“ዘረኝነትን ራቋት፣ አትቅረቧት”

27

ባሕር ዳር: መስከረም 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሚዛን ታስታለች እና ዘረኝነትን ራቋት፣ ሰበዓዊነትን ታስረሳለች እና ዘረኝነትን አትቅረቧት፣ ፍቅርን ታጠፋለች እና ዘረኝነትን ሽሿት፣ አንድነትን ታናጋለችና ዘረኝነትን አትቅረቧት፣ መዋደድን ታረክሳለች፣ ጉርብትናን ታጠፋለች፣ የከበረውን ነገር ታዋርዳለች እና ዘረኝነትን ራቋት፡፡ ቀዬን ከቀዬ ታቃቅራለች፣ ቂምና በቀልን ታበቅላለች እና ዘረኝነትን አትቅረቧት፡፡

ጦር እያማዘዘች፣ ሳንጃ እያሳለች፣ ክፋት እያሳሰበች፣ መለያየትን እያገነነች፣ አንድነትን እያኮሰመነች፣ አብሮነትን እያጠለሸች ደም ታፋስሳለች፣ አጥንት ታከሳክሳለች፣ ሕይወት ታስገብራለች እና ዘረኝነትን ራቋት፡፡ የአንድን ሀገር ሕዝቦች ታባላለች፣ መልካሙን ዘመን ታጠፋለች፣ ደጉን ዘመን ትረሳለች፣ ታስረሳለች፣ አብሮ መብላትን፣ አብሮ መጠጣትን፣ ለአንድ ዓላማ ለአንድ ክብር አብሮ መሞትን ታስጥላለች እና ዘረኝነትን አትቅረቧት፡፡

ለፍቅር ተፈላለጉ እንጂ ለጥል አትፈላለጉ፣ ለፍቅር ጓጉ እንጂ ለጥል አትጓጉ፣ ፍቅርን ገንዘባችሁ አድርጓት፣ ሰላምን እንደ ዓይን ብሌን ጠብቋት፣ ብሌን በጠፋች ጊዜ ብርሃን ይጠፋል፣ ጨለማም ይኾናል፡፡ ሰላምም በጠፋች ጊዜ ምድር ትናወጻለች፣ በጦር ፍላጻ ትወጋለች፣ በመከራ ቆፈን ትሸበባለች፣ በጦር አውታር ትወጋለች፣ አብዝቶ የሚመረውን የመከራ ጽዋ ትጎነጫለች፡፡ ዘረኝነት በነገሠች ጊዜ ምድር ሰላምን ትነጠቃለች፣ በደም ጎርፍም ትጥለቀለቃለች፡፡ በሁካታና በብጥብጥ ትመላለች፡፡

ዘረኝነት በነገሠች ዘመን ሕጻናት ያለቅሳሉ ፤ እናትና አባቶቻቸውን ይነጠቃሉ ፤ እናቶች ልጆቻቸውን ያጣሉ፣ ማሕጸናቸው ፍሬን እንዳልሰጠች፣ ጡታቸውም ወተትን እንዳልመገበች፣ ክንዳቸውም ልጅን እንዳላቀፈች፣ ጀርባቸውም እንዳላዘለች፣ ልባቸውም በእናት ፍቅር እንዳልደመቀች ይኾናሉ፣ ወዮልን ወዮታ አለብን እያሉ አብዝተው ያዝናሉ፤ ፊታቸውን ይነጫሉ፣ የሚዋቡበትን ልብሳቸውን ያወልቃሉ፣ ደረታቸውን ይደቃሉ፣ ጥርሳቸውን በሀዘን ያፏጫሉ፡፡ አዛውንቶች ያለ ቀባሪ ይቀራሉ፣ በለቅሶና በዋይታ በባዶ ቤት ይኾናሉ፣ ወጣቶች ያለ ፍሬ ያልፋሉ፣ ተስፋቸውን ይነጠቃሉ፡፡

መተማመንን ታጠፋለች፣ የሰፋውን ታጠባለች፣ የጠነከረውን ታደክማለች፣ የረዘመን ታሳጥራለችና ዘረኝነትን ራቋት፡፡ አንድነትን አጠንክሩ፣ ስለ ሰላም ታትሩ፣ ስለ ፍቅር ተባበሩ፣ ስለ አብሮ መኖር ምከሩ እንጂ ዘረኝነትን ራቋት፣ አትቅረቧት፣ አብዝታችሁም ጥሏት፤ ከልባችሁ መዝገብ ላይ ደምስሷት፡፡ በቀያችሁና በአድባራችሁ እንዳትኖር አድርጓት፡፡

