“ሁሉም ሰው ከዘረኝነት ወጥቶ ሃይማኖቱ ያዘዘውን በአግባቡ ቢያከናውን ጥላቻ፣ አለመግባባት ፣ መለያየት እና መገፋፋት ቦታ አይኖራቸውም ነበር” ሼህ ሙሐመድ ኢብራሒም

31

ባሕር ዳር: መስከረም 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) 1498ኛው የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የልደት በዓል በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በድምቀት ነገ ይከበራል። የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የዳዕዋ እና ትምህርት ክፍል ተጠሪ ሼህ ሙሐመድ ኢብራሒም “በመውሊድ ሰላም ተሰብኳል” ብለዋል። ነብዩ በፈጣሪያቸው አሏህ ተመርጠው ወደ ተልዕኮ ሲገቡ የመጀመሪያው ሥራቸው አካባቢውን ሰላም ማድረግ ነበር።

ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በተወለዱበት ዘመን እና አካባቢ የሚገኙ ጎሳዎች ፀብ ላይ ነበሩ። ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ተወልደው ለተልዕኮ በተመረጡበት ወቅት የመጀመሪያ ሥራቸው ፀብ ላይ የነበሩ ጎሳዎችን ማስማማት እና ሰላማቸው ተጠብቆ በፍቅር እና በአንድነት እንዲኖሩ ማድረግ ተቀዳሚ ሥራቸው እንደነበር ገልጸዋል።

ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ከፈጣሪያቸው ዘንድ ተልእኮ ተሰጥቷቸው ወደ አስተምህሮቱ የገቡት በአርባ ዓመታቸው እንደነበርም ሼህ ሙሐመድ ገልጸዋል። በአምላካቸው ተመርጠው ነብይ ከመኾናቸው በፊት በንግድ እና በልዩ ልዩ ሥራዎች ተሠማርተው ቆይተዋል። ታማኝ በመኾናቸው “ሙሐመድ ታማኙ” የሚል ቅፅል ስም ነበራቸው።

ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ሰላምን፣ ፍቅርንና አንድነትን ለዓለም አስተምረዋል። መጋጨትን፣ መለያየትን፣ መጣላትን፣ መዳማትን እና አለመስማማትን በይፋ ያወገዙ ነብይ እንደነበሩም ሼህ ሙሐመድ ተናግረዋል።

“ሰላምን እንስበክ ካልን የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) አስተምህሮ በቂ ነው” ሲሉም ሼህ ሙሐመድ ይናገራሉ። በተለይ መዲና ላይ የነበሩ የተለያየ ሃይማኖት ይከተሉ የነበሩ ጎሳዎች ይጋጩበት የነበረውን ነገር አስቀርተው ሁሉም የሚፈልውን ሃይማኖት እንዲከተል ቃል እያስገቡ ማስማማታቸውን ተናግረዋል።

የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የሰላም አስተምህሮ ለኢትዮጵያ ብሎም ለዓለም ትልቅ ትምህርት መኾን አለበት ነው ያሉት። ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ሁሉም የሚፈልገውን እምነት እንዲከተል፣ ወንድም ወንድሙን እንዳይጠላ፣ እንዳይገድል እና እንዳያሳድደው አስተማሩ እንጂ ዓለም ጎራ ፈጥሮ እንዲዋጋ አላስተማሩም ሲሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ከምንኖረው ሕዝቦች ብዙው የራሳችን የምንለው ሃይማኖት አለን የሚሉት ሼህ ሙሐመድ በሁሉም እምነት ውስጥ ደግሞ ፀብ ወይም ክርክር አይፈቀድም፣ ወንድም ወንድሙን መግደል፣ ማሳደድ ሀጢአት ነው ተብሎ ተጽፏል። ታዲያ አሁን ያለው ለፀብ መፈላለግ እና መገዳደል ከየት የመጣ ነው? ወይስ ኹላችንም ከሃይማኖቱ አስተምህሮ ገለል ብለናል ማለት ነው? ምክር አዘል አባታዊ ጥያቄ አቅርበዋል።

