
ኢትዮጵያውያን መለኮታዊ መሠረት ያላቸው ሃይማኖታዊ አስተምህሮቶችን ቀድሞ በመገንዘብም ሆነ በመቀበል ረገድ ከቀዳሚዎቹ ጥንታውያን ሕዝቦች መካከል ፊተኞቹ ስለመኾናችን በታሪክ ተሰንዷል።
በተለይም ስረ መሠረታቸውን ከነብዩ አብርሃም ፈለግ ላይ ያደረጉና መለኮታዊ ዳና ያላቸው የአይሁድ፣ የክርስትና እና እስልምና ሃይማኖትን ከመቀበልም ባሻገር በሃይማኖታቸው ምክንያት ጉዳት ሲደርስባቸው የነበሩ አማንያን በማስጠጋት፣ ከለላ በመስጠትና አብሮ በማኖር ረገድ ዓለም ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን የተሻለ ሌላ ተምሳሌት አላገኘችም፡፡
በገዛ ወገኖቻቸው ለተጠቁትና የትውልድ ስፍራቸውን ጥለው መሰደድ ግድ ለሆነባቸው ቀደምት ተከታዮቻቸውን “ወደ ሐበሻ ምድር ሂዱ፣ እርሷ እውነተኛ ንጉሥ ያለባት የፍትሕ ምድር ናትና፡፡” ሲሉ ነብዩ ሙሐመድ መመስከራቸው የእልፍ ዘመን አስረጂ ሆኖ ለ14 ምዕተ ዓመታት ዘልቋል፡፡
በመሆኑም የአምላክ እዝነት መገለጫና መልእክተኛው የሆኑትን ታላቅ ነብይ የተወለዱበትን እለት ስናከብር የዘወትር አስተምህሮቶቻቸው የሆኑትን ሰላም ወዳድነትን፣ ፍትሃዊነትን፣ እውነተኛነትን፣ አዛኝነትን እና እኩልነትን በመካከላችን በማኖር ሊሆን ይገባል፡፡
በተለይም የዘንድሮውን የመውሊድ በዓል ስናከብር ከሌሎች ወንድም እህቶቻችን ጋር የመኖር ባህላችንን አጥብቀን በመያዝ፣ የተቸገሩ ወገኖቻችንን በመርዳት፤ የታረዙትን በማልበስ በኢትዮጵያዊነት የመቻቻልና የአብሮነት መንፈስ እንዲሆንና በክልላችን እየመጣ ያለውን ሠላም የበለጠ እንዲጠናከር ክልላችን የሠላም ተምሳሌት እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል። በዓሉ የሠላም የፍቅርና የመተሳሰብ እንዲሆን እንመኛለን!!
በድጋሚ መልካም የመውሊድ በዓል!
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ
መስከረም 15/2016 ዓ.ም