የአለቃ ገብረሃና ሊቅነትና ሌላ ገጽታ በ‹‹አራት ዐይና›› ትውፊታዊ ቴአትር እንዴት ተገለጸ?

952

ባሕር ዳር፡- ጥር 18/2012ዓ.ም (አብመድ) መቼቱን በታላቁ ሊቅ አለቃ ገብረ ሃና የህይዎት ታሪክ ዙሪያ ያደረገው እና ‹‹አራት ዐይና›› የሚል መጠሪያ የተሰጠው ትውፊታዊ ቴአትር በሙሉ ዓለም የባህል ማዕከል ተዘጋጅቶ ትናንት ተመርቋል፡፡

በ1814 ዓ.ም በቀድሞው የጎንደር ጠቅላይ ክፍለ ሃገር ወረታ አካባቢ ልዩ ስሙ ናበጋ ጊዮርጊስ ስጋ ነስተው ነፍስ ዘርተው ይችን ምድር የተቀላቀሉት እና በ1898 ዓ.ም ከዚህ ዓለም የተለዩት አለቃ ገብረ ሃና ደስታ ተገኝ በበርካቶች ዘንድ በሰፊው የሚታወቁት በቀልድ አዋቂነታቸው ነው፡፡ አለቃ ገብረ ሃና በዘመኑ ከነበረው ባህላዊ ስሪት አፈንግጠው በእውቀት እና በጥበብ ነገሮችን መርምረው እና አመስጥረው በድፍረት መተቼታቸው በአቅራቢያቸው የነበሩ የቤተ ክህነት እና የቤተ መንግስት ሰዎች ስማቸው ከቀልድ እንዳይዘል ለማድረግ የሰሩት ስራ ሊቅነታቸውን ለዘመናት ቀልድ እና ቧልት እንዲሸፍነው አድርጎታል፡፡

ከራስ አሊ እስከ አፄ ቴዎድሮስ፣ ከአፄ ዮሃንስ እስከ እምየ ምንሊክ የአራት ነገስታት የፍርድ ምሰሶ፣ የፍትሃ ነገስት ሊቅ፣ የአቡሻከር ጠቢብ፣ የነገስታቱ አማካሪ እና የኋላ ቀር አስተሳሰብ ሞረድ የነበሩት አለቃ ገብረ ሃና ‹‹ከማያስተምሩህ ጋር አትዋል›› የሚለውን የመምህራቸውን አስተምህሮና ምክር አሻሽለው ‹‹የሰው ቀለም አትናቁ›› በሚል በዘመኑ ባልተለመደ መልኩ ለእውቀት ከፍ ያለ ዋጋ የሰጡ ሊቅ እንደነበሩ ትውፊታዊ ቴአትሩ ይዳስሳል፡፡

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አነጋግሬ ጋሻው (ዶክተር) አለቃን ‹‹ከዘመናቸው በፊት የተፈጠሩ እና እውቀት የጠገቡ ሊቅ ነበሩ›› ብለዋቸዋል፡፡ ይህን ቴአትር ለተመልካች ለማድረስ እና መሰል የጥበብ ስራዎችን ለሚሰራው ሙሉ ዓለም የባህል ማዕከል ለማገዝ ዩኒቨርሲታቸው ዝግጁ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ፀሃፊ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ፣ ጌትነት እንየው፣ አበረ አዳሙ፣ የደብረ ታቦር ኢየሱስ ሊቃውንት፣ የተክሌ አቋቋም ተማሪዎች፣ የቴአትር ተማሪዎች፣ የአዲስ አበባ፣ የጎንደር እና የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተገኝተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

Previous articleበኩር ጥር 18/2012 ዓ/ም ዕትም
Next article“ይህን የመሰለ ከባድ የእናቶች ሁለተኛ የምጥ ሰዓት ላይ እንዴት አስችሎዎት ዝም አሉ?” ታማኝ በየነ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