታ ሀገር መኾኗንም አንስተዋል። ከውለታም አልፎ “በዓለም ላይ ያለ ሙስሊም ሁሉ ባለዕዳ ነው” ሲሉ ነው የሚናገሩት ፕሮፌሰሩ።

ፕሮፌሰር ሐጂ አደም ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ከኢትዮጵያ ጋር የነበራቸውን ልዩ የግንኙነት ታሪክ በወጉ ማወቅ እና ለሌሎች ሀገራትም ማሳወቅ ያስፈልጋል ብለዋል። ይህም ከፍተኛ የቱሪዝም ጠቀሜታ ይዞ ይመጣል ነው ያሉት።
በዓሉ የሰላምና የአንድነት ይኹን!

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በዓል አደረሣችሁ።
Next article“ከታመኑት የታመነች፣ ከተመረጡት የተመረጠች”