በሐረር ታላቁ ጃሚ መስጂድ ኢማም ዑዝታዝ አብዱልሀኪም መሐመድ የእስልምና ሃይማኖት ዘረኝነት እጅግ አስቀያሚ እንደኾነ ያስተምራል ይላሉ፡፡ ነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) የተለያዩ ቀለም ያላቸው፣ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ሰዎችን ይቀበሉ ነበር፡፡ ሰውን የሚቀበሉት በሰውነቱ፣ በመልካምነቱ፣ በቀና ልቡናው እና ለፈጣሪ ተገዥነቱ እንጂ በመጣበት ሀገር፣ በሚናገረው ቋንቋ፣ በተፈጥሮ ቀለሙ አልነበረም፡፡ ሰው በሰውነቱ እኩል ነው፣ አንዱን ከሌላኛው የሚለየው መልካም ባሕሪው ፣ ትህትናው ፣ አዛኝነቱ ፣ ፍቅሩና ታዛዥነቱ ነው፡፡

ዑዝታዝ አብዱልሀኪም ስለ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ሲናገሩ “ ነብዩ ሙሐመድ ከአረቦች ስለተገኙ እና አረቦች ነብዩ የተላኩት ከእኛ ነውና እኛ ከሌሎች የተሻልን ነን እንዳይሉ አረብ የኾኑት አረብ ካልኾኑት የሚሻሉበት ሁኔታ የለም፡፡ አላህን በመፍራት፣ ጌታን በመታዘዝ ብቻ ነው ክብርን ማግኘት የሚቻለው፡፡ በቀለም፣ በዘር፣ በሃብት አይደለም ሰው ከሰው የሚለየው፡፡ ክብር የሚገኘው አላህን በመታዘዝ ነው” ብለዋል ይላሉ፡፡

በዘር መለያየትን፣ በዘር እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ መባባልን፣ በዘር መቧደንን እሳቸው አብዝተው ይፀየፋሉ፡፡ ክብር የሚገኘው አላህን በመፍራት ነው፣ የሚበልጠው አላህን በመታዘዝ ነው፤ ዘረኝነት ግን የተጠላች ናት ይላሉ ነው ያሉት፡፡ በነብዩ አስተምህሮ “ ዘረኝነት ጥንብ ነች፣ ትገማለች፣ አትቅረቧት ፣ ራቋት” ተብላለችም ይላሉ ዑዝታዝ አብዱልሀኪም የዘረኝነትን መጥፎነት ከነብዩ ቃል ጋር አጣቅሰው ሲናገሩ፡፡

እሳቸው የዘረኝነትን መጥፎነት፣ የዘረኝነትን ከፋፋይነት እና ለሰዎች ያልተገባች መኾንን አስቀድመው አስምረዋል ፤ ትዕዛዝና ሕግንም አስቀምጠዋል፡፡ እሳቸው ስለ ዘረኝነት መጥፎነት ያስተማሩትን የእሳቸውን አስተምህሮ የሚከተሉት ብቻ ሳይኾኑ ሌሎችም ቢኾኑ ቢወስዱት የተገባች እና መልካም የኾነች አስተምህሮ ናት ይሏታል፡፡

ሁሉንም ማድረግ ያለብን በመልካምነት እንጂ በዘረኝነት አይደለም፣ ለራሳችንና ለሌሎችም መልካሞች ኾነን ክብርን ማግኘት አለብንም ነው የሚሉት፡፡ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ኢትዮጵያ መልካም ሀገር እንደኾነች የተናገሩላት ታላቅ ሀገር ናት፡፡ ለታላቅ ሀገር የሚመጥን መልካምነት ያስፈልጋል ፤ ዘረኝነት ለተወደደች ሀገር የተገባች አይደለችም ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ በነብዩ አንደበት ሰላምና ፍትሕ ያለባት ሀገር መኾኗ ተመስክሮላታል፡፡ ሰላምና ፍትሕ አዋቂ ንጉሥ የነገሠባት ከመባል አልፋ በክፉ ዘመን ታምና አደራ ተቀምጦባታል፣ አደራዋንም በሚገባ ተወጥታለች፣ ከተሰጠችው ሳታጎድል ጠብቃለች፡፡ ይህች ሀገር ፍትሕና ሰላም ይኖርባት ዘንድም መሥራት ይገባል፣ አንደኛው በሌላኛው ላይ በክፋት መነሳት በሃይማኖት የተከለከለች ናትና ይላሉ ዑስታዝ፡፡

