
ባሕርዳር፡ መስከረም 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሒጅራ አቆጣጠር ከመጀመሩ ከ53 ዓመታት በፊት የተወለዱት እና በኢትዮጵያዊቷ በረካ (እሙ አይመን) እጅ ያደጉት ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ.) ከተወለዱ እና ነብይ ከሆኑ ጀምሮ ሰዎችን በመልካም ሰብእና እና ምግባር አንፀዋል፡፡ በዚህም የተነሳ የእሳቸው ተከታዮች ለፍጥረታት ሁሉ ጉዳትና ጥቃት እንዳይደርሱባቸው የሚከላከሉ ነበሩ፡፡
በተወለዱ ማግስት በድርቅ ተትመቶ የነበረው
ሀገር በረከት የሞላበት ሆኖ ነበር፡፡ ወላጆቻቸው እና የቅርብ ቤተሰብ አሳዳጊዎቻቸው በልጅነታቸው ስለሞቱባቸው ብዙ ችግርና መከራ አይተዋል፡፡
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በዘመናቸው ሕዝቡ እና ተከታዮቻቸው በመልካም ሥነ ምግባር የታነፁ እንዲሆኑ አርዓያ ሆነዋል፡፡ የእስልምና ሃይማኖት መመሪያ የሆነው ቅዱስ ቁርኣን በመላዒካ የወረደላቸው የመጨረሻው ነብይ ናቸው፡፡
ለሐበሾች ታላቅ ፍቅርና አክብሮት ያላቸው ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ከልጅነት እድሜያቸው ጀምሮ ቅን፣ አስተዋይ፣ ለፍጥረታት ሁሉ የሚያዝኑና ክብር የሚሰጡ፣ አንዱን ከአንዱ የማያበላልጡ፣ ዘረኝነትን በጽኑ የሚቃወሙ እና የመልካም ባህሪያት ባለቤት እንደነበሩ ይነገርላቸዋል፡፡
“ዘረኝነት መጥፎ ሽታ ያለው ነገር ነውና ራቁት፤ የሰው ልጅ እንደማበጠሪያ ጥርስ እኩል ነው” በማለትም አስተምረዋል፡፡ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) አምልኮን፣ ሕክምናን፣ የሒሳብ ስሌትን እና ሌሎችንም ነገሮች ትምህርት ቤት ገብተው ሳይማሩና የተፃፉ መጽሐፍት ሳያገላብጡ እንዲሁም ከአዋቂዎች ወይም ከምሁራን ጋር ሳይቀመጡ ያወቁ ናቸው፡፡
በሰዎች መካከል የሚነሱ ግጭቶችንና ውዝግቦችን ለመፍታት ነብይ ከመሆናቸውም በፊት ጀምሮ የተለየ ችሎታ ነበራቸው ይባላል፡፡ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ከመዲና ወደ መካ ሲገቡ ሃሳብ ከኃይል ወይም ከጉልበት በላይ ኃይል እንዳለው ስላወቁ ለስደት የዳረጓቸውን ጠላቶቻቸውን ከመበቀል ይልቅ በይቅርታ ተቀብለው አሻግረዋቸዋል፡፡
ነብዩ በአስተዳደራቸውም ወቅት ልዩነቶች ሁሉ ውሳኔ የሚያገኙት በምክክር ነበር፡፡ የእርሳቸው መንግሥት ሁሉንም ሰው ፍትሐዊ በሆነ መልኩ የሚመለከት እንደነበር ይነገራል። ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች እንኳ እኩል መብት የነበራቸው እና የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ነበር፡፡ የሕዝባቸውን ሃይማኖታዊም ሆነ ምጣኔ ሃብታዊ ፍላጎት በሚገባ ጠብቀዋል፡፡
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ንግግራቸው መልካም፣ ምክራቸው አስተማሪ፣ አስተምህሯቸው ማስረጃ የሚኾን እና ዲፕሎማሲያዊ ችሎታም ነበራቸው፡፡ ከሌሎች ጋር ያደረጓቸውን ውሎችና ስምምነቶች ያፈረሱበት አጋጣሚም አልነበረም፤ ለቃላቸው ተገዥ ነበሩ፡፡
ጠንካራ፣ ከጠላቶቻቸው የተሻለ የማሸነፍ ዕድል እና አቅም ላይ ኾነው እንኳን አንድም ጊዜ ቀድመው ጦርነት ቀስቅሰው አያውቁም፡፡ ከጦርነት ይልቅ ሰላም ወዳድ እና ተስማምቶ መኖርን የሚመርጡ የሰላም ሰው ነበሩ፡፡
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በጌታቸው ላይ ፍፁም የሚመኩ፣ ያላቸውን ሁሉ ለተቸገረ የሚለግሱ፣ ስስትን ድል ያደረጉ፣ ሕፃናትን ጊዜ ሰጥተው የሚያጫውቱ፣ የእንስሳቶችን ስሞታ እንኳ የሚያዳምጡ፣ የተምር ዛፍ ሳይቀር በናፍቆት ያነባላቸው ተወዳጅ ነብይ ናቸው፡፡
ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንደ መሪ፣ እንደ አባት፣ እንደ ባል፣ እንደ መንፈሳዊ መሪ የተሟላ ስብዕና የተሰጣቸው ለሰው ልጆች ሁሉ አርዓያ መሆን የቻሉ የአላህ ባሪያ ነበሩ፡፡
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በመጨረሻ ካደረጓቸው ንግግሮች “ሰዎች ሆይ! ማንም ሰው እንዳያጠቃችሁ በማንም ሰው ላይ ጥቃት አታድርሱ፣ ሁላችሁም እኩል ናችሁ። ማንም ሰው ከሌላው የሚበልጥበት መንገድ የለም፣ አላህን በመፍራት፣ በጥሩ ምግባሩ እና ተግባሩ ቢሆን እንጂ!፣ በሴቶቻችሁ ላይ የተወሰኑ መብት ያላችሁ መሆኑ እርግጥ ነው። ነገር ግን እነሱም በናንተ ላይ መብት አላቸው። በናንተ ቁጥጥር ስር እስካሉ ድረስ የመመገብ፣ የማልበስና በርህራሄ የመያዝ ግዴታ ይኖርባችኋል። ሴቶቻችሁ የኑሮ ጓደኞቻችሁና የቅርብ ደጋፊዎቻችሁ በመሆናቸው በርህራሄ ተንከባከቧቸው። አስታውሱ! አንድ ቀን በአላህ ፊት ቀርባችሁ ለሠራችሁት ሥራ ትጠየቃላችሁ” በማለት ከፈጣሪ የተሰጣቸውን ተልዕኮ እንዳጠናቀቁ ለሕዝቡ ያዘጋጁትን የፈጣሪን ቃል የከተቡበትን ቅዱስ ቁርኣን አበርክተው በ63 ዓመታቸው ወደማይቀረው ዓለም አልፈዋል፡፡
ምንጭ፡- Ethiomuslims.net፣ አፍሪካ ቲቪ፣ ዛውያ ቲቪ
በእመቤት አህመድ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!