የጋራ የኾነውን ሰላማችን መጠበቅ ያስፈልጋል ያሉት ሼህ ሙሐመድ ኢብራሂም ሰላማችንን አሳልፈን ሰጥተን ሰላም እንፈልጋለን ማለት “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” ይኾናል ብለዋል። የጋራ የኾነችውን ሀገራችንን በጋራ ስለሰላሟ መስበክ፣ መወያየት እንጂ የመከፋፈልን አዋጅ መስበክ ተገቢ አይደለም ፤ የራሳችንን ስቃይ ነው የምናበዛው ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን የሰላም ባለቤቶች ነበሩ ፤ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ተከታዮቻቸው ችግር በገጠማቸው ወቅት ሂዱ ሰላም ወዳለባት ፍትሕ ወደነገሰባት ሀገር ብለዋቸው ነበር ያሉት ሼህ ሙሐመድ ዛሬ የእኛ ሰላም ጠፍቶ ከሌሎች ሰላማችንን ለመቀበል መሞከር ሞኝነት ነው ብለዋል። ሁሉም ሰው ከዘረኝነት፣ ከጎጠኝነት ወጥቶ ሃይማኖቱ ያዘዘውን በአግባቡ ቢያከናውን ጥላቻ፣ አለመግባባት ፣ መለያየት እና መገፋፋት ቦታ አይኖራቸውም ነበር ብለዋል።

ሰላም የሁላችንም ምርጫና ፍላጎት እንጂ አንዱ ሰላም ለማድረግ ሲለፋ ሌላኛው የሚያጠፋ ከኾነ ከንግግር ባለፈ የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ትምህርት ተግባራዊ አልተደረገም ማለት ነው ብለዋል። ሼህ ሙሐመድ በማንኛውም ጊዜ እና ቦታ ስለሰላም ማውራት፣ መነጋገር እና መመካከርን እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ሁሉም ሰው የሰላም አምባሳደር ኾኖ ሰላምን መስበክ እንዳለበትም ተናግረዋል።

ከነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ብዙ ስሞች መካከል ውስጥ “ሰላም” አንዱ ነው የሚሉት ሼህ ሙሐመድ ዱዓ (ጸሎት) ሲደረግም አሏህ ሆይ አንተ ሰላም ነህ፣ ሰላም የሚገኘው ካንተ ነው እኛንም፣ ሀገራችንንም ወገናችንንም ሰላም አድርግልን” ብሎ መለመን ከሃይማኖት አባት የሚጠበቅ ነው ብለዋል። ምዕመኑም የሃይማኖት አባቶችን ምክርና ተግሳጽ በመቀበል እና በመተርጎም ለነገ የሀገራችን እጣ ፈንታ ድርሻ ልንወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል። ሰላም የጋራ አጀንዳችን ኾኖ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።

የነገሮች ሁሉ ቁንጮ የኾነው ሰላም ከእጃችን ካመለጠ በቀላሉ መመለስ እንደማይቻል ነው ሼህ ሙሐመድ የተናገሩት። የሃይማኖት አባቶች የሚናገሩትን በአግባቡ ማዳመጥ፣ ያዳመጡትንም በተግባር ማሳየት እና የሰላም ሰባኪ ኾኖ መቀጠል እንደሚገባም ተናግረዋል። ሰላምን ለማምጣት የምንጓዝበት መንገድ ሰላማዊ፣ አንዱ የአንዱን ሰላም የማይጨፈልቅ፣ ከእኔ ይልቅ ወንድሜ ብሶት አለበት ብሎ መጨነቅ ከእያንዳንዱ ሰው የሚጠበቅ ጉዳይ መኾን አለበትም ብለዋል።

በመገዳደል፣ ደም በመፋሰስ፣ በጠብ እና በብጥብጥ ሰላም ከቶውንም መጥቶ አያውቅም ነው ያሉት። ሁሉም ሰው ለእምነቱ፣ ለሀገሩ እንዲሁም ለጎረቤቱ ታማኝ ኾኖ የነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) የልደት በዓልን በሰላም እንዲያከብር ምኞታቸውን ገልጸዋል።

ዘጋቢ:-ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለመላው ሙስሊም ማኅበረሰብ በሙሉ እንኳን ለ1498ኛ የመውሊድ በዓል አደረሣችሁ!
Next article“ዘረኝነትን ራቋት፣ አትቅረቧት”