ዘረኝነትን ፈጽሞ መተውና በፍቅር መኖር በፈጣሪ ዘንድ የተወደደች ናት ብለዋል፡፡ እስልምና በራሱ ሰላም የኾነ፣ ሰላምን የሚሰብክ ሃይማኖት ነው ያሉት ዑስታዝ አብዱልሀኪም ባለንበትም ቦታ ፣ በሄድንበትም ሥፍራ ሁሉ ሰላምን መስበክ አለብን ነው የሚሉት፡፡

ተምሮ ለማወቅም፣ ሠርቶ ለመክበርም፣ ወጥቶ ለመግባትም፣ ልጅ ወልዶ ለማሳደግም፣ አሳድጎም ለወግ ለማዕረግ ማብቃትም ሰላም ታስፈልጋለች፡፡ ሰላም ከሌለች ደስታም የለችም፣ ሰላም ከሌለች ሕይዎትም የለችም፣ ሁሉም ነገር የለም፡፡ ሰላም የሁሉም ነገር መከወኛ መንገድ ናት፡፡ በሰላም መንገድ የሚጓዙ ይደርሳሉ፣ ቢዘሩት ያፍሳሉ፣ ቢወልዱት ያድጋል፣ ለቁም ነገር ይበቃል፤ ሰላም ያልኾነ መንገድ ግን ስንዝር አያረማምድም፣ ከአሰቡትም አያደርስም፡፡

ሁከትና ብጥብጥ በኾነ ጊዜ ሕጻናት ይሞታሉ፣ ደካሞች መከራ ይቀበላሉ፣ ሮጠው የማያመልጡት፣ የመከራን በትር የማይቋቋሙት አብዝተው ይጎዳሉ፣ በግፍም ያልቃሉ፡፡

ጦርነት ውድመትን እና ብክነትን ያስከትላል፣ አንድነት እና መስማማት ግን ለሀገርና ለሕዝብ ይጠቅማል ነው ያሉኝ ዑዝያዝ፡፡ መፍትሔ የሚኾነው ችግሮችን በስክነት እና በውይይት መፍታት ነው ይላሉ፡፡ ከሰላም ውጭ ያለው እና የተጠላው አካሄድ ያጠፋፋ ይኾናል እንጂ መፍትሔ አያመጣምም ብለዋል፡፡

በነብዩ ሙሐመድ አስተምህሮ ለጎረቤቱ ጥሩ የኾነ ትክክለኛ አማኝ ነው፡፡ ለራሱ የወደደውን ነገር ለጎረቤቱ ካላደረገ በአላህ አላመነም ማለት ነው ይላሉ፡፡ ለራስ የሚፈልጉትን መልካም ነገር ለሌሎችም እንዲኾንላቸው መሻት፣ እንዲኾንላቸው ማድረግ የተገባች እና የተወደደች ናት፡፡

በኢትዮጵያ የሚታየውን ያልተገባ እና ያልነበረ የዘረኝነት አስተሳሰብ ለማጥፋት የነብዩ ሙሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) አስተምህሮ መተግበር በእጅጉ ወሳኝ ነው፡፡ ሰላምና ፍቅር እንዲቀርብ፣ ጥልና ጥላቻ እንዲርቅ፣ አንድነት እና ወንድማማችነት እንዲጎለብት፣ አብሮ መብላት እና መጠጣት ከዳር ዳር እንዲሠፋ ዘረኝነትን መራቅና መሸሽ ግድ ይላል፡፡ እሳቸው እንዳሉት ዘረኝነት የከፋች እና የተጠላች ናትና ጥሏት፣ አትቅረቧት፣ አብዝታችሁ ራቋት፣ በምትኖሩበት ሁሉ እንዳትኖር አድርጓት፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሁሉም ሰው ከዘረኝነት ወጥቶ ሃይማኖቱ ያዘዘውን በአግባቡ ቢያከናውን ጥላቻ፣ አለመግባባት ፣ መለያየት እና መገፋፋት ቦታ አይኖራቸውም ነበር” ሼህ ሙሐመድ ኢብራሒም
Next article“ነብዩ የሰላም አባት”