
ባሕር ዳር፡- ጥር 18/2012ዓ.ም (አብመድ) አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ የታገቱ ተማሪዎችን በተለመከተ ግልጽ መረጃ እንዲሰጥ ጠየቁ፡፡
በደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ሲማሩ የነበሩ የታገቱ የአማራ ተወላጅ ተማሪዎች በፍጥነት እንዲለቀቁ፣ ስለድርጊቱም ግልጽ መረጃዎች እንዲሰጡ ጥያቄዎች እየቀረቡ ነው፡፡ የኪነ ጥበብ ሰዎች እና ሌሎች ታዋቂ ግለሰቦችም በተማሪዎቹ ላይ የተፈጸመውን እገታ እያወገዙ ነው፡፡ ተማሪዎቹ በአስቸኳይ እንዲለቀቁና ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉም ነው እየጠየቁ የሚገኙት፡፡
የታገቱ ተማሪዎችን በተመለከተ የመንግስት ዝምታ ተገቢነት እንደሌለውም በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች እያሳወቁ ይገኛሉ፡፡ በተለይም አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው በተንቀሳቃሽ ምስል ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶክተር) ባስተላለፉት መልዕክት ስለጉዳዩ ግልጽ ማብራሪያ እንዲቀርብ ጠይቀዋል፡፡
“ዛሬ በድሃ አቅማቸው አስተማረው፣ ሀገራችን ነው ብለው ድሃ ልጆቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ መሬት፣ ወደ ኢትዮጵያ ልከው፣ አድገው ተምረው እንዲረዷቸው የላኳቸው ወጣቶች ታፍነው ከ50 ቀን በላይ ድምጻቸው አልሰማ ሲል ከመንግስት የሰማነው ተፈትተው በቅርቡ ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ ነው፡፡ ይሄው ያንን ከተባልንም ቀናት ተቆጠሩ፤ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ እንዴት አስቻለዎት፣ በሌላ ጉዳይ ላይ ብዙ ጊዜ እየወጡ የተናገሩትን ያህል ይሄን የመሰለ ከባድ የእናቶች ሁለተኛ የምጥ ሰዓት ላይ እንዴት አስችሎዎት ዝም አሉ? ዝምታው ለምን ይሆን?” ሲሉ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡
እየተደረገ ያለው ምን እንደሆነ፣ ማን ምን እንዳደረገ ዕውነቱ ዛሬ ሊነገር እንደሚገባም ነው አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ የጠየቁት፡፡ መንግሥት ይህን የማድረግ አቅም አለው ብለው እንደሚምኑም ተናግረዋል፡፡ እናም ‹‹በፍጹም ሳይውሉ ሳያድሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የእነዚህን የታፈኑ ኢትዮጵውያን መጨረሻ ያሳውቁን ስል በአክብሮት እጠይቃለሁ›› ብለዋል ታማኝ በየነ፡